Get Mystery Box with random crypto!

ዘመናዊ የባላባት ስርኣት ድሮ በዘመነ ባላባት ህዝብ በተለያየ እርከን የተከፋፈለ ነበር፡፡ አንደኛ | አል ሂዳያ የየቲሞች መርጃና በጎ አድራጎት ጀማአ 0993632424//0703136300አዲስ አበባ

ዘመናዊ የባላባት ስርኣት
ድሮ በዘመነ ባላባት ህዝብ በተለያየ እርከን የተከፋፈለ ነበር፡፡ አንደኛ ደረጃ ሰው፣ ሁለተኛ ደረጃ ሰው፣ ሶስተኛ ደረጃ ሰው…፡፡ የታችኛው ደረጃ ለላይኛው ይሰግዳል፣ ያጎበድዳል፡፡ ታችኛው ላይኛውን ሊያገለግል “የተፈጠረ” ነው፡፡ ላይኛው ሲበዛ የተንቀባረረ ነው፡፡ ከሌሎች ጫፍ ሳይደረስ በራሱ አጥር ውስጥ በተገደበ “ጃሎ” ቢልም በተቻለ፡፡ አንጀቴ መቻል! እሺ ይሁን ችግሩ ግን መንቀባረሩም አጉራ-ዘለል መሆኑ ነው፡፡ ባለ ነጭ በቅሎው፣ ባለ ነጭ ጭራው፣ ኩፍሱ የላይኛው መደብ አባል ሲያልፍ ሲያገድም እገረ ቡላው፣ ፀጉረ ጨብራራው፣ አመዳሙ የታችኛው መደብ አባል እንደ ሰፌድ እየተዘረጋ፣ እንደማጭድ እየተቆለፈ ካላሳለፈ ወዮ ለናቱ! የሚለፋው ለሌላ! የሚኖረው ለሌላ! ግን አይበቃም በዚህም ላይ ብዙ ግፍ አለ! “ይቺም እንጀራ ሆና ሚጥሚጣ በዛባት” አሉ፡፡ ቢመርህም ሲያምርህ ይቀራል እንጂ ሌላ ህይወት አታስብ፡፡ በቃ መሮህ መሮህ መሮህ … ከዚያ መሮህ ስለ ምሬትህ ትማረራለህ፡፡ እንደ መረረህ ትኖራለህ እንደመረረህ ትሞታለህ፡፡
“ለምስለኔው ሙክት ለጭቃው ወጠጤ
እንዲህ ሆኜ ነው ወይ ባገር መቀመጤ” ትል ይሆናል፡፡ ካልተመቸህ ካገር ውጣ! ምን ታመጣለህ?! “እምቢ” ካልክ ደግሞ ያንተው ቢጤ እልቆ መሳፍርት አመዳም ጭሰኞችን ያን መከረኛ ከርሳቸውን ወጥቆ ባንተ ላይ ያዘምታቸዋል፡፡ ከመቅፀብትም ትቢያ ያደርጉሃል፡፡ ባይሆን አንዳንዴ ይሳካል፡፡ እምቢታ እምቢተኞችን ይጠራል፡፡ የእንቢተኞች ህብረት ይፈጠራል፡፡ “ፋኖ ተሰማራ” ይዘመራል፡፡ የባላባቱ አከርካሪ ይሰበራል፡፡ ምን ዋጋ አለው እፎይ አትል! ሌላ የባላባት ስርኣት ቀስ እያለ ይጎመራል፡፡ እጀ ጠባቡ በቦላሌ ይቀየራል፡፡ የትላንቱ ባላባት መኮፈሻ ነጭ ፈረስ ተገባብጦ እያነከሰ ጋሪ ይጎትታል፡፡ አንተ ግን ያው ነህ! ከየተረኛው ባላባት ወፍጮ ገብተህ ትፈጫለህ፡፡ እምቢ ያልክ እለት እንደ አንጣሪያ፣ እንደ አቀንጭራ፣ እንደ ቅንጬ አረም በደቦል ተመንጥረህ ትጣላለህ፡፡ አይበቃህም፡፡ መጠጥ ስትል በደንብ ሳትደርቅ ዘርህ ሳይረጭ ትቃጠላለህ፡፡ ተረኛው ይቀጥላል፡፡
ግን ያኔ ያኔ ነበር፡፡ ድሮ በቃ ድሮ ነበር፡፡ አሁንስ በድሮ በሬ አይታረስ ነገር? እኔን ግራ የሚገባኝ ግን የታሪክ አዙሪቱ ነው፡፡ “ታሪክ እራሱን ይደግማል” የሚባለው እውን ተረት ነው ወይስ ሀቂቃ? የትላንቱ የባላባቶች ታሪክ የቋንቋ፣ የቅብና የውርርስ ሂደቱ እንጂ ለካስ ዛሬም ቀጥሎ ኖሯል?!
እስኪ አስቡት! በአለም ላይ ፍርድ ቤት አካባቢ የሚታየው ድንበር ዘለል አጀብ ከባላባቱ ስርኣት ምን ያህል ነው ርቀቱ? ባለጉዳይ ጠንቋይ ቤት እንደገባ ቂላቂል ካልተሸማቀቀ በቃ የፍትህ ስርኣቱ ክብሩ ተደፍሯል ማለት ነው፡፡ ታዲያ “እንዲህ አይባልም”፣ “እንዲህ አይቀመጥም”፣ “እንዲህ አይቆምም”፣ … እያሉ ሰንሰለታማ መመሪያዎችን ከሚደረድሩት እናቶቻችን ምን ይሆን ልዩነቱ? ህገ-ደንቦች ፋሽናቸው ያለፉ፣ አሰልቺ፣ ማዘር እስታይል ትብትቦች አድርገን መቆጠራችን ለምን? የዳኞች ዋና አላማ ፍትህን ማስፈን ወይስ አስፈሪ አባታቸው ገብቶ በስጋት ዐይናቸውን እንደሚያቁለጨልጩ ህፃናት ፍትህ ጠባቂዎችን ማርበትበት ነው? ዶክተሮች አካባቢ የሚታየው መረን የለቀቀ አንባገነንነትስ ሃይ ባይ ማጣቱን ምን ይሉታል? ስነ ምግባር የሚባል ነገር አልነበረም? ዛሬ ቀረ ወይስ መልኩ ተቀየረ? ድብርብር፣ ጭፍግግ፣ ኩፍስፍስ፣ ቅብርርር እያሉ በበሽተኛ ወገን መሀል መንጎባለል ምን የሚሉት ጀብደኝነት ነው? ተረኛ በሽተኛ ተኮርትሞ ተቀምጦ በዘመድ በትውውቅ በጎን ማስገባቱስ ምን የሚሉት ጭራቃዊነት ነው? አቤት ወጥ ረገጥነት! የዚህ የምትበሻቀጥበት ምስኪን በሽተኛ ድምር ጥረት እኮ ነው አንተን ለወግ ማዕረግ ያበቃህ!!! ደግሞ አስተውል አንበሳ በበሽተኛ አንበሶች መሃል የሚጀነን ከሆነ አንበሳ ሳይሆን ጂብ ሆኗል ማለት ነው፡፡
እዚያጋ ደግሞ የበሰበሰውን የጥንቱን የባላባት ስርኣት የሚኮንን የዩኒቨርሲቲ አስተማሪ አንዴ በአይነ ህሊናችሁ ቃኘት አድርጉትማ፡፡ ስለ መልካም አስተዳደር ይሰብካችኋል:: እሱ ግን መልካም ስብእና አልሸተተውም፡፡ መሪዎች አካባቢ ያለውን አንባገነናዊ አካሄድ ከፊታችሁ በምላሱ ያንኮታኩተዋል፡፡ መላ ሰውነቱ ግን ከአንባ ገነንነት የተገነባ ነው፡፡ ምነው ግን ለራሱ ሲሆን “ዘመናዊ” የባላባት ስርኣት ሊገነባ ይታገላል? ስለመከባበር አትሞግቱኝ፡፡ እኔ ከዚያ በላይ ስላለው ሰፈር ነው እያወራሁ ያለሁት፡፡ በቃ እንዲሁ ነው፡፡ በየሙያ ዘርፉ ሁሉም የራሱን የፊውዳል ስርኣት ገንብቷል ወይም እየገነባ ነው፡፡ “ለምን” ካልክ የሙያውን ክብርና ዋጋ አጣቅሶ ያስረዳሃል፡፡ ባይገባህም ይገባሃል፡፡ አሁንም ካልገባህ ግን ያስገባሃል፡፡ “ፍየል ወዲያ ቁዝምዝም ወዲህ” ይሏል ይሄ ነው፡፡ በነገራችን ላይ ፌስቡክም ላይ የፌስቡክ ባላባቶች መሆን የሚያምራቸው የትየሌሌ ናቸው፡፡ ምንም እንኳን በየጥጉ የሚያደፍጡ የፌስ ቡክ ሽምቅ ተዋጊዎች ለፌስቡክ ባላባቶች ምቾት ቢነሱም በተለያየ መልኩ ሰፋፊ ርስቶችን ዘርግተው ፌስቡከኛውን ሁሉ “እኛ እናውቅልሃለን”፣ “እንዲህ ተንፍስ”፣ እንዲህ አስነጥስ” የሚሉት ቀላል አይደሉም፡፡ “ኧረ እንዴት ነው ነገሩ” ብሎ የጠየቀን ሁሉ የፌስቡክ ጭሰኛ ለማድረግ መጠነ ሰፊ ዘመቻ ወይም ወረራ የሚፈፅሙ ባላባቶች እንዳሉ ፌስ ቡኩ ይቁጠረው፡፡ የሚገርመው እነዚህ የፌስ ቡክ ባላባቶች አማራጭ የነፃ ሀሳብ ማንሸራሸሪያ እንደሆኑ የሚሞግቱ፣ ስለ ነፃ ፕሬስ ሌሎችን የሚኮንኑ፣ በነፃ ፕሬስ ፀበል ፀዲቅ ሌሎችን የሚያጠምቁ ከመሆናቸው ጋር ከነሱ የተለየን ሀሳብ ለማስተናገድ ግን ዲሹም፣ ሪሲቨሩም፣ አንቴናውም ይገዳቸዋል፡፡ …
ህይወት እንዲህ ይቀጥላል፡፡ ይሄ ሲያልፍ ተረኛው ይገባል፡፡ እብድ አለም እብድ ስብስብ እብድ ስርአት፡፡

@HidayaTv