Get Mystery Box with random crypto!

#ፉዣዥ ባለፈው እኮ ነው። ፉዣዥ የጠፋለት። ተቅበዝብዤ በሌላ ፕሮፋይል ስፅፍ ነበር። አንደኛው | Alex Abreham በነገራችን - ላይ

#ፉዣዥ

ባለፈው እኮ ነው። ፉዣዥ የጠፋለት። ተቅበዝብዤ በሌላ ፕሮፋይል ስፅፍ ነበር። አንደኛው የፃፍኩት ከታች ያለው ነው።
*
“እግዚአብሄር ቬጂተሪያንን (ስጋ ጠሎችን) ይጠላል” አለኝ አንድ ወዳጄ። ስጋ ቤት ምሳ እየበላን።

“እረ ባክህ” አልኩት በመገረም።

“የገረመህ ይመስላል”

“እንዴታ። እንዴት አይገርመኝ። መዳፌን አፌ ላይ መጫን ብቻ እኮ ነው የቀረኝ። ባለሁበት ደርቄ እያየኸኝ። ምን ጥያቄ አለው? ገርሞኛል እንጂ”

“ለምን ገረመህ?”

“ያልጠበቅኩት ነገር ነዋ”

“ምኑን ነው ያልጠበቅከው?”

“እግዚአብሄር ስጋ ጠሎችን (ቬጂተሪያኖችን) እንደሚጠላ”

“ማንን የሚጠላ ነበር የሚመስልህ?”

“እኛን ነዋ። ስጋ አፍቃሪዎችን”

“እኛንማ ይወደናል”

“እንዴት ይወደናል? ህይወት እያጠፋን እንዴት ይወደናል?”

“የአቤል እና የቃየንን ታሪክ ታውቀዋለህ መቼም?”

“እንዳንተ ባይሆንም በጥቂቱ”

“ምን ታውቃለህ? እስኪ ንገረኝ”

“ቃየን ታላቅና አርሶ አደር እንደነበር። አቤል ታናሽና አርብቶአደር እንደነበር አውቃለሁ። በተጨማሪም ቃየን ታናሽ ወንድሙን አቤልን እንደገደለው”

“ለምን ገደለው?”

“በቅናት ተነሳስቶ”

“ምን አስቀናው?”

“እግዚአብሄር የአቤልን መስዋእት ወዶ የእርሱን ግን ስላልተመለከተለት”

“አቤል ምን መስዋእት አቅርቦ ነው?”

“ከመንጋዎቹ ውስጥ መጀመሪያ የተወለዱትንና የሰቡትን”

“ቃየንስ ምን አቀረበ?”

“ቃየንማ አርሶ አደር ስለነበር ገብስና በቆሎ ድንችና ዳጉሳ ይሆናላ”

“ታዲያ እግዚአብሄር ምን አለ”

“እግዚአብሄር የአቤልን ስጦታ ወደደው”

“የቃየንስ?”

“የቃየንንማ እንኳን ሊወደው አልተመለከተውም ነበር”

“ታዲያ ከዚህ በላይ ምን ትፈልጋለህ። እግዚአብሄር ስጋ ተመጋቢዎችን ይወዳል”

ጥርግ አድርገን በላን። እግዚአብሄር እንደሚወደን እያሰብን በደስታ ተመገብን። ቬጂተሪያኖች እንዳይነሱብን ብቻ። ከተነሱብንም እንደ ቃየን በምድረበዳ መቅበዝበዛቸው ነው።

አንድ ነገር ግን ከነከነኝ። አቤል ከብት አርቢ ነበር፥ ቃየን ግን አርሶ አደር። ይህ ማለት አቤል ስጋ ብቻ ተመጋቢ ነበር ማለት ነው?

ቃየን ስጋ አይበላም ነበር ማለት ነው?

አቤል እና ቃየን አይገበያዩም ነበር ማለት ነው?

ደወልኩ ወዳጄ ጋር። በስንት ጥረት አገኘሁት። የከነከነኝን ጥያቄ አነሳሁለት።

“አንተ ደግሞ ቀልድ አታውቅም” አለኝ።

“ምን አይነት ቀልድ ነው? ሲሪየስ በሆነ ጉዳይ ትቀልዳለህ እንዴ?”

“ምን ተጎዳህ። በደስታ ጥርግ አድርገህ በላህ አይደል”

“እርሱማ ልክ ነህ”

“አንተም እንዴት እንደ ቃየን ትሆናለህ”

“እንደ ቃየንማ አልሆንኩም፤ እንደ አቤል እንጂ”

“ምኑን እንደ አቤል ሆንክ? እንደ ቃየን እንጂ። የአቤልን መስዋእት እግዚአብሄር ወዶታል፥ የኔን አልወደደውም ብሎ ያመነው፥ የደመደመው እራሱ ቃየን ነው። እግዚአብሄር ይሄንን ይውደድ፥ ያንን ይጥላ፤ በምን አይቶ ነው ያመነውን ያመነው? እግዚአብሄርን የኔን አልተመለከተውም ብሎ ያመነው በምን አይቶ ነው? እግዚአብሄር የማይመለከተው ነገር አለ እንዴ? በእግዚአብሄር ዘንድ እኮ ክፉ እና መልካም የሚባል የለም። ሁሉም አንድ ነው። ክፉና መልካምን የፈጠሩት የቃየን እናትና አባት ናቸው። እንደ እግዚአብሄር ተፈጥረው እያለ "እንደ አንዱ" ብቻ የሆኑትና ይሄን መልካም ያንን ክፉ እያሉ መመደብ የጀመሩት፤ እናትና አባቱ ናቸው። ሁሉ ገንዘቡ የሆነው እግዚአብሄር፤ አንዱን ወዶ ሌላውን አይጠላም”

“የእነ አቤል እና ቃየን ታሪክ ጉዳይ ታዲያ ምንድር ነው?”

“ታሪኩማ ሁለት አካላት ለእግዚአብሄር ስላቀረቡት መስዋእት ነው”

“ምንድር ነው የምታወራው ሰውየ? ምን ታወናብደኛለህ?”

“እንግዲህ ከዚህ በላይ ምንም ማለት አልችልም። ሳምንት ቅዳሜ እስክንገናኝ ድረስ አዲዮስ”

ዘጋው። ስልኩን ዘጋብኝ።

“ጆሮዬ ላይ ስልኩን ዘጋብኝ” ብዬ ለጋራ ወዳጃችን አማረርኩ።

“ምን ያናድድሃል? ከሁለት አንደኛው ሌላኛው ጆሮ ላይ ስልኩን ሳይዘጋ የሚጠናቀቅ የስልክ ምልልስ አይቼ አላውቅም” አለኝ።

ያሁኑ ይባስ።

ድጋሚ ደወልኩለት።

“ጥያቄዬን አልመለስክልኝም” አልኩት።

“ምኑን?”

“አቤል ከጠቦቶቹ ጥቂት ለቃየን ሰጥቶ ከቃየን ድንችና ዳጉሳ እንዲሁም ጤፍ አይገበይም ነበር? ገበያ አይታወቅም ነበር?”

“አንተ ደግሞ ስለ ገበያ ታወራለህ። አቤልና ቃየን እኮ ምድር ከተፈጠረች በኋላ፥ የሰው ልጅ ከተፈጠረ በኋላ የተወለዱ ናቸው። የመጀመሪያዎቹ ተወላጆች እኮ ናቸው። አንተ ስለ ገበያ ታወራለህ። ገበያ የተፈጠረው ገና ትናንት አይደለም እንዴ። አዳም ስሚዝ አይደለም እንዴ ስለ ገበያ ጥቅም የፃፈውና የሰውን ልጅ ስለ ነፃ ገበያ ጥቅም ያስተማረው”

ከቅድሙ “ያሁኑ ይባስ” ይልቅ የዚህኛው “ያሁኑ ይባስ” ባሰ።

“እሺ ይሁንልህ። አቤል የአዳም ልጅ አይደለም የሚባለውስ እውነት ነው?”

“ማነው ያለው?”

“አንዳንድ አስተማሪዎች እንደዛ ይላሉ”

“በምን አወቁ?”

“አዳም ሚስቱን ሄዋንን አወቀ ፀነሰችም፥ ቃየንን ወለደች ይላል መፅሃፉ። አቤል ከተገደለ በኋላም አዳም ሚስቱን ሄዋንን አወቀ ፀነሰችም፥ ሴትን ወደለች ይላል መፅሃፉ። ስለ አቤል አወላለድ ሲያወራ ግን ሄዋን አቤልን ወለደች ይላል እንጂ አቤል ከመወለዱ በፊት አዳም ሚስቱን ሄዋንን እንዳወቀና እንደፀነሰች ምንም የሚለው ነገር የለም። ከዚህ ተነስተው አቤል የአዳም ልጅ አይደለም ይላሉ” አልኩት።

“የማወቀው ነገር የለም። ያንተ የልደት ሰርተፊኬት ላይ አባትህ እና እናትህ ተገለፁ እንጂ አባትህ እናትህን እንዳወቃት ተፅፏል?” አለኝ።

“አልተፃፈም”

“ይህ ማለት አንተ ያባትህ ልጅ አይደለህም ማለት ነው?”

“ነኝ እንጂ”

“ታዲያ ምን ታደርቀኛለህ? የአቤልም እንደዛው ነው”

“ታዲያ የቃየን እና የሴት ሰርተፊኬት ላይ አዳም ሄዋንን እንዳወቃት ለምን ተፃፈ?” አልኩት።

“ሰርተፊኬቱ እንደወጣበት ቀበሌ ይለያያላ። አንዳንዶች ይፅፉታል ሌሎቹ አይፅፉትም። በቃ እንደዛ ውሰደው። ለመሆኑ ግን ሄዋን አቤልን ከአዳም ካልወለደችው ከማን ትወልደዋለች ተብሎ ተፈርቶ ነው? ከአትክልተኛው?”

“ምን አውቃለሁ?”

“በል አሁን ቻው ስራ አለብኝ። እንዳንተ ፀጉር የምሰነጥቅበት ትርፍ ጊዜ የለኝም” ብሎ ጆሮዬ ላይ ዘጋብኝ።

#ፉዣዥ