Get Mystery Box with random crypto!

ወንድሜ ሆይ! እህቴ ሆይ! ልጆቻችን ከአላህ የተሰጡን አማናዎች ናቸው፡፡ አማናን በአግባቡ አለመያዝ | Al HiDAYA MidiA የተበዳይ ሙስሊሞች ጉዳይ ያሳስበኛል📚ተዉሂድ የሁለት ሀገር የስኬት 🔑ቁልፍ ነዉ📖

ወንድሜ ሆይ! እህቴ ሆይ! ልጆቻችን ከአላህ የተሰጡን አማናዎች ናቸው፡፡ አማናን በአግባቡ አለመያዝ ከአላህ ዘንድ ያስጠይቃል፡፡ መቼም የልጆች አስተዳደግ በኢስላም ያለው ቦታ የላቀ እንደሆነ አይሰወርም፡፡ ከልብስና ከጉርስ ባለፈ አጠቃላይ ጤናማ የሆነ አስተዳደግ እንደሚገባቸው ይታወቃል፡፡ ስለ አካላዊ ደህንነታቸው ከምንጨነቀው በበለጠ ስለ አእምሯዊና ስነልቦናዊ ጤንነታቸውም ልንጨነቅ ይገባል፡፡ ስለ አካዳሚ ትምህርታቸው ከምንጨነቀው በበለጠ ዘላለማዊ ህይወታቸውን ስለሚወስነው ስለ ዲናዊ ግንዛቤያቸውም ልንጨነቅላቸው ይገባል፡፡ ዛሬ ለጤናማ የልጆች አስተዳደግ የምናደርገው ጥረት ነገ ጤናማ ማህበረሰብ ይኖረን ዘንድ የመሰረት ድንጋይ ነው፡፡ በእርግጥ አሁን የፈለግኩት ስለ አጠቃላይ የልጆች አስተዳደግ ማውራት አይደለም፡፡ ይልቁንም “ጭራቅ መጣብህ!” “የሰው ጅብ መጣብህ”፣ “አያ ጅቦን እጠረዋለሁ” እያልን ልጆችን የምናስፈራራበት ውርስ ቢቀንስም ዛሬም አለ፡፡ በተጨማሪም አንዳንድ ከነጩ ሰው የሚመጣውን ሁሉ እንደወረደ የሚወስዱ ወላጆች ልጆቻቸው ሲረብሹ በአንድ ክፍል ቆልፎ በመዝጋት ለብቻ እያቆዩ የሚቀጡበት መንገድ አደጋ እንዳለው ማስታወስ ነው የፈለግኩት፡፡ ሀሳቡን የወሰድኩት ከታላቁ ዐሊም ሸይኽ ሙሐመድ ኢብኑ ሷሊሕ አልዑሠይሚን ረሒመሁላህ ነው፡፡ በአዲስ መስመር እንገናኝ፡-
“… ‘እንትን መጣብህ’ ‘እንደዚህ መጣብህ’ እያሉ በማስፈራራትና በማሸበር አንዳንድ መሀይማን ሰዎች በትንንሽ ልጆቻቸው ላይ የሚፈፅሙት አለ፡፡ ህፃኑ ፈሪ ሆኖ ይቀራል፡፡ ይሄ ፍርሃትና ርደት ከልቡ ይቀርና ባህሪው የሚሆን አለ፡፡ ሁሌ በፍርሃትና በጭንቀት ላይ ይሆናል፡፡ ይሄ እንግዲህ አባት በልጁ ላይ፣ እናት በልጇ ላይ የሚፈፅሙት ግፍ ነው፡፡
ኧረ እንዲያውም አንዳንድ ቂላቂሎች ህፃኑ ሲያጠፋ ብቻውን ከአንድ ክፍል ውስጥ አስገብቶ የሚዘጋ እንዳለ ተነግሮናል፡፡ ህፃኑ ይጮሃል፤ ነገር ግን አያዝንለትም፤ በሩንም አይከፍትለትም፡፡ ይሄ በጂን እንዲያዝ ከሚያደርጉ መንሰኤዎች ውስጥ ነው፡፡ ልክ በአንዳንድ በጂን በተለከፉ ልጆች ላይ ያለ ጂን እንደተናገረው ማለት ነው፡፡ ወላጆቹ በር ዘግተውበት ሲጮህ ጊዜ እንደያዘው የተናገረ አለ፡፡ ስለዚህ ለእንዲህ አይነት አደጋዎች መንሰኤ ከሚሆኑ ዛሬ ብዙ ሰዎች ከተዘፈቁባቸው ነገሮች ልንጠነቀቅ ይገባል፡፡…”
ስለዚህ ልጆቻችን ቢቻል ከምክር በዘለለ ወደ ሌላ ቅጣት ልንገባ አይገባም፡፡ አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ ግን የምንቀጣበት መንገድ ጤናማ መሆኑን በውል መፈተሽ ይገባል፡፡ ዛሬ በልጆች ላይ የምንወስደው የተዛባ “ቅጣት”፣ ከብልሹ ቅጣትነቱ ባለፈ እነሱም በተራቸው በዚህ መልኩ ልጆቻቸውን እንዲቀጡ የተበላሸ ውርስ ማቀበል ነው፡፡ በእርግጥ “ልጆች በምንም መልኩ፣ የፈለገ ቢያጠፉ ሊነኩ አይገባቸውም” የሚለው አስተምህሮት ምክንያታዊ አይደለም፡፡ የሰው ልጅ ባህሪው ብዙ አይነት ነው፡፡ ስትመክረው የሚሰማ እንዳለ ሁሉ ለምክር ደንታ የሌለው ብዙ አለ፡፡ ከምክር ይልቅ ቁጣ የሚመልሰው በተጨባጭ አለ፡፡ ከዚህም አልፎ ካልተቀጣ በስተቀር ከጥፋቱ የማይታቀብ ብዙ ልጅ አለ፡፡ ገና ጥፋትን ሲያስብ የሚጠብቀውን ቅጣት ፈርቶ ሊቆም ይችላል፡፡ አዋቂውም እንዲሁ ነው፡፡ ህግ ባይኖርም የሰው ሐቅ የሚፀየፍ፣ ከሰው ላይ እጁን የማያሳርፍ ብዙ እንዳለ ሁሉ ቀጪ ህግ ባይር ኖሮ፣ በአጥፊዎች ላይ የሚወሰዱትን እርምጃዎች ባያይ ኖሮ ከጥፋት የማይመለስ ብዙ ሰው አለ፡፡ ይሄ ለማንም የማይሰወር ሐቅ ነው፡፡ ልጆችም እንዲሁ ናቸው፡፡ ነብዩ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም “ልጆቻችሁን የሰባት አመት ልጆች ሲሆኑ በሶላት እዘዟቸው፡፡ የአስር አመት ልጆች ሲሆኑ ደግሞ (ካልሰገዱ) ግረፏቸው” ማለታቸው ይህንን ሐቅ ፍንትው አድርጎ ያሳያልል፡፡ [ሶሒሑል ጃሚዕ፡ 5868] መቼም ለጠቢብ ነብይ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ሳይኮሎጂ አስተምራለሁ ብሎ የሚዳፈር አይኖርም፡፡ “ከልብ ወለድም አይናገምና፡፡ ይልቁንም እሱ (ንግግሩ) ረእይ እንጂ ሌላ አይደለም፡፡” [አንነጅም፡ 3-4]
ስለዚህ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ልጆችን መቅጣት ተገቢ ነው፡፡ ባይሆን ከግምት ሊገቡ የሚገባቸው ነገሮች እንዳሉ ዐሊሞች ይጠቅሳሉ፡፡ እነሱም፡-
1. ልጆቹ ለቅጣት የደረሱ ሊሆኑ ይገባል፡፡
2. ቅጣትን የሚረዱ (የሚያውቁ) ሊሆኑ ይገባል፡፡ ቅጣትን የማይረዱ ከሆኑ እድሜያቸው ደረሰም አልደረሰም መቅጣቱ ተገቢ አይደለም፡፡
3. የሚቀጣው በምክር ወይም በቁጣና መሰል ነገሮች የማይመለሱ ከሆነ ነው፡፡
4. ቅጣቱ ሲያጠፉ ብቻ ሊሆን ይገባል፡፡ አንዱ ባጠፋውም ሌላውንም መጨመር፣ በማያስቀጣ ጥፋት መደብደብ፣ የውጭ ብስጭትን ልጆች ላይ ማራገፍ፣ ወዘተ ተገቢ አይደለም፡፡
5. በልኩ ሊሆን ይገባል፡፡ የቅጣት አላማው ልጆችን ወደ መስመር መመለስ እንጂ ንዴትን ማብረድ አይደለም፡፡ ጥፋት እንኳን ቢኖር በትንሽ በትልቁ መቀጥቀጥ ሁሌ የሚፈፀም ከሆነ ቅጣት እራሱ ትርጉም ያጣል፡፡ ልጆችም ይደነዝዙና በቅጣት የማይማሩ ይሆናሉ፡፡
6. ቅጣቱ ጉዳት የሚያስከትልባቸው መሆን የለበትም፡፡ ወላሁ አዕለም፡

=
@AlhidayaMidia