Get Mystery Box with random crypto!

እልል ያለ የፍቅር ታሪክ ! (በእውቀቱ ስዩም ) አማረችን እወዳታለሁ፤ እሷም ትወደኛለች ፍቅራች | Alex Abreham በነገራችን - ላይ

እልል ያለ የፍቅር ታሪክ !

(በእውቀቱ ስዩም )
አማረችን እወዳታለሁ፤ እሷም ትወደኛለች
ፍቅራችን የታይታ ሳይሆን የታይታኒክ ነው ፤
የዛን ቀን የተቀጣጠርንበት ቦታ ስደርስ፥
“ በጣም አስጠበቅኸኝ” አለችኝ
“ ትራፊክ ፖሊስ ይዞኝ ነው “ ብየ መለስኩላት፤
“ መኪና ሳይኖርህ ትራፊክ እንዴት ሊይዝህ ይችላል? “
“ከተፈቀደው ፍጥነት በላይ ሮጠሀል ብሎ ያዘኝ “
ቢራ አዘዝኩ፤
አማረች ፥ አማሩላ አዘዘች፤
ከውስጥ የሂሩት በቀለ ተወዳጅ ዜማ ይንቆረቆራል፤
“ እንደ መሽኮርመም ይላል ምነው
አፋር አይሉት ሶማሌ ነው “

ቀዝቃዛ ነፋስ መንፈስ ጀመረ፤
ሰማዩ ብልጭ አለ፤
ፊቷ ላይ አማተብኩላት፥
ሰማዩ ማጉረምረምና ማካፋት ጀመረ፤
የመብረቅ መከላከያ የተገጠመለት ጃንጥላየን ዘረጋሁ፤

“ በረደሽ ? “ ስል ጠየኳት፥

ጭንቅላቷን ባዎንታ ነቀነቀች፥
ካቦርቴን ምሽልቅ አድርጌ አወለቅሁና ኮሌታውን አስተካክየ መልሸ ለበስኩት፤

ከፊትለፊታችን የተንጣለለው የአበባ እርሻ የፍቅር ስሜቴን ቀሰቀሰው፤ በአበባ እርሻው ውስጥ ልዩ ልዩ ቀለም እና መአዛ ያላቸው ፌስታሎች ተበትነዋል፤

ከአበባ ርሻው አጠገብ የሚገማሸረው የግንፍሌ ወንዝ አካባቢውን የበለጠ ግርማ ሞገስ ሰጥቶታል፤ ወንዙ ከአቃቂ ወንዝ የተረከበውን የውሻ አስከሬን በመሸኘት ላይ ነበር፤
“የልጅነት ትዝታየ ተቀሰቀሰብኝ “ አልኳት፤

“ አባብልህ አስተኛው “ አለችኝ፤

“ በልጅነቴ አሳ እያጠመድሁ ቤተሰቤን እደግፍ ነበር “ በማለት ቀጠልኩ፤
“ በመረብ ወይስ በመንጠቆ?”

“ በወንጭፍ”

“ እንዴት ተደርጎ?”

“ ከሰፈራችን ብዙ ሳይርቅ አንድ ግዙፍ ዋርካ ነበር ፤ዋርካዋው ስር ጋደም እልና ማንጎራጎር እጀምራለሁ፤ ገዴ የተባለችው አሞራ እየበረረች ትመጣና ዛፉ ላይ ጉብ ብላ ታዳምጠኛለች፤ ለረጅም ጊዜ ስራ ፈትታ ስለምታደምጠኝ ይርባታል፤ ራቡ ሲጠናባት ከዛፉ አጠገብ ካለው ከሚገማሸረው ወንዝ ስር ከሚርመሰመሱ አሶች አንዱን ባፏ ይዛ ወደ ዛፉ ትመለሳለች፤ ወድያው ወንጭፌን አውጥቼ አነጣጥሬ እጥላታለሁ፤ አሳውን ለግብጽ ግምበኞች፥ ወፊቱን ለኩባ ወታደሮች እሸጣለሁ”

ጠጋ አለችኝና ትስመኝ ጀመር፤
አንባቢ ሆይ! ታሪኩን እዚህ ላይ ልጨርሰው አስቤ ነበር፤ ግን ደስታ በራቀው ዘመን በደስታ እሚጠናቀቅ ታሪክ መጻፍ አልፈቅድም፤

ለሁለት ሳአት ያክል ስትሰመኝ ከቆየች በሁዋላ፤ ከንፈሯን ከግንባሬ ላይ አንስታ፥
“መጀመርያ ስታገኘኝ ፥ ምኔ ነው አይንህን የሳበው? “ የሚል ጥያቄ ደቀነችብኝ ፤

“ ሁለመናሽን ወድጄው ነበር ፤ ግን “ ቶ “ የሚለውን ምልክት አንገትሽ ላይ ተነቅሰሽ ሳይ ተረታሁ”

“ እንዴት ?”

“ ምን ብየ ላስረዳሽ ፤ አየሽ “ ቶ” የሚለው ምልክት ለኔ ከጌጥ በላይ ነው፤ በጥንታዊ የኩሽ ህዝቦች ዘንድ “ የሕይወት ቁልፍ ‘የሚል ትርጉም አለው፤ እና ምልክቱን ሳይ “ እቺ ሴት የተዘጉ በሮችን ሁሉ የምትከፍትልህ ቁልፍ ናት የሚል ሃሳብ ብልጭ አለልኝ”

አሜክስ ትንሽ ስታመነታ ከቆየች በሁዋላ እንዲህ አለች፥

“ህምምምም! To be honest with you “ ቶ “ የሚለውን ምልክት የተነቀስኩት “ ቶፊቅን “ ለማስታወስ ነው “

“ቶፊቅ ደሞ ማን አባቱ ነው ?’

“ የመጀመርያ ፍቅረኛየ ነበር”

እሷ የሞተ ፍቅረኛዋን አስባ፥ እኔ የሞተ ፍቅሬን አስቤ መላቀስ ጀመርን፤

Bewuketu Siyum