Get Mystery Box with random crypto!

ከሰማይ የተገለጠው የወንጌል እውነት ለሚበርዝ ወዮለት ! “ይህም ወንጌል በሥጋ ከዳዊት ዘር ስለ | የእግዚአብሔር ቃል በሙላት ይኑርባችሁ (pastor Alemayehu Abebe )

ከሰማይ የተገለጠው የወንጌል እውነት ለሚበርዝ ወዮለት !

“ይህም ወንጌል በሥጋ ከዳዊት ዘር ስለ ተወለደ እንደ ቅድስና መንፈስ ግን ከሙታን መነሣት የተነሣ በኃይል የእግዚአብሔር ልጅ ሆኖ ስለ ተገለጠ ስለ ልጁ ነው፤ እርሱም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።”
— ሮሜ 1፥3-4
በዘመናት መካከል ይህንን የወንጌል እውነት ለመሸቃቀጥ የተነሱ ጥቂቶች አይደሉም ። ወንጌል ምንድነው ? በወንጌልስ የሚሰበከው ማነው ? ወንጌል በኃይል የእግዚአብሔር ልጅ ሆኖ ስለ ተገለጠ ስለ ልጁ ነው፤ እርሱም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። የሚለው እውነት ለዘላለም የታመነ ነው ።

ሐዋርያው የያዘውን የወንጌል እውነት እንዲሸቃቅጥ የሚስሩ እጅግ ብዙ ነበሩ እርሱ ግን እንዲህ አለ :-“የወንጌልም እውነት በእናንተ ዘንድ ጸንቶ እንዲኖር ለአንድ ሰዓት እንኳ ለቅቀን አልተገዛንላቸውም።”
— ገላትያ 2፥5
እውነተኛ አገልጋይ የወንጌል እውነት ጸንቶ እና ተጠብቆ እንዲኖርም ጭምር ይተጋል።

ሐዋርያው የወንጌልን እውነት ሲበርዙ የሌለውን ያልተላኩትን ወንጌል የሚሰብኩትን ጨምሮ በእርግማን አውግዞአል። በቤተክርስቲያን አዕማድ የተባለውን ፣ የበጎች እረኛ እና ጠባቂነት የመጋቢነት ኃላፊነት እና ሹመት የተሰጠውን ኬፋን /ጴጥሮስን/ ከወንጌል እውነት ተጣሞ ሲያገኘው ፊት ለፊት ተቃወምኩት አለ ።“ነገር ግን ኬፋ ወደ አንጾኪያ በመጣ ጊዜ ፊት ለፊት ተቃወምሁት፥ ይፈረድበት ዘንድ ይገባ ነበርና።”አለ
— ገላትያ 2፥11

የወንጌል እውነት ተጠብቆ እንዲኖር ዋነኞች መስለው ሊታዩ የሚወዱትን መገሰጽ ይገባል ። ስህተታቸውንም አጋልጦ በማረም ሕዝብን ከጥፋት መታደግ ይገባል።የወንጌል እውነት ኢየሱስ ክርስቶስ ነው ። ይህንን አውነት ጥለው በርሱ ቦታ ሌላ ተተክቶ የማያድን የሐሰተ ወንጌል ያቆሙ በእግዚአብሔር ፊት ስላደረጉት ሁሉ ከፍርድ አያመልጡም ። የወንጌል እውነት ያጣመሙ ተጣሞ እንዲጻፍ ያደረጉ የሰበኩትም ጭምር የተረገሙ ናቸው።

"ነገር ግን እኛ ብንሆን ወይም ከሰማይ መልአክ፥ ከሰበክንላችሁ ወንጌል የሚለይ ወንጌልን ቢሰብክላችሁ፥ የተረገመ ይሁን። አስቀድመን እንዳልን እንዲሁ አሁን ሁለተኛ እላለሁ፥ ከተቀበላችሁት የተለየውን ማንም ቢሰብክላችሁ የተረገመ ይሁን።"(ገላትያ 1:-8-9)

ሐዋርያው ጳውሎስ የወንጌል እውነት ተጠብቆ እንዲኖር ሊያጣምሙ የሚሯሯጡትን ከመገሰጽም አልፎ ከተሰበከው ከኢየሱስ ክርስቶስ ውጪ ሌላ ወንጌል እንደሌለ አስረግጦ እየተናገረ ከተሰበከው ውጪ የሚሰብክ የተረገመ ይሁን አለ። ዛሬም ወንጌል ተጣሞ እያዩ ዝም ያሉ ፣ሐሰተኛ ወንጌል የሰበኩ ፣የወንጌልን እውነት አጣመው በመሸቃቀጥ ትውለድን ያሳቱ ፣ሐሰት ተተክቶ እንዲሰበክ ያደረጉ ከተጠያቂነት አያመልጡም። እግዚአብሔር የሰው ልጅ እንዲድንበት የገለጠውን ልጁን ኢየሱስ ክርስቶስን በመስበክ ፋንታ ትውልደ ትውልድ እንዲጠፋ የተሸቃቀጠ የተበረዘ ወንጌል አስቀምጠዋልና።

እውነተኛውን ወንጌል ኢየሱስን በመስበክ እግዚአብሔርን ከመስደሰት ይልቅ ጣዖት ተክለው ለሰው ደስታ ኖረዋልና ታላቅ ፍርድ ይጠብቃቸዋል ።
“ሰውን ወይስ እግዚአብሔርን አሁን እሺ አሰኛለሁን? ወይም ሰውን ደስ ላሰኝ እፈልጋለሁን? አሁን ሰውን ደስ ባሰኝ የክርስቶስ ባሪያ ባልሆንሁም።”
— ገላትያ 1፥10

የወንጌል እውነት በብሉይ የተተነበየለት ፣ በወንጌል የተገለጠ ፣ በሐዋርያት የተሰበከለት ፣ በመልዕክቶች የተብራራ ፣ በራዕይ በክብር የተገለጠ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው ። ከርሱ ውጪ የሚሰብክ የሚጽፍ እግዚአብሔር የገለጠውን የመዳን እውነት የሚያዳፍን የተረገመ ነው።