Get Mystery Box with random crypto!

'ናፊባ' ክፍል ~ ዘጠና አንድ በአምባዬ ጌታነህ @Adwa_1888 የራሺያው Russian Times | የዮቶር ልጅ - አምባዬ ጌታነህ

"ናፊባ"
ክፍል ~ ዘጠና አንድ
በአምባዬ ጌታነህ @Adwa_1888
የራሺያው Russian Times ጋዜጣና የአሜሪካው Washington Post የኢንስፔክተር ሸዋንግዛውን መታፈን የዜና አርዕስታቸው በማድረግ የእርሱንና የልጆቹን ምስል የፊት ገፅ በማድረግ ከሰፊ ሀተታ ጋር ለንባብ አበቁ። የኢትዮጵያ መንግስት በፍጥነት እየተሰራጨ ላለው የኢንስፔክተሩ አፈና ይህን ያህል አጥጋቢ መልስ ባይሆንም አፈናውን እንደሚቃወምና መንግስት አስፈላጊውን ሀይል በመጠቀም ወንጀለኞችን ለፍርድ እንደሚያቀርብና ኢንስፔክተሩን ነፃ እንደሚያወጣ ዝቷል። ነገር ግን ዜጎቹ ደግሞ በተደጋጋሚ የመንግስትን ለዘብተኝነትን እየተቸ ከአንድ ጊዜም ሁለት ጊዜ የመንግስትን የተሳሳተ አካሄድ ስለሚቃወም ኢንስፔክተሩን ያፈነው ራሱ መንግስት ነው ባይ ናቸው። ይህንን የህዝቡን ፍላጎት የሚያራምዱ በርካታ ተከታይ ያላቸው የማህበረሰብ አንቂዎችም በስፋት እያስተጋቡት ይገኛሉ። በሌላ በኩል ኢንስፔክተር ሸዋንግዛው በኃላፊነት የሚሠራበት ዋና የግድያ ወንጀል ክፍል ያሉ ባልደረቦች በኢንስፔክተሩ መታፈን ዙሪያ የመንግስት እጅ ይኖርበታል በማለት ጥርጣሪያቸውን ያልደበቁ አባላቶች እንዳሉ አንዳንድ የማህበረሰብ አንቂዎች የተለያዩ ማስረጃዎችን ዋቢ በማድረግ በማህበራዊ ትስስር ገፆቻቸው ሰንደዋል። የኢንስፔክተሩ መታፈን ታላቅ ፖለቲካዊ ኪሳራ ነውና በኢንስፔክተሩ ጉዳይ መንግስት የወሰደው አቋም ካለ ባስቸኳይ ማብራሪያ መስጠት አለበት ሲል የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ይገልፃል"በማለት የፕሬዚዳንቱን ሙሉ ሀሳብ ያሰፈረውን ዜና በስፋት ያትታል። በአንፃሩ የሩሲያ ታየምሱ ዜና ደግሞ "መንግስት የህዝቡን ስሜትና ፍላጎት በሚገባ ሊረዳና ሊያከብር ይገባል። በማንኛውም ዓለም የመንግስት ጠመንጃ ያዥ ሀይሎች እውነትንና ፍትሕን በሚሹ አቢዮተኞች ድል ተደርገዋልና መንግስት ከወዲሁ የህዝቡን ተቃውሞ በጠመንጃ እፈታለሁ ብሎ የሚያስበውን ከመጀመሪያው እንዳይጀምር ከጥልቅ ምሳሌና ማብራሪያ ጋር የሩሲያን የውጪ ጉዳይ ምኒስቴር ቃለ አቀባይ ዋቢ በማድረግ አስፍሯል። በአንድ ጀንበር የአለምን የዜና ሽፋን የተቆጣጠረው የኢንስፔክተሩ መሰወር የኢትዮጵያ መንግስትን ክፉኛ ከማስቆጣትም በላይ አስፈርቶታል። ህዝቡ ደግሞ ከቀፎው ወጥቶ የመንግስት ሁነኛ ቦታዎች ላይ ተቃውሞ ለማስነሳት በመንጋ ለመውጣት የልባቸውን ደወል ብቻ እየተጣበበቁ ይገኛሉ። ውጤት አልባው የፓርላማና የምኒስቴሮች ስብሰባ አሁንም በጭንቀትና በግራ መጋባት ያለ ስአታቸው ቀድመው ወንበራቸውን ይዘው በመጠባበቅ ላይ ይገኛሉ።የጦር አዛዦችና የመከላከያ አባላትም በዚህ ልዩ የሆነ ስብሰባ ላይ ለመሳተፍ በጊዜ ተገኝተዋል። በዚህ አስቸኳይ ስብሰባም የጦር ውሳኔዎች ሳይቀሩ ይተላለፋሉ ተብሎ ይጠበቃል። የኢትዮጵያ መንግሥት አይንና ጆሮ ነው የሚባለው የቴሌቪዥን ጣቢያ ዋና አስተዳዳሪም በስብሰባው ላይ ተገኝቷል።
**********
"አለቃ ይሄ ነገር በጣም እየተስፋፋ ነው። ምንም የምናደርገው ነገር የለም?" "የምናደርገው ነገርማ አለ አሁን ነው ወደ ኢንስፔክተር ሸዋንግዛው መሄድ ያለብኝ።"በማለት በፈገግታ ታጅቦ ቀጥታ ኢንስፔክተር ሸዋንግዛው ወዳረፈበት ክፍል ሊገባ ሲል ከእንደገና ሀሳቡን በመቀዬር "አይ ጥሩ አይደለም ወደ እኔ ክፍል እሱ ቢመጣ የተሻለ ነው። ልጆቹ ፊት ማናገሩ ጥሩ አይደለም። ምን አልባት ፍርሃት ሊያድርባቸው ይችላል። ስለዚህ እናንተ አምጡልኝ" በማለት ወደ ዋና ቢሮው የሚወስደውን ኮሪደር ይዞ መሄድ ጀመረ። ምድራዊው ሰፊ ነፀብራቅ።በርካታ ኮምፒወተሮችና ካሜራዎች የሚበዙበት ይህ ከምድር በታች የተሰራ ህንፃ ፍፁም እጅግ በሚማርኩ ጌጣጌጦችና የቀለም ቅቦች ዲዛይኖች የተዋበ ሲሆን በየግድግዳዎቹም ላይ የኢትዮጵያን መልክና ገፅ የሚያንፀባርቁ ስዕሎች ተሰቅለውበታል። ለአብነት ያህል የአልነጃሺ መስጊድ፣የንግስተ ሳባ ደንገጡሮችና ሎሌዎች እንዲሁም ንጉሱ ሰለሞንን ለመጎብኝት ወደ እየሩሳሌም በመሄድ ላይ እያለች የሚያሳይ ምስል፣ የቅኔ ተማሪዎችና ቁምጣ ለብሰው በረባሶ ጫማቸውን ተጫምተው ራሳቸው ላይ በእዳይት የተጠለፈ ጉኒና በማድረግ ከመርጌቶች ትምህርታቸውን በዋሸራ ሲከታተሉና ሲያጠኑ የሚያሳይ ምስል ይታያል እንዲሁም ወሎ ወረባቦና ሀራ ላይ ታላቅ ሊቅ ዑለማዎች ደረሳቸውን ቁራዕን ሲያስቀሩ የሚያሳይ ምስል፣ በሌላኛው ኮሪደር ደግሞ በሬዎቹን እያረሰ ከኋላው የምታጎለጉለውን ሚስቱን ዞሮ ሲመለከት የሚያሳይ ምስል፣ በሌላኛው ግድግዳ ደግሞ የገደሉ አፋፍ ላይ ተቀምጦ ከፊት ለፊቱ ማዶ ላይ የሚወርደውን የፏፏቴ ድምፅ እየሰማና ጭሱን እየተመለከተ በዋሽንቱ ተፈጥሮን በትንፋሹ የሚዘክር ድንቅ እረኛ ይታያል። ይህ ምስል ድምፅ ሲያወጣ ነፍስን በዋሽንቱ ዜማ ሲያመንን ከምስል አልፎ በድምፀም የሚያጋባ ነው። በሌላኛው ገፅ ደግሞ አንዲት አቅመ ደካማ የምትመስል ሴት አንገቷን ወደ ግራ ጠንዘል አድርጋ ወፍጮ ስትፈጭ ያሳይና ከእሷ አናት ላይ ደግሞ ዶሮዎች የቤቱ ምሰሶ ላይ ቆመው ያሳያል። ይች የተንጋደደች የገጠር ጎጆ ውስጥ የሚታይ ምስልም ሌላኛው ትልቅ ሀሳብ የተንፀባረቀበት ምስል ነው። እነዚህነና ሌሎችም በርካታ አይነት ምስሎች ያሉበትን ቦታ አልፎ ወደ ቢሮው ሊገባ ሲል በሩ ላይ በትልቅ ሸራ የሚታየው ምስል ይበልጥ ኢትዮጵያን የሚገልፅ ይመስላል ሁለት መርጌቶችና ሼሆች በሀሴት ፈገግ ብለው የሚታዩበት ምስል ሲሆን ከጎኑም በርካታ ሰዎች የሚገበያዩበት የገበያ ቦታ ይታያል። ምስሉ የድሮ መልክ እንዲኖረው black &white ቀለምን ተጎናፅፏል።በሩን ከፍቶ በቀጥታ ኮቱን አውልቆ የኮት ማስቀመጫው ላይ አስቀምጦ ወንበሩ ላይ ተቀመጠ። ወንበሩን ወደ ኋላና ወደፊት እያደረገ አንድ ክብ የሚሆን ከተሽከረረከ በኋላ ከመሳቢያው አንድ ሪሞት አውጥቶ የቀይ መብራቷን ሲነካ ፊት ለፊቱ የተቀመጠው ባለ 45 inch የቴሌቪዥን እስክሪን ተከፍቶ በጥሩ ጥራት እያንዳንዱ ኮሪደር ላይ ያሉ እና ውጪ ላይ የተገጠሙ ካሜራዎቸን ይመለከት ጀመር።
ኢንስፔክተር ሸዋንግዛው የልጆቹን ፀጉር እያሻሸ ባለበት ወደ ጆሮው ጠጋ ብሎ" አለቃዬ አሁን ሊያገኝህ ይፈልጋል። ለአንተና ለልጆችህ ባለው ፍቅርና አክብሮት የተነሳ ወደ ክፍልህ መጥቶ ሊያገኝህ ነበር ሀሳቡ ነገር ግን ልጆችህ እንዳይፈሩ በማሰብ ወደ ቢሮው እንድትመጣ ይፈልጋል" አለ ቀልጠፍ ያለና ፊቱ ላይ የፈገግታ ፅንፍ የማይለየው ወጣት። ኢንስፔክተር ሸዋንግዛው በፅሞና ካዳመጠው በኋላ በወጣቱ ሀሳብ በመስማማት አንገቱን ነቀነቀና ልጆቹን በቀስታ አስተኝቶ ተነስቶ ይከተለው ጀመር። ኢንስፔክተር ሸዋንግዛው የግድግዳ ምስሎቹን ሲመለከት ፍፁም የሆነ አግራሞትን ፈጥሮበታል። በዛን ስአት በርካታ ጥያቄዎችን ራሱን እየጠየቀ ስለሰውዬው ሀገራዊ ፍቅር ለመገመት አፍታ አልፈጀበትም።ስዕሎቹ እንኳን የሀገር ፍቅር የሚሰማውን አንድ ኢትዮጵያዊ ይቅርና የሌላ ሀገር ዜግነት ያለውን ሰው ሳዬቀር የሚያማልሉና ሆድ የሚያባቡ ናቸው።ፍፁም ሰላማዊ ና እረፍት እንዲሰማ የሚያደርጉ ኢትዮጵያዊነትንና ኢትዮጵያዊያንን የሚገልፁ በመሆናቸው ኩራትም ሀሴትም ተሰምቶታል። ምስሎቹን ለመመልከትና በደንብ ለማጤን ዘግየት ሲል ከፊት ለፊት ሆኖ የሚመራው ወጣት ቆም ብሎ ሲጠብቀው ከእንደገና እየጠበቀው መሆኑን ሲመለከት ሲከተለውና ሲተያዩ በፈገግታ እየተሸነጋገሉ ዋና ቢሮው ደረሱ።

@amba88
@amba88