Get Mystery Box with random crypto!

የጎዱህን የምትላቸውን ለመባረክ የምስጋና ቀን አዘጋጅ ! ' ጌታም የጭንቀትን እንጀራና የመከራን | የእግዚአብሔር ቃል በሙላት ይኑርባችሁ (pastor Alemayehu Abebe )

የጎዱህን የምትላቸውን ለመባረክ የምስጋና ቀን አዘጋጅ !

" ጌታም የጭንቀትን እንጀራና የመከራን ውኃ ቢሰጥህም አስተማሪህ እንግዲህ ከአንተ አይሰወርም፤ ዓይኖችህ ግን አስተማሪህን ያያሉ፥ወደ ቀኝም ወደ ግራም ፈቀቅ ብትል ጆሮችህ በኋላህ፦ መንገዱ ይህች ናት በእርስዋም ሂድ የሚለውን ቃል ይሰማሉ። (ት.ኢሳ 30 :-20-21) ጭንቀት እና መከራውን የሰጠህ ጌታ ሆኖ ሳለ ስለምን በአስጨናቂዎችህ እና መከራን ባሳዩህ ሰዎች አስፈጻሚው ታዝናለህ ታቄማለህ ? አየህ እነርሱ ጉዳይ አስፈጻሚ ብቻ ናቸው ።

የጭንቀት እንጀራ እና የመከራ ውሃ አያስደስትም አንዳንዴ እንጀራውም ውሃውም ከእንባህ ጋር ወደ አፍህ የሚገባ ይሆናል። ታለቅሳለህ ታነባለህ በምሬት ትንገበገባለህ ይሁን እንጂ ለገር ለሁ ለበጎ መቀየሩ አይቀሬ ነው ።

በቆይታ መከራው የመጣው ጭንቀቱ የመጣው ለጥቅምህ ለጥቅምህ እንደሆነ ይገባሃል ። አየህ መራራውን ያላየ የጣፋጩን ጣዕም አያደንቅም ። ሐዘንን ያላየ የሐሴት እና የደስታ ልኬት የለውም።ስለዚህ ነገር ቢመርህም ቢጨንቅህም አስተማሪህ ካንተ ጋር ነውና አታስብ በጉዞህም አቅጣጫ ጠቋሚ መሪ አስተማሪ አለ እርሱም ጌታ ነው።

እግዚአብሔር መልካም አስተማሪ ነው። አሳደዱኝ ገፉኝ አሰቃዩኝ አንላቱኝ አንቋሸሹኝ ተፉብኝ ጎዱኝ... ወዘተርፈ
ያልካቸው ሁሉ ባለውለታዎችህ ናቸው ። ዛሬ ይህ እውነት ገብቶህ ለማመስገን እግር ለማጠብ ለመሸለም ተነሳ ስለ እነርሱ እግዚአብሔርን ይመስገን!

እስቲ አስቡ ምንም ብትገፉ አልወደቃችሁም ፣ ቢያሳድዷችሁ ሳያውቁት አሳደው አሳደው የጌታ እጅ ላይ ጣሏችሁ ፣ ቁልቁል ቢወረውሯችሁም ራሳችሁን ያገኛችሁት በተራሮች አናት ላይ ነው ። የተባለባችሁ አልሆነባችሁም አሳደው አሳደው በዘመናችሁ ወደማትችሉበት ክብር አደረሷችሁ ።

እየሆነ ያለው ነገር ቶሎ ባይገባንም ዘመን ይመጣል የሆነው ሁሉ እንኳን ሆነ የቀረው ሁሉ እንኳን ቀረ የምንልበት ። ያኔ ለምን ቀረ ብለን ያነባንበት ለምን ሆነ ብለን ምርር ብለን ያለቀስንበት ጊዜው ሲደር እንዳዲህ ይዘመርበታል ። ከጉዳታችን ትርፉ ይበልጥና ፣ ከሐዘኑ በላይ ደስታው ይልቅና እግዚአብሔር አዋቂ ነው ብለን ለምስጋና እንቆማለን።

ወርቅ በእሳት ነጥሮ ለጌጥ እስኪሆን ጌጥ አይደለም ፣ እንጨት በመጋዝ በመቁረጫ ማሽን በመላጊያ በመሳሰሉት ነገሮች ተሰርቶ ተቆራርጦ ለከበረ ዕቃነት እስከሚበቃ እንጨት እንጂ ዕቃ አይባልም ጌታም እኛን ለመስራት አንዳንድ ሰዎችን እንደ መጋዝ ፣ አንዳንድ ሰዎችን እንደ ማንጠርያ የእቶን እሳት ፣አንዳንድ ሰዎችን እንደ መግረፊያ አለንጋ (ጅራፍ) እና እንደ መቅጫ ዱላ የሚጠቀማቸው ሰዎች አሉ። እግዚአብሔር ልትቀረጹ ልትመከሩ ልትማሩ የምትችሉባቸውን መንገዶች ያዘጋጃል።እርሱስ ቢሆን “ምንም ልጅ ቢሆን፥ ከተቀበለው መከራ መታዘዝን ተማረ፤” አይደለምን ? (ዕብራውያን 5፥8)

ታዲያ መንገዱ በመከራም ቢሆን ዛሬ ላለህበት ያበቁህ ባለውለታዎችህ አይደሉም¡ እንዴ ? ናቸው እንጂ ።

በፍጻሜ ግብህ
በጸጋው የምትጎናጸፈው ድል ነው
በክብር የምትጎናጸፈው ጽናት ነው
የምትጎናጸፈው መንፈሳዊ ብቃት ነው
በምስጋና በተራሮች አናት ላይ ትሆናለህ