Get Mystery Box with random crypto!

#የአምላካችን_የክርስቶስ_ጥንተ_ስቅለት መጋቢት ፳፯ ✞ የነገሥታት ንጉሥ የሕይወት ራስ ኢየሱ | ጎዶልያስ

#የአምላካችን_የክርስቶስ_ጥንተ_ስቅለት
መጋቢት ፳፯
✞ የነገሥታት ንጉሥ የሕይወት ራስ ኢየሱስ ክርስቶስን የአይሁድ ጭፍሮች በዕለተ ዐርብ የእሾኽ አክሊል ጐንጒነው በራሱ ላይ ደፍተውለታል፤ የእሾኽ አክሊል በመቀዳጀቱ በዘፍ ፫፥፲፰ ላይ አዳምን አስቀድሞ “ምድር እሾኽንና አሜከላን ታበቅልብኻለች” ብሎት ነበርና ያነን መርገም ደምስሶለት ለአዳም ክሷል፡፡
✞ ዳግመኛም አዳምና ሔዋን ምክረ ከይሲን ሰምተው የድል ነሺዎች አክሊል ተለይቷቸው ነበርና ያነን ሰማያዊ አክሊል እንደመለሰልን ለማጠየቅ፡፡ ይኽ ለካሳ አምላካችን ስለፈጸመው የድኅነት ምስጢር ቅዱሳት ደናግል በጥልቀት እንዲኽ አብራርተዋል፡-
✞ “አስተቀጸልዎ ከመዝ ለርእሰ ሕይወት አክሊለ ሦክ …” (የሕይወት መገኛ ርሱን የእሾኽ አክሊልን አቀዳጁት፤ መላእክትን የብርሃን ራስ ቁር የሚያቀዳጃቸው የነገሥታት ገዢ የሚኾን ርሱን የሾኽ አክሊል አቀዳጁት፤ በሾኽ አክሊልም ከራሱ ክፍል ያቆሰሉት ሺሕ ናቸው፤ ከራሱም ቊስሎች ደም እንደ ውሃ በዝቶ ፈሰሰ፤ ፊቱም ደምን ለበሰ ሰውነቱም በደም ተጠመቀ፤ የጽዮን ልጆች እናቱ ያቀዳጀችውን አክሊል ተቀዳጅቶ አዩት፤ ተድላ ደስታ የሚያደርግበትና የሙሽርነቱ ቀን ነውና (መሓ ፫፥፲፩) … ነገር ግን የሾኽ አክሊልን በመቀዳጀቱ በምድራችን ላይ የበቀሉትን አሜከላና እሾኽ ርግማንን አጠፋልን (ዘፍ ፫፥፲፰)፤ ራሱንም በዘንግ በመመታቱ የታላቁን እባብ ሰባቱን ራሶቹን ዐሥሩን ቀንዶቹን አጠፋልን (ራእ ፲፫፥፩)) ብለዋል፡፡
✞ ሊቁ ቅዱስ ኤራቅሊስም ስለፈጸመው ካሳ እንዲኽ አስተምሯል፡-
☞ “እንዘ ይትቄጸል አክሊለ ሦክ አብጠለ ኲነኔሁ ለቀኖተ ሞት ወእንዘ ቅንው ዲበ ዕፀ መስቀል ኢተዐርቀ እምነ መንበሩ…” (የእሾኽ አክሊል ደፍቶ የሞትን ሥልጣን ፍርድ አጠፋ፤ በመስቀል ላይ ተቸንክሮ ሳለ ከዙፋኑ አልተለየም፤ ከባሕርይ አባቱ ከአብ፤ ከባሕርይ ሕይወቱ ከመንፈስ ቅዱስ አልተለየም፤ በምድር አይሁድ እንደ በደለኛ ሲዘብቱበት፤ መላእክት በሰማይ የከበረ ጌትነቱን ይናገሩ ነበር) (ቅዱስ ኤራቅሊስ)
✞ እጆቹና እግሮቹ ስለመቸንከሩ አስቀድሞ በነቢዩ ዳዊት ዐድሮ በመዝ ፳፩፥፲፮ ላይ “ብዙ ውሾች ከብበውኛልና የክፋተኞች ጉባኤም ያዙኝ እጆቼንና እግሮቼን ቸነከሩኝ፤ ዐጥንቶቼ ኹሉ ተቈጠሩ እነርሱም አዩኝ ተመለከቱኝም” በማለት ውሻ ከአፉ ያወጣውን መልሶ ለምግብነት እንዲፈልገው፤ አይሁድም ኦሪትን እለፊ ካላት በኋላ ሲሠሯት በመገኘታቸው በውሻ መስሎ ትንቢት ያናገረባቸው ሲኾን፤ ይኽም ሊፈጸም ንጹሓት እጆቹና እግሮቹ በምስማር ከዕፀ መስቀሉ ጋር አያይዘው ቸንክረውታል፡፡
✞ የክብር ባለቤት ኢየሱስ ክርስቶስ ሔዋን በእግሮቿ ወደ ዕፀ በለስን በማምራቷ በድላ ነበርና ለርሷ ካሳ ሊኾን ንጹሓን እግሮቹ ሲቸነከሩ፤ በእጆቿም በለስን በመቊረጧ ንጹሐ ባሕርይ አምላክ እጆቹ በችንካር ተቸንክረዋል፡፡ በመቸንከሩም ለ፭ሺሕ ፭፻ ዘመን በሰው ልጆች ላይ የሠለጠነ የሞት ችንካር ጠፍቶልናል፡፡
✞ ምስጋና ይግባውና ኢየሱስ ክርስቶስ በመቸንከሩ ስለፈጸመው ካሳ ደናግል ሲተነትኑ፡-
☞ “ወበቅንዋቲሁ ሠበረ ለነ ቀኖተ ሞት …” (በመቸንከሩም የሞት ችንካርን አጠፋልን፤ ሔዋን በእግሮቿ ወደ ዕፀ በለስ ስለ ተመላለሰች እጆቹንና እግሮቹን በመቸንከር ከፍሏልና፤ በእጆቿም የበለስን ፍሬ ስለቈረጠች ፈንታ በእውነት የእግዚአብሔር ቃል በሥጋው ከመስቀል ዕንጨት ጋራ ተቸነከረ) በማለት አስተምረዋል፡፡
✞ መተርጒማን ሊቃውንት እንዳመሰጠሩት ጌታ በዕንጨት መስቀል ላይ መሰቀሉ ስለምን ነው ቢሉ?፤ እሾኽ በሾኽ ይነቀሳል ነገር በነገር ይወቀሳል እንዲሉ በዕፀ በለስ ምክንያት የገባውን ኀጢአት በዕፅ ለማውጣት በዕፀ መስቀል ላይ ተሰቅሏል፡፡
✞ ጌታችን ከምድር ከፍ ከፍ ብሎ ስለምን ተሰቀለ? ቢሉ፦ “እምከመ ተለዐልኩ እምድር እስሕብ ኲሎ ኀቤየ” (ከምድር ከፍ ከፍ ባልኊ ጊዜ ኹሉን እስባለኊ) ብሎ ነበርና ይኽነን ሊፈጽም ነው (ዮሐ ፲፪፥፴፪)፡፡
ዳግመኛም ከምድር ከፍ ከሰማይ ዝቅ ብሎ መሰቀሉ “ኅሩይ ማእከለ እግዚአብሔር ወሰብእ” እንዲል አምላክ ወሰብእ ኾኖ እንዳስታረቀን ለማጠየቅ፡፡
በመጨረሻም ምድርን በኪደተ እግሩ እየተመላለሰ እንደ ቀደሳት፤ ዐየራትን ደግሞ ሥብ እያጤሱ አስተራኲሰውት ነበርና አየራትን ለመቀደስ ነው፡፡
✞ ንጹሐ ባሕርይ ጌታችንን አይሁድ መስቀሉን አሸክመው ቀራንዮ ወደሚባል ቦታ ከወሰዱት በኋላ ኹለት ወንበዴዎችን በቀኝና በግራ አድርገው ጌታችንን በመኻከል ሰቅለውታል (ማቴ ፳፯፥፴፰፤ ማር ፲፭፥፳፯፤ ሉቃ ፳፪፥፴፫፤ ዮሐ ፲፱፥፲፰)፡፡
✞ ክፉዎች አይሁድ ይኽነን ያደረጉበት ምክንያት በክፋት ነው፤ ይኸውም በቀኝ የሚመጡ ሰዎች በቀኝ የተሰቀለውን ወንበዴ አይተው “ይኽ ምንድነው?” ብለው ሲጠይቁ “ወንበዴ ነው” ይሏቸዋል፤ ከዚያም ጌታን “ይኽስ ምንድነው?” ብለው ሲጠይቁ “ይኽስ ከርሱ ልዩ ነውን አንድ ነው እንጂ” ብለው ሰዎችን ለማሳሳት፤ በግራ የሚመጡ ሰዎች በግራ የተሰቀለውን ወንበዴ አይተው “ይኽ ምንድነው?” ብለው ሲጠይቁ “ወንበዴ ነው” ይሏቸዋል፤ ከዚያም ጌታን “ይኽስ ምንድነው?” ብለው ሲጠይቁ “ይኽስ ከርሱ ልዩ ነውን አንድ ነው እንጂ” ብለው ሰዎችን ለማሳሳት ያደረጉት ነው፡፡

ዳግመኛም አነገሥንኽ ብለውታልና ቀኛዝማች ግራዝማች ሾምንልኽ ለማለት ለመዘበት፡-
በተጨማሪም ነቢዩ ኢሳይያስ በምዕ ፶፫፥፲፪ ላይ “ከዐመፀኞችም ጋር ተቈጥሯልና” የሚለው ትንቢቱን ሊፈጽም ሲኾን ምስጢሩ ግን እኛን ከጻድቃን ጋራ አንድ ያደርገን ዘንድ ርሱ ከበደለኞች ጋር ተቈጥሯል፤ ሌላውም በዕለተ ምጽአት እኛን ኃጥኣንን በግራ ጻድቃንን በቀኝ ታቆማለኽ ሲያሰኛቸው ነበር (ማቴ ፳፭፥፴፫፤ ራእ ፩፥፯)፡፡
✞ በኹለት ወንበዴዎች መኻከል ከሰቀሉት በኋላ ጲላጦስም “የአይሁድ ንጉሥ የናዝሬቱ ኢየሱስ” የሚል ጽሕፈት በዕብራይስጥና በሮማይስጥ በግሪክም ጽፎ በመስቀሉ ላይ አኖረው፤ (ዮሐ ፲፱፥፲፰-፳፪)፤ የአይሁድ ካህናት አለቆች ጲላጦስን “ርሱ የአይሁድ ንጉሥ ነኝ እንዳለ እንጂ የአይሁድ ንጉሥ ብለኽ አትጻፍ” ሲሉት፤ ጲላጦስም “የጻፍኹትን ጽፌአለኊ” ብሎ መልሶላቸዋል፤ ይኽነንም በሕማማት ድርሳኑ ላይ ሲተረጒሙት፡- “ወዝ መጽሐፈ ጌጋይ ዘጸሐፎ ጲላጦስ ወአንበሮ መልዕልተ ርእሱ ይደምስስ ለነ በኲሉ ጊዜ መጽሐፈ ዕዳነ ዘጸሐፉ አጋንንት” (ጲላጦስ ጽፎ ከራሱ በላይ ያኖረው በደሉን የሚናገር ይኽ መጽሐፍ ኹልጊዜ አጋንንት የጻፉትን የዕዳችንን መጽሐፍ ያጠፋልን ዘንድ ነው) በማለት አራቅቀው ገልጠዋል፡፡
✞ ጌታችን በሚሰቀልበት ጊዜ ብርሃን ያለበሳቸውን አምላክ ዕርቃኑን ለመሰወር ከስድስት ሰዓት እስከ ዘጠኝ ሰዓት ድረስ ፀሓይና ጨረቃ ብርሃናቸውን ነሥተዋል (ማቴ ፳፯፥፵፭፤ ማር ፲፭፥፴፫፤ ሉቃ ፳፫፥፵፬-፵፭)፡፡
❖ ይኽ በጌታ ስቅለት ዕለት እንደሚደረግ አስቀድሞ በነቢዩ አሞጽ ኹለት ጊዜ በትንቢት ተነግሯል፡- ይኸውም
“የእግዚአብሔር ቀን ብርሃን ሳይኾን ጨለማ አይደለምን? ጸዳል የሌለውም ድቅድቅ ጨለማ አይደለምን?” (አሞ ፭፥፳)