Get Mystery Box with random crypto!

አሁንስ ናፈቀኝ ! ያኔ ገና ያኔ ድሮ ሁሉ ሲኖር ተንቀባሮ ኢትዮጵያ ሐገሬ እማማ ነበር ሲሰማብሽ | የእግዚአብሔር ቃል በሙላት ይኑርባችሁ (pastor Alemayehu Abebe )

አሁንስ ናፈቀኝ !

ያኔ ገና ያኔ ድሮ
ሁሉ ሲኖር ተንቀባሮ
ኢትዮጵያ ሐገሬ እማማ
ነበር ሲሰማብሽ የፍቅር ዜማ
የእድገት መሠረት የሥልጣኔ ማማ

ያገር ባህል ድምቀቱ
የሰው ለሰው ሕብረቱ
የአንድነት ውበቱ
መተጋገዝ መረዳዳቱ
እርስ በርስ መጽናናቱ
መከባበር ቤተሰባዊነቱ
የአንዱ ጥቃት የሁሉ ጉዳት
የአንዱ ውበት የሁሉ ድምቀት
በሌላው ደስታ ተደስተን
በሐዘኑ አዝነን
የወደቀውን እያነሳን
በአብሮነት ሕይወት ተጋምደን
በዜግነት ክብር ኮርተን
የአንድ አብራክ ክፋዮች
የአንድ ሐገር ሕዝቦች
የእናት ኢትዮጵያ ልጆች
ታላቅ ሐገር ይዘን
ምነው መንደር ናፈቀን ?

ዛሬ ዛሬማ ነገር ተገላብጦ
በተቃራኒው ተለውጦ
ወንድም የወንድሙን ሕይወት ሊቀማ
ለመጠፋፋት ሲጠማ
ባገር ሆነን ሐገር ሲናፈቀን
የሚሰማው ሁሉ ሲያሰቅቀን
እነሆ አመታትን ቆጠርን

ለናት ሐገር የሚያስብ ጠፍቶ
ሁሉ አበደ የዘር መርዝ ተግቶ
መካሪ እና ሐይ ባይ የጠፋባት
ሕዝብ በዘረኛነት ተመርዞ
አገር ጥሎ ወደ መንደር ጉዞ
እኔ የኔ እያለ ለሞት ተጠርዞ
ታላቅ የተባለው ሕጻን ልጅ ሆነብን
አንቀልባ እየገዛን ስንቱን ሰው አዘልን
ያስተምራል ብለን አክቲቪስት ያረግነው
ወደ እናቱ ሸክም ተመልሶ አየነው !

ነገር ሁሉ የመልካሙ ተገላቢጦሽ
ወየው ሐገሬ ምን ላድርግሽ
አስለቀሰኝ የዛሬ ላይ ምጥሽ
የትውልዱ ሩጫ ፍለጋ ሲፈተን
እውቀት ጥሎ ዘሩን ሲተነትን
ፍቅር ጥሎ ጥላቻን
ክብር ጥሎ ውርደትን
አገር ጥሎ መንደሩን
ያባት ጉምጉምታ የእናት ሐዘን
እባክህ ፈጣሪ በቃ በለን !

ያን ሁሉ መተሳሰብ ፍቅር ጥለን
ዛሬ ዛሬ ላይ ይኸው ወድቀን
መሥራት ቀርቶ ለአመጹ እጅ ሰጠን
የሟቹን ሞት አልወድም ያለ ፈጣሪ
የእውነት የጽድቅና የፍትህ መሪ
ወየው ለኛ የሚበጀንን ላላወቅን
ቅኑን መንገድ ጥለን አመጻን ለመረጥን
በለው በለው ባዩ አስተኳሹ በዝቶ
ሐገር ሰላም አጥታ ጭንቀተ ተንሰራፍቶ
አልሚ ሳይሆን አፍራሽ ባገር የናኘበት
ወይ አገሬ ጫካው ከየት ላምጣሽ
ብፈልግሽ ብናፍቅሽ ከየት ላግኝሽ
ዲያስፖራው ከምቾት ማማ ላይ
በለው በለው እንጂ ስቃይሽን ላያይ
ወንድማማቾች ጦር ሲማዘዙ
ጠላቶችሽ በደስታ ስካር ሲፈነጥዙ
አመጻ ጦርነት ሲስፋፋ
ምነው አስተዋይ ጠፋ ?

አስታራቂ ለሰላም የሚጮህ
ሁሉ አገርህ ሁሉ ወገንህ
የሚል ሁሉን በእኩል የሚያይ
ሰላምን አስፍኖ የሚያሳይ
ላገር ለወገኑ የሚያስብ
ሁሉን በአንድ እቅፍ የሚሰበስብ
አስፍቶ የሚያይ አርቆ አሳቢ
ወላጅ ያጡትን አሳዳጊ ቀላቢ
የአባቶቹን ኪዳን ጠባቂ
እውነትና ጽድቅን አርቃቂ
የተናገረውን የሚኖር መራቂ
አሁንስ ናፈቀኝ የአንድነት ድምቀቱ
የመከባበር ክብረቱ የፍቅር ውበቱ !