Get Mystery Box with random crypto!

እንኳን ለጌታችንና ለመድኃኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በአል መታሰቢያ በሰላም አደረሳችሁ ! | የእግዚአብሔር ቃል በሙላት ይኑርባችሁ (pastor Alemayehu Abebe )

እንኳን ለጌታችንና ለመድኃኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በአል መታሰቢያ በሰላም አደረሳችሁ !

ጌታ የተወለደበትን ዓላማ በመረዳት በዓሉን ማክበር ይሁንላችሁ ! (ሉቃስ 2:-8-14)

የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል ሲታሰብ ከመብልና በመጠጥ፣ የመልካም ምኞት መግለጫ ካርድ ከመለዋወጥ፣ በዘፈን እና በስካር የመታሰቢያ በዓሉን ከማሳለፍ ይልቅ የበዓሉን መልዕክት የእግዚአብሔርን አላማ እና እቅድ መረዳት ሰው በምድር እንዲኖር በተሰጠው ዘመን አገኘሁት ከሚላቸው ውድ ነገሮች ይልቅ መለኮት በሕይወቱ ያለውን የከበረ የደህንነት ዓላማ እንዲረዳ ያስችለዋል።

ዓላማውን የሳተ ለኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በአል መታሰቢያ አከባበር እግዚአብሔርን ደስ አያሰኘውም! በአሉ ትርጉም የሚኖረው ጌታ የተወለደበትን የማዳኑ ዓላማ በመረዳት ታላቁን የወንጌል ተልዕኮ በማወጅ ጌታ ወደምር የመጣበትን የማዳን ዓላማ በማከናወን ነው። እግዚእብሔር ሰውን ከዘላለም ጥፋት ለማዳን ያለው እቅድ እና ዓላማው የወንጌሉ የምስራች ሚስጥር ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስን ለመዳናችን አሳልፎ መስጠቱ ነው ::ስለዚህ እባካችሁን የተወለደበትን ዓላማ ለሰዎች በማወጅ ልደቱን እናክብር።

ስለዚህ ይህ የልደት በዓል በማክበር ብቻ የሚታለፍ አንድ ተራ ታሪካዊ ድርጊት አይደለም :: ይህ ወቅት በሰው ልጆች ታሪክ ውስጥ ከመሆኑም በፊት ያልነበረ ከሆነም በኃላ ያልተደገመ የአስደናቂ መለኮታዊ እቅድ ክንዋኔ ነው:: የሰው ልጅ በኃጢያቱ ምክንያት የሞቱን መርዶ በሕግ ተረድቶ ፣ በሐይማኖት ስርአት ተተብትቦ ፣ በሕግ በአድርግ አታድርግ ተወጥሮ ፣ፍርዱን ሲጠባበቅ፣ የእግዚአብሔር ድምፅ ለራቀው፣ በዲያቢሎስ እስራት ሲሰቃይ ለኖረው ፣ሰው ሁሉ ያለበትን ሁኔታ ጠልቶ ሰላም በጥማት በተፈለገበትና አዳኝ በታላቅ ጉጉት በተጠበቀበት አዳኙ ጌታ ተወለደ !(ሉቃ 2:10) የጌታ መልአክ በታላቅ ብረሀን ታጅቦ ተገለጠ ለህዝብ ሁሉ የሚሆን ታላቅ የምስራች አወጀ የምስራቹም " ዛሬ ... መድኃኒት እርሱም ክርስቶስ ጌታ የሆነ ተወልዶላችኋልና።" የሚል ነው(ሉቃ 2:11)

" አማኑኤል " እግዚአብሔር ከሰው ጋር ሰውም ከእግዚአብሔር ጋር ሆነ ! (የዮሐንስ 1:1)
እግዚአብሔር የሆነው ቃል ሥጋ ሆነ ጸጋንና እውነትንም ተመልቶ በእኛ አደረ (ዮሐንስ 1:14) ስለዚህ ታላቅ ደስታ የተባለው የምሥራቹ ነው ! በስጋ የተገለጠው ኢየሱስ ክርስቶስ ፍፁም ሰው ፍፁም አምላክ መሆኑ ነው (ማቴ 1:21) ይህ እግዚአብሔር በልጁ የገለጠው በፀጋ የሆነ ፅድቅ የሰው ልጅ ኃጢያት የሚያስተሰርይ ነፃ የሚወጣበት ከዘላለም ፍርድ የሚያመልጥበት ከሰይጣን እስራት የሚፈታበት ከድቅድቅ ጨለማ ወደሚደነቅ ብረሀን የሚሻገርበት ወደ ፍቅሩ ልጅ መንግስት የሚፈልስበት አስደናቂ የእግዚአብሔር የማዳኑ ጸጋ ነው ። (2ኛ ቆሮ 5:21)

ጌታ በተወለደበት ወቅት ልዪነት ነበር ! በአይሁድና በአህዛብ መካከል በእግዚአብሔርና በሰው ልጆች መካከል በባርያና በጌታ መካከል ልዪነት ጥል ነበረ :: (ኤፌሶን 2:-14 -16) ነገር ግን የሰላሙ አለቃ ኢየሱስ ተወለደ በመካከል ያለውን የጥል ግርግዳ በስጋው አፈረሰ ። ልዩነትንና ጥልን በመስቀል ገደለና አንድ አዲስ ሰውን ፈጠረ ::“ስለዚህ ማንም በክርስቶስ ቢሆን አዲስ ፍጥረት ነው፤ አሮጌው ነገር አልፎአል፤ እነሆ፥ ሁሉም አዲስ ሆኖአል።”
(2ኛ ቆሮ 5፥17)

ስለዚህ አሮጌው ነገር አለፈ ፣ ሁሉም አዲስ ሆነ ፣ ልዩነት ተወግዷል፣ ዛሬ ሰዎች በብሔር፣ በቋንቋ ፣ በዘር ልዩነቶችን እየገነቡ ያሉት ልዩነትና ጥል ጌታ በመስቀሉ የገደለውን ነው:: ጌታ ገድሎ የቀበረውን ልዩነት እና ጥል ከመቃብር ቀስቅሰው ሕይወት ሊዘሩበት ይታገላሉ። ይህ ልዩነት እርስ በርስ የሚያጠፋፋ መርዝ ነው ! ጥላቻን መናናቅን ክፋትና አመፃን የሚዘራ ነው ::

ኢየሱስ የሰላም ዓለቃ ነው !(ት. ኢሳ 9:-6) ስለዚህም ነው ይህንን ያየው ስመዖን የእስራኤልን መፅናናት የንጉስንም መወለድ ሳያይ እንማይሞት በመንፈስ ቅዱስ ተረድቶ ነበር :: ከዚያ ከማርያም ተቀብሎ አቅፎ አቤቱ አይኔ ይህንን ማዳንህን የአዳኙን መወለድ ካየች እኔን ባርያህን በሰላም አሰናብተኝ አለ :: ፈቃዴ መሻቴ ናፍቆቴ ፍላጎቴ ተፈፅሞአል አለ::የሩቅ ምስራቀቅ ጠቢባንም እንዲሁ ብዙ ማይልስ አቋርጠው " የተወለደው የአይሁድ ንጉስ ወዴት ነው ?" እያሉ ወርቃቸውን ከርቤያቸውን እጣኖቻቸውን በግመሎቻቸው ጭነው ሲፈልጉት የምናየው ለዚሁ ነው ::

ለምን ፈለጉት ? የርሱ ንጉሳዊ አስተዳደር ዓለም ላለችበት ችግርና እንቆቅልሽ ሁሉ መፍትሔ ነው :: ምክንያቱም እርሱ የሠላም ንጉስ ነው ! የፍቅር ንጉስ ነው ! ለመንግስቱ ሕግ ሳይሆን የሰው ልጅ እንዳይሞት የራሱን ሕይወትስ እንኳ በወንጀለኛው ፋንታ የሚያኖር ንጉስና አዳኝ ነው :: እርሱ የማይፈታው ቋጠሮ የማይመልሰው ጥያቄ የማይፈውሰው ቁስል የለም ::

የጠቢባኑ ጥያቄ ግራ የሚያጋባ ነው ! ሕዝቡ ከሚያውቁት ንጉስ ሌላ ከየት መጣ ? ኧረ መጥቷል ሰው የተወለደበትን ቦታ አቅጣጫ ባይረዳ ኮከቡ በመለኮት ትዕዛዝ ሊመራ ወጥቷል::እነርሱም በኮከቡ ተመርተው ባገኙት ጊዜ
ተንበርክከው ሰገዱለት :: የያዙትን እጅ መንሻ ሰጡት ይህ ደግሞ ተቀናቃኙ ለግድያ እየፈለገው ስለሆነ ለማርያምና ለዮሴፍ የግብፅ ስደት በቂ የመለኮት አቅርቦት ነው :: የተወለደው የአይሁድ ንጉስ ወዴት ነው ? ዛሬም እርሱ ለሰው ልጆች ሁሉ ያስፈልጋል :: በኃጢያትና በአጋንንት እስራት ፍርዱን ለሚጠባበቅው በሞት ፍረሀት ለሚኖረው የሰው ልጅ ሁሉ ኢየሱስ የመዳኛ መንገድ ነው ! የሽግግር ጌታ ከሞት ወደ ህይወት ያሻግራል ! ታዲያ ይህ ንጉስ አያስፈልግምን ? አፍ ባይናገርም የሰው ልጅ የውስጥ ማንነት የዘወትር ጩኸት ነው ! (መዝ 42:2) የውስጥ ጩኸት ናፍቆትና የዘወትር ጥማት ከተናፋቂው ሌላ ነገር ቢቀርብ እርካታ አይሆንም ሰላም አይሰጥም አያሳርፍም ::

ብዙዎች ለዚህ የውጥ ጩኸት ሌላ ብዙ ምላሽ ቢሰጡም ጩኸቱ ዛሬም አላቆመም ንጉሱ ካልተገኘ ሕይወት ኑሮ ትርጉም አልባ ነው :: ሰላም እና እረፍት አይታሰብም። ዛሬ እንደ ጠቢባኑ ብዙ ማይልስ ማቋረጥ አይጠበቅብንም :: ንጉሱ በስፍራ አይወሰንም ዛሬ እንደ ገሊላ ሴቶች እርሱን ፍለጋ ወደ ሙታን መንደር መሮጥ አያስፈልገንም ::(ሉቃስ 45:-5) ኑ ወደ ንጉሱ ! ሠላማችሁ እንደ ወንዝ ይሆናል :: እረፍታችሁ ይበዛል :: የተጫናችሁ የኃጢያት ሸክም ይራገፋል ::በዚህም በምድር ከሞት በኃላ ሊመጣ ባለው ዓለም ድናችሁ ትቀራላችሁ !“ፊልጶስ ናትናኤልን አግኝቶ፦ ሙሴ በሕግ ነቢያትም ስለ እርሱ የጻፉትን የዮሴፍን ልጅ የናዝሬቱን ኢየሱስን አግኝተነዋል አለው።”(ዮሐንስ 1፥46) ጌታን ማግኘት እና ድኖ መቅረት ይሁንላችሁ ! ተባርካችኃል!