Get Mystery Box with random crypto!

ለኡድሒያ የሚበቃው እንሠሣ ተቀባይነት ያለው የእድሜ ገደብ፦ ጃቢር አሏህ መልካም ስራውን ይውደድ | ¶ ፊቅሁል ኢስላም ¶

ለኡድሒያ የሚበቃው እንሠሣ ተቀባይነት ያለው የእድሜ ገደብ፦
ጃቢር አሏህ መልካም ስራውን ይውደድለትና ባወራው ሀዲስ መልእክተኛው እንዲህ ብለዋል፦ "እድሜያቸው መካከለኛ(የደረሱ)
/ከግመል፣ላም፣በሬ፣ፍየል/የሆነቱን እንጂ እንዳታርዱ፡፡ ነገር ግን እናንተ ላይ ጫና የሚያመጣ ከሆነ ከበግ(ትንሿን) እረዱ፡፡[ሙስሊም ዘግበውታል ]
ይህ ሀዲስ ለኡድሒያ እድሜ መስፈርት እንደሆነ ከሚያመላክቱ ሀዲሶች አንዱ መሆኑ ነው፡፡
ከግመል አምስ አመት፣ከከብት(ከላም/ላም) ሁለት አመት፣ ከፍየል አንድ አመት የሆናቸው፡፡[ሸርህ ሙምቲዕ 460/7].

በበግ የእድሜ ላይ ግን ልዩነት ያመጡ ሲሆን፤ ከፊሎቹ አመት የሞላት ፣ ስድስት ወር ፣ ስምንት ወር ብለው ጠቅሰዋል፡፡ [ነይሉል አውጣር 302/5].

ከላይ ያሣለፍነው የጃቢር ሀዲስን ይዘው፤ የሀዲሱንም ውጫዊ ገለፃውን በመያዝ ከኢብን ኡመርና ከዙህሪይ በበግ(ትንሹን) አይበቃም ብለዋል፡፡
ኢማም አንነወዊይ እንዲህ ይላል፦ ለኡድሒያ እርድ ከበግ(ትንሹ)ን ማረድ ፤ከሱ ውጪ ሌላ ተገኝቶም ይሁን ሳይገኝ ለእርድ እንደሚበቃ ከእውቀት ባለቤቶች የአጠቃላዮቹ ምርጫ ነው፡፡ይህንን ሀዲስንም ከበግ(ትንሹ) ውጪ ማረድ የተወደደ መሆኑን ነው የገለፁት፡፡ ሀዲሱ ላይ ግልፅ የሆነ ክልከላ የለም ፡፡ የሀዲሱንም ውጫዊ ገለፆ እንደማንይዝ ሁሉም የተስማማበት ነው፡፡
[ፈትሁል ባሪ ላይ ኢብን ሀጀር ይህን ንግግር አጠንክሮታል 15/10].

የእርዱ ጊዜ

አነስ አሏህ መልካም ስራውን ይውደድለትና የአሏህ መልእክተኛ የእርዱ ቀን እንዲህ አሉ፦ ከሶላት በፊት ያረደ አንደገና ይረድ፡፡ በሌላ ዘገባም፦ ከሶላት በፊት ያረደ፤ ያረደው ለራሱ ነው፡፡ ከሶላት በሗላ ያረደ በእርግጥም እርዱን አሟልቷል፡፡የሙስሊምችንም መንገድ ገጥሞል(አግኝቷል)፡፡[ቡኻሪና ሙስሊም].
ይህ ሀዲስ እንደሚያመላክተው ከሆነ የመጀመሪያው የእርድ ጊዜ ከሶላተል ኢድ በሗላ እንደሆነ ነው፡፡ ነገር ግን ከሶላት በፊት ያረደ ኡድሒያን አላገኘም፡፡ እርዱም ለራሱ ብሎ እንዳረደው እርድ ይሆንበታል፡፡ በዚህም ምንም አይነት ምንዳ አይመነዳም፡፡ እርዱን ከአዲስ ሌላ ኡድሒያ ማድረግ ይኖርበታል፡፡

ከዚህም በተለየ ማሊኪያዎች እርድ የሚባለው ተቀባይነት እንዲኖረው በሌላ መስፈርት አጣምረውታል፡፡ እሱም ኢማም ከማረዱ በሗላ ማረድ አለበት፡፡ ለዚህም ንግግራቸው ያቀረቡት ሐዲስ ሲሆን ፦ ጃቢር እንዲህ ይላል መልእክተኛው መዲና ላይ የእርዱ ቀን አሰግደውን ሲያበቁ ፤ መልእክተኛው አርደው የጨረሱ መስሏቸው፤ ሰዎች ለእርድ ተሸቀዳድመው
እርዳቸውን አረዱ፡፡ መልእክተኛውም ከሳቸው በፊት እርድ ያረደን ሌላ እንዲያርድ አዘዙ፡፡ ስለዚህም መልእክተኛው ሳያርዱ አያርዱም ነበር፡፡[ሙስሊም ዘግቦታል].
ነገር ግን ይህ ማሊኪያዎች የጠቀሱትን ማስረጃ አንዳንድ ኡለማዎች በመልእክተኛው ብቻ የተገደበ ነው ሲሉ መልስ ሰጥተዋል፡፡
ኢማሙ አሽሻፊዒይ ይህ ከላይ ያለፈው ንግግር ከጊዜ ጋር የተቆራኘ (የተገደበ) እንደሆነ እንዲህ ሲሉ ተናግረዋል፦ የአድሀ ወቅት ኢማሙ ለሶላት እስከሚገባበት ልክ ነው፡፡ ይህ ማለት ፀሀይቷ ብርሀናማ ስትሆን፤ ሁለት ረከዐን ይሰግድና ሁለት አጠር ያሉ ኹጥባዎችን ያደርጋል፡፡ በዚሁ በቀኑ ክፍል አጠናቆ ሲሄድ እርዱም ይፈቀዳል፡፡ [መዓሊም አስሱነን 234/2].
ስለ ማብቂያው(ማገባደጃው) መቼ ነው ለሚለው ሀዲስ የገለፀው ሲሆን እሱም፦
ሁሉም አያመ አትተሽሪቅ(ከእርዱ ቀን አንስቶ እስከ ዙል ሂጃ 13 ፀሀይ መጥለቂያ)እርድ አለ የሚለው ነው፡፡

በነውሩ ምክንያት ለኡድሒያ ማይበቁ እንስሣት
በራእ ኢብን ዓዚብ የአሏህ መልእክተኛ እንዲህ አሉ፦ አራት አይነቶች ለኡድሒያ አይበቁም 1.እውርነቷ ግልፅ የሆነ እውር 2.በሽተኛ በሽታኝነቷ ግልፅ የሆነ 3. አንካሳ ስብራቷ ግልፅ የሆነ 4. ስጋ የሌላት ከሲታ የሆነች፡፡[አቡ ዳውድ እና ቲርሚዚይ ሶሂህ ብለው ዘግበውታል].
ዓሊ አሏህ መልካም ስራውን ይውደድለትና እንዲህ ይላል፦ መልእክተኛው አይንንና ጆሮን እንድንመለከት አዘውናል፡፡ ጆሮ የተቆረጠ፣ ጆሮ ላይ ቀዳዳ ያለበትና የጆሮ ጫፍ ወይም ጥግ ላይ እንከን ያለበትን ለኡድሒያ እንዳናደርግ ከልክለውናል፡፡ [አቢዳውድ፣ ነሣዒ፣ ትርሚዚይና ኢብን ማጀሕ ሶሂህ ብለው ዘግበውታል].
እነዚህ ሀዲሶች እንደሚያመላክቱት ከሆነ ጆሮ ላይ እንከን መኖር፣ግልፅ የሆነ ስብራት(አንካሳ)፣ ግልፅ የሆነ ከሲታነት፣ ግልፅ የሆነ እውርነትና ግልፅ የሆነ በሽታ እነዚህ ለኡድሒያ በቂ ያልሆኑ መሆናቸው ነው፡፡
በሽታው ወይም ስብራቱና መሰል እንከኖቹ ትንሽና ግልፅ ያልሆኑ ከሆኑ ኡድሒያ ለማድረግ በቂ ይሆናሉ፡፡ ለምን ከተባለ ሀዲሱ ላይ "ግልፅ የሆነ" በሚል ተጣምሯልና፡፡
እንደ እውርነትና ስብራት ከነዚህ በተጠቀሱት እንከኖችና ከነሡ የበለጡ እንከኖች ከተገኙ ኡድሒያን በነዚህ ማድረግ አይበቃም፡፡[ነይሉል አውጣር 206/5].
ለኡድሒያ ግዢ ጥሩውን መምረጥ ይወደዳል፡፡ከላይ ሀዲሱ ላይ እንዳሣለፍነው "አይንና ጆሮን እንድንመለከት ታዘናል" እንዚሁ በሌላ ሀዲስ አቢ ኡማማ እንዲህ ይላል " ለኡድሒያ ብለን መዲና ላይ እንስሳቶችን እናደልብ ነበር፡፡ሙስሊሞችም ያደልቡ ነበር፡፡"[ቡኻሪይ በተእሊቅ ዘግቦታል9/10].
ኡድሒያው ላይ ያለፋብን ሀዲሶች ላይ ከተጠቀሱት እንከኖች ውጪ ከተገኘባቸው ለኡድሂያ መቅረብ ይችላሉ ኡድሒያውም በቂ ነው፡፡ በላጩ ከየትኛውም ጉድለት የጠራው ከመሆኑም ጋር፡፡ ስለዚህ ቀንዱ ሙሉውን ወይም ከፊሉን የተሠበረ፣ ጥርሱ የተሠበረ፣ጭራው የተቆረጠና ሌሎች ኡድሒያው በቂ ከመሆን ምንም ተፅዕኖ የላቸውም፡፡ ለምን ከተባለ እነዚህን አስመልክቶ (ኡድሒያ በነዚህ አይበቃም) ብለው የተዘገቡት ሀዲሶች ደካማ(ውድቅ) ናቸው፡፡ [ሙሓላ 9-13/8].

ለአንድ ሠው የሚያብቃቃው የኡድሒያ አደራረግ
ለአንድ ሰው እና ለቤተሠቡ አንድ በግ ያብቃቃዋል፡፡ ከብት(ላም/በሬ)እና ግመል ለሠባት(ከነቤተሰቦቻቸው)፡፡ ስለዚህ ለሰባቶቹ ከብትን ወይም ግመልን ለሰባት ሆነው ይካፈላሉ ማለት ነው፡፡ አጧዕ ኢብን የሣር አቢ አዩብ አል አንሷሪይን በመልእክተኛው ዘመን እርዳቹህ እንዴት ነበር ስል ጠየቁኩት? እርሱም እንዲህ አለ፦ "አንድ ሠው በመልእክተኛው ዘመን አንድ ሠው ለራሱና ለቤተሠቡ አንድ በግን ያርዱና ይመጋባሉም ይመግባሉ፡፡[ሶሂህ ቲርሚዚይ ዘግቦታል]. ስለ ከብትና ስለ ግመል ማስረጃው ጃቢር ባወራው ሀዲስ እንዲህ ይላል፦ "መልእክተኛው በግመል ወይም በበሬ(ከብት) ሰባት ሆነን እንድንካፈል አዘውናል፡፡[ሙስሊም ]
@alfiqhulmuyser