Get Mystery Box with random crypto!

ወደ ፀጋው ዙፋን መቅረብ ዕብ4:16 (ክፍል 2) መቼም እግዚአብሔር ባለንበት ሆነን መባረክ: | Albastros Ministries

ወደ ፀጋው ዙፋን መቅረብ ዕብ4:16 (ክፍል 2)

መቼም እግዚአብሔር ባለንበት ሆነን መባረክ: መስጠት: መፈወስ አቅቶት አይደለም:: እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ ወደ እኔ ኑ: እኔም አሳርፋችዋለው ሲል: ባለንበት ሆነን ሸክማችንን መውሰድ: ማሳረፍ አቅቶት አይደለም::: አንድያ ልጁ ክብሩን ትቶ እንዲወርድ የጨከነበት ምክንያት ወደ እርሱ እንድንቀርብ ከእርሱም ጋር ህብረትን እንድናደርግ እንደ ተወደዱ ልጆች በቤቱ እንድንኖር: ከእግሩ ስር እንድንሆን ነው::

እናም ፀጋን: ምህረትን: በረከትን ማንኛውንም የሚያስፈልገንን ነገር ስንጠይቀው አሁንም "ቅረቡ" ይለናል:: ወደ ፀጋው ዙፋን :ወደ መገኘቱ ወደ ህልውናው እንድንቀርብ ይፈልጋል:: የምንፈልገውን ነገር ይዘን እንድንሄድ ሳይሆን: እርሱ ጋር እንድንኖር: ከምንፈልገው ነገር በላይ እሱን እንድንሻ: የምንፈልገው ነገር ግዜአዊ :እርሱ ግን የዘላለም ፍላጎታችን መሆኑን ልናሳየው ይወዳል:: ስለዚህ እንቅረብ: ከትላንትናው ይልቅ ወደ ፀጋው ዙፋን እንቅረብ::

ታድያ ወደ ዙፋኑ ሲቀረብ: በብዙ አክብሮት በመፍራት: የሚገባውን ክብር በመስጠት: በመገዛት በአጠቃላይ በአምልኮ ነው:: በአምልኮ ወደ ፀጋው ዙፋን ስንቀርብ: የምናየው ችሎታውን ነው:: የማድረግ ችሎታ: ጉልበቱን አቅሙን::

ያንን ሁሉን ቻይነቱን ስናይ: ይዘን የመጣነው ችግር: ድካም: አቅም ማጣት: እንረሳዋለን:: ከጉልበቱ ጉልበትን: ከአቅሙ አቅምን እናገኛለን:: ያኔ አቤቱ ጕልበቴ ሆይ፥ እወድድሃለሁ።እግዚአብሔር ዓለቴ፥ አምባዬ፥ መድኃኒቴ፥ አምላኬ፥ በእርሱም የምተማመንበት ረዳቴ፥ መታመኛዬ እንለዋለን:: እርሱ ደግሞ በእርሱ የሚታመኑትንም ያውቃል። ለእነርሱም መልካም ነው፥ በመከራ ቀንም መሸሸጊያ ነው::

ኢየሱስም ሃዋርያቱም አገልግለው ያለፉት: ሰዎች ወደ እግዚአብሔር በእምነት እንዲቀርቡ ነውና: እኛም አገልግሎታችን ሰዎች ወደ እኛ ሳይሆን ወደ እርሱ እንዲቀርቡ ይሁን::

አባት ሆይ: ወደ ፀጋህ ዙፋን በእምነት እቀርባለው

ሳሙኤል ተስፋ ሚካኤል ብዙነህ