Get Mystery Box with random crypto!

#ሰው_ባለው_ነው.....' Mengistu M Tsion ሰንበት ማለዳ ላይ ረፈድ አድርጌ ብነሳም | Alex Abreham በነገራችን - ላይ

#ሰው_ባለው_ነው....."
Mengistu M Tsion


ሰንበት ማለዳ ላይ ረፈድ አድርጌ ብነሳም በእንግድነት መጥቶ ከኔ ቤት ሶፋ ወንበር ላይ የተኛው ባልንጀራዬ ግን አሁንም አልነቃም ነበር። ማታ የጠጣቸው ባዶ የቢራ ቆርቆሮዎች ጠረጴዛውን ሞልተውታል። የአሜሪከን ባንዲራ ቀለም ያለበት ትልቅ ላይተርና American Spirit የሚባል ቢጫ ቀለም ያለው የትንባሆ ፓኬት ደግሞ ከጠረጴዛው ስር ወድቋል። መጋረጃውን ወደ አንድ ጎን ሰብስቤ የሳሎኑን መስኮት ከፈትኩት። ብሩህ ሞቃት ማለዳ! ገና ከጠዋቱ አራት ሰዓት እንኳ ሳይሆን ሙቀቱ ፊት ይጋረፋል! ተዘግቶ ያደረው ክፍል ይንፈስበት ብዬ እንጂ የቤቱን ውስጥ ቅዝቃዜ ለመጠበቅ መስኮትም ሆነ በር የግድ መዘጋት ነበረበት።

የተጋደመውን ወዳጄን ገልመጥ አድርጌው
"አንተ አትነሳም እንዴ?" እያልኩ ወደጄን በድምፄ ትልቁን ቲቪ ደሞ በርቀት መቆጣጠሪያው ከእንቅልፋቸው አባነንኳቸው። ባልንጀራዬ አፋሽኮ ተገላብጦ ተመልሶ ቢተኛም የቀሰቀስኩት ቲቪ ግን ብቻውን ያወራ ጀመር። ስለሃገሬ "ተስፋ ቢስ" ወሬ የምቃርመው አልያም ፈገግ የሚያሰኙኝን የቪዲዮ ክሊፖች መልከት የማደርገው ሰንበት ማለዳ ላይ ነው። ታዲያ ዛሬም አንዲት የfb ወዳጄ "ተመልከታቸው!" ስትል ከላከችልኝ ሁለት ሊንኮች አንዱን ተጭኜ ከፈትኩት። ይህች የfb ወደጄ በጣም ካላስገረማት፣ ወይ ካላሳቃት፣ ወይ ካላስደነቃት በቀር መልዕክቶቿን ወደ እኔ ስለማትልካቸው ብዙ ግዜ የምትልካቸውን ተመልክቼያቸዋለሁ።

የቪዲዮ ምስሉ የሚያሳየው በቲቪ ተከታታይ ድራማ ላይ የሚታወቀውን ንብረት ገላውን (እከ) ቃለ ምልልስ ነበር። እከ ልክ ድራማው ላይ እንዳለው የዋህ ነው ለካ! አወራሩ ምስኪን ባላገር ፣ አቀራረቡ ቀጥተኛ፣ ካንደበቱ በሚወጡት ገራገር ቃላት የተነሳ ደግሞ የነብሱን ቅንነት ማየት ይቻላል። "ካፍ የሚወጣ ከልብ ይወጣል" አይደለ የሚል መፅሀፉ! ድንግጥ ብዬ ፍንድት እስክል የሳቅኩት "ባንድ አረፍተ ነገር ለምን አልገላገለውም" ሲል አስቦ ይመስለኛል "ዘማዊ አርቲስት ነበርኩ በቃ" ሲል ነው። ያኔ ነበር በረጅም ሳቄ የተነሳ ከእንቅልፉ የተነሳው ባልንጀራዬ ክንብንቡን ገልጦ አይኖቹን እያሻሸ
"ምን እያየህ ነው ?" ያለኝ
"ታሪክህን" አልኩት ይህው በእንስት ጉዳይ የማይታማውን ወዳጄን። መልስ አልሰጠኝም። ቆይቶ
"ስንት ሰዓት ነው አለኝ?" እከ ላይ ተመስጬ ስለነበር አልመለስኩለትም። ተከናነበና ተመልሶ ተኛ!

እከ የዋህ ልበለው ጂል ግራ እንደገባኝ ቃለ ምልልሱ ሳይሆን "የንሰሀ" ፕሮግራሙ አለቀ። በዚህ ክፉ ግዜና የተበላና የተጠጣው ሳይቀር በማህበራዊ ሚዲያ ላይ በሚከርምበት ዘመን ራስን እንዲህ አጋልጦ ፣ ድካምና ገመናን አደባባይ ማስጣት ለምን እንደፈለገው አልገባኝም። የርሱስ ዘመዶች፣ የሚስትስ ቤተሰቦችና ባልንጀሮች ላይ የሚያደርሰው አሉታዊ ተፅእኖው የከፋ አይሆንም ወይ?? በርግጥ ሁላችንም ትንሽ ትንሽ "እከ" ነን። ሆኖም አንዳንድ ነገር ደሞ ከመገለጡ ይልቅ መሸፈኑ ነው ይበልጥ አስተማሪነቱ።
"ከኔ ተማሩ! ከትዳር በፊት አትቅበጡ" በሚል ያደባባይ ንሰሀውን ያጠናቀቀውን "እከ" ን ትቼ "ይህን የእርሱን ፕሮግራም ካየች በኋላ ቢሆን ኖሮ እስከ ጋብቻዋ በድንግልና ትፀና ነበር" እያልኩ እየቀለድኩ "ካለብኝ የወሲብ ሱስ የተነሳ ሃምሳ የሚበልጡ ወንዶችን በተከታታይ አውጥቻለሁ። ግን ቅምም አላለኝ። ምን ላድርግ? እርዳታ ፈልጋለሁ" ወደምትል ሃያዎቹ መጀመሪያ ላይ ወደምትገኝ ሌላኛይቱ ተናዛዥ ታሪክ መመልከት ተሸጋገርኩ። ልጅቱ መልኳ ባይታይም የሚያማልል ድምፅ ያላት ወጣት ነበረች። ታሪኳ የውሸት ይሆን እንዴ ስል በጥርጣሬ የሰማኋት ቢሆንም ከታሪኩ consistency እንዲሁም ከምትናገርበት ጥልቅ ስሜት ድምፀት የተነሳ ጥርጣሬዬን ለማስወገድ ተገድጄ ነበር። ልጅቱ ልትተው በምትፈልገው ግን ባልቻለችው ክፉ የዝሙት ሱስ ሰንሰለት ተጠፍንጋ ስትሰቃይ ላደመጣት ታሳዝናለች።
"በነጠላ ጫማ ባንቺ አረማመድ
እንዴት አለቀልሽ ያሁሉ መንገድ" እንደሚለው ዘፈን ሁሉ ባንድ ሰሞን ብቻ ሃምሳ ኮርማ አስተናግዶ ቅም ያላለው የወሲብ ዛሯን ከልጅነቷ ጋር አነፃፅሬ
በውስጤ " ሰው ብርቱ......." ብየለሁ።

የዚህችን ወጣት ታሪክ ተገርሜ እያደመጥኩና እየተመለከትኩ በነበረበት ወቅት ተኝቷል ብዬ የነበረው ባልንጀራዬ ለካስ ነቅቶ ኖሮ ክንብንቡን ገለጥ አድርጎ አብሮኝ ሲከታተል ነበርና ፕሮግራሙ ሲያልቅ
"ስልኳን አላስቀመጠችም እንዴ?" አለኝ
ንቅት ብሎ ጥርት ባለ ድምፅ!
"ለምን ፈለከው?" አልኩት አትኩሬ እያየሁት።
"እርዱኝ! እርዳታ ፈልጋለሁ ስትል አልሰማሃትም እንዴ? ዛሬ አይደል እንዴ ሃገር ቤት የምበረው?" አለኝና በረዥሙ አፋሸከ።
"እሺ ኮርማው! በምን ልትረዳት ነው?" አልኩት የግርምት ሳቅ እየሳቅኩ
"ያው ሰው ባለው አይደል የሚሰለፈው!? በምችለው አቅም ልረዳት ነው። እህታችን እኮ ነች" አለኝና ወደ መታጠቢያ ቤት ለመሄድ ከሶፋው ላይ ተነሳ!
ከ...................ት ብዬ እየሳቅኩ ቁርስ ላዘጋጅ ተነሳሁ!

ብያለሁ እኮ ትንሽ ትንሽ ሁላችንም "እከ" ነን።

Mengistu M Tsion