Get Mystery Box with random crypto!

መንገድ ክፍል 1 (በእውቀቱ ስዩም) በደናው ቀን ብርቱ ነበርሁ፤ ባንድ እጄ ፑሽአፕ እየሰራሁ | Alex Abreham በነገራችን - ላይ

መንገድ
ክፍል 1
(በእውቀቱ ስዩም)

በደናው ቀን ብርቱ ነበርሁ፤ ባንድ እጄ ፑሽአፕ እየሰራሁ በሌላው እጄ ጢሜን እላጭ ነበር፤ አሁን አንድ ኪሎ ሜትር ከተራመድሁ ይደክመኛል፤ ትናንት ከቤት ወጥቸ የቀበናን መንገድ ትንሽ ወረድኩና እንግሊዝ ኢምባሲ የተከለውን የስልክ እንጨት ተደግፌ እፍወይይይይ ብየ ተነፈስሁ፤ እፎይይ ስል ከሆዴ መለስተኛ አውሎ ነፋስ ወጣ! መንገድ ዳር በቆሎ ጠብሰው የሚሸጡ ሴቶች ባተነፋፈሴ ተደንቀው ዞር ዞር ያሉ አዩኝ “ አሁን የተነፈስከውን ባግባቡ ብትጠቀምበት አምስት ምድጃ ያቀጣጥላል” የሚሉኝ መሰለኝ ፤
የቀረውን መንገድ በመኪና ለመመለስ ፈለግሁ፤ ግድ ካልሆነ በቀር ራይድ አልጠራም፤ ቀን ጥሏቸው መንገድ ዳር የቆሙ ላዳዎችን እጠቀማለሁ፤ ይቺ ላዳ አሮጌ ናት፤ ፍሬቻዋ ስለተሰረቀ ፋኖስ ተገጥሞላታል፤ የላዳውን በር ልከፍተው ሞከርኩ፤ እምቢ አለኝ ፤ ሰውየው ከውስጥ ሆኖ ሊያግዘኝ ተፍጨረጨረ ፤ በመጨረሻ ወጣና ለሁለት መታገል ጀመርን፤ ከእልህና እህል አስጨራሽ ትግል በሁዋላ የላዳው ጋቢና በር እንደ ድስት ግጣም ተነሳ! ገባሁና ከሁዋላ ተቀመጥሁ፤ ሾፌሩ የሳይክል እግር የሚያክለውን መሪ እንደ በረኛ ተጠምጥሞበት ጉዙ ጀመርን፤
ከጎኔ ያለውን ሳተራምስ ከቆየሁ በሁዋላ “ ቀበቶ የለም እንዴ?” ስል ጠየኩት
“ ቀበቶ ተበላሽቷል! ሰንሰለቱን ብትጠቀም ይደብርሀል?”
እንደ ባህታዊ ሰንለቱን ታጥቄ ጉዞ ጀመርን፤
“ የማንን ሙዚቃ ላድርግልህ? “
“ የሙሉቀን መለሰ ይኖራል?”
“ አይጠፋም “ አለና ፤ ከእግሩ ስር ዳንቴል ለብሶ የተጋደመውን ቴፕ ቆስቁሶ ጥላሁን ገሰሰን ከፈተልኝ ፤
“የዘንባባ ማር ነው ፍቅርሽ
ቄጤማ ይመስላል ጸጉርሽ”
“ የዘንባባ ማር የሚባል ነገር ግን አለ?” የሚል ጥያቄ አነሳሁ፤
“ ፍቅር አይያዝህ ወንድሜ” አለ ሾፌሩ” ፍቅር ከያዘህ አይደለም የዘንባባ ማር ፤ የግራዋ ወተት ሊታይህ ይችላል” አለኝ ሾፌሩ
እንዲህ እያወጋን ስንሄድ የትራፊክ ፖሊስ ነፍቶ አስቆመን፤
“ ጥፋቴ ምንድነው?”
“ ወድያ ያለውን መብራት ጥሰህ መጥተኻል”
ሰውየው በናቱ በአባቱ በመላእክቱ እና በህብረተሰቡ ምሎ ሸመጠጠ፤
ለሀያ ደቂቃ ከተከራከሩ በሁዋላ ሾፌሩ “ የዛሬን አስተምረህ ልቀቀኝ “ ሲል ሰማሁት፤
“ አስተምሬ ብቀጣህ እመርጣለሁ” አለ ፖሊሱ ቅጣቱን ፈርሞ አቀበለው ፤ ከዚያ ሌላ ህግ የሚጥስ መኪና ፍለጋ በጉጉት ማማተር ጀመረ፤
ሾፌሩ የተሰጠውን ደረሰኝ ዳጎስ ባለ የቅጣት መዝገቡ ውስጥ ከወሸቀ በሁዋላ ፖሊሱ ወደ ቆመበት አቅጣጫ እየተመለከተ
በሚጢጢ ድምጽ “ እስቱቢድ” ብሎ ተሳደበ፤ በሆዱ ቢሳደብ ራሱ ከዚህ የተሻለ ሳይሰማ አይቀርም፤