Get Mystery Box with random crypto!

'በዚያም ቀን ፀሐይ በቀትር እንድትገባ አደርጋለኊ ይላል ጌታ እግዚአብሔር በብርሃንም ቀን ምድሩን | ጎዶልያስ

"በዚያም ቀን ፀሐይ በቀትር እንድትገባ አደርጋለኊ ይላል ጌታ እግዚአብሔር በብርሃንም ቀን ምድሩን አጨልማለኊ” (አሞ ፰፥፱) ተብሎ
✞ በዕለተ ዐርብ በጌታችን ስቅለት ዕለት ስለተደረገው ስለዚኽ ታላቅ ተአምር ሊቃውንት እንዲኽ ይገልጹታል፡-
☞ “ጐየ ፀሓይ ወጸልመ ወርኅ ወከዋክብትኒ ተኀብኡ ከመ ኢያብርሁ ለምእመናን በጊዜ ስቅለቱ ቅዱስ እንዘ ፍጹም በገሃሁ ወርኅ ኢያብርሀ…” (ፀሓይ ብርሃኑን ነሣ ጨረቃም ጨለመ፤ ከዋክብትም በከበረ ስቅለቱ ጊዜ ለምእመናን እንዳያበሩ ብርሃናቸውን ነሡ፤ ጨረቃም በምልአቱ ሳለ አላበራም፤ ፀሓይ ብርሃኑን በነሣ ጊዜ ፍጡራን ኹሉ በጨለማ ተያዙ፤ የፈጠራቸው ፈጣሪያቸው እንደ ሌባ እንደ ወንበዴ በዕንጨት ላይ ተሰቅሎ እንዳያዩ ቀኑ ጨለመ፤ ባለሟሉ መልአክም ከሓድያንን ያጠፋቸው ዘንድ ሰይፉን በእጁ መዝዞ ይዞ ከመላእክት መኻከል ወጣ፤ የክርስቶስም ቸርነት በከለከለችው ጊዜ ያ መልአክ የቤተ መቅደሱን መጋረጃ በሰይፉ መታው ቀደደውም፤ ከላይ እስከ ታችም ወደ ኹለት አደረገው (ማቴ ፳፯፥፶፩፤ ማር ፲፭፥፴፰፤ ሉቃ ፳፫፥፵፭)፤ መላእክትም ኹሉ በሰማይ ኹነው ርሱን አይተው በአንድነት ሲቈጡ የአብ ምሕረቱ፣ የወልድ ትዕግሥቱ፣ የመንፈስ ቅዱስ ቸርነቱ ከለከለቻቸው፤ ፀሓይ ብርሃኑን ነሣ፤ በጨለማ ተይዞ ሲድበሰበስ ዓለምንም ተወው፤ ይኽ ኹሉ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነፍሱን ከሥጋው ከመለየቱ አስቀድሞ ተደረገ) (ቅዱስ አትናቴዎስ)
☞ “እስመ ሶበ ተሰቅለ ክርስቶስ ጸልመ ሰማይ አሜሃ ወፀሓይኒ ሰወረ ብርሃኖ ወወርኅኒ ደመ ኮነ…” (ክርስቶስ በተሰቀለ ጊዜ ያን ጊዜ ሰማይ ጨለማ ኾነ፤ ፀሓይም ብርሃኑን ነሣ፤ ጨረቃም ደም ኾነ፤ ምድርም ተነዋወጠች ደንጊያውም ተከፈለ፤ መቃብራትም ተከፈቱ፤ ስለዚኽም ለፍጡራን ከፈጣሪያቸው ጋር ሊታመሙ ተገባቸው (ማቴ ፳፯፥፵፭-፶፩) (ቅዱስ ሱኑትዩ)
☞ “ፀሓይ ጸልመ ወወርኅ ደመ ኮነ ወከዋክብት ወድቁ ፍጡነ ከመ ኢይርአዩ ዕርቃኖ ለዘአልበሶሙ ብርሃነ” (ፀሓይ ጨለመ፤ ጨረቃም ደም ኾነ፤ ከዋክብትም ፈጥነው ወደቁ፤ ብርሃንን ያጐናጸፋቸውን የጌታን ዕርቃን እንዳያሳዩ) (አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ)
✞ ሊቁ አባ ጊዮርጊስም ምስጢሩን በመጠቅለል በሕማማት ሰላምታው ላይም፡-
“ፀሓይ ብሩህ አሜሃ ጊዜ ቀትር ጸልመ
ወወርኅኒ ጽዱል ተመሰለ ደመ
ትንቢት ከመ ቀደመ፤ ስብሐት ለከ”
(ብሩህ የኾነ ፀሓይ ያን ጊዜ በቀትር (በስድስት ሰዓት) ጨለመ፤ ጽዱል የኾነ ጨረቃም ደምን መሰለ፤ አስቀድሞ ትንቢት እንደተነገረ፤ ጌታ ሆይ ምስጋና ይገባኻል) በማለት ከትንቢተ ነቢያት በመነሣት በዚኽ በስድስት ሰዓት ምስጋናው ላይ በሰዓቱ ከተከናወነው ምስጢር በመነሣት አስተምሯል፡፡
✞ በመስቀል የተሰቀለው የክብር ባለቤት ሰማይን የፈጠረ ነውና በሰማይ ከላይ የተጠቀሱት ተአምራት ሲደረጉ ምድርንም የፈጠረ ነውና በምድር ደግሞ አራት ተአምራት ማለት የቤተ መቅደሱ መጋረጃ ከላይ እስከ ታች ለኹለት ተቀደደ፤ ምድር ተናውጣ ዐለቶች ተሠንጥቀዋል፤ መቃብራት ተከፍተዋል፤ ከ፭፻ በላይ ሙታን ተነሥተዋል (ማቴ ፳፯፥፵፭፤ ፳፯፥፶፩፤ ፳፯፥፶፪-፶፫)፡፡
✞ ከዚኽ በኋላ የተነገረው ትንቢት ኹሉ እንደተፈጸመ አይቶ የሕይወት ውሃ ምንጭ ጌታ ከእኛ ጽምዐ ነፍሳችንን ለማራቅ በፈቃዱ “ተጠማኊ” ባለ ጊዜ ነቢዩ ዳዊት አስቀድሞ በመዝ ፷፰፥፳፩ ላይ “ወወደዩ ሐሞተ ውስተ መብልዕየ ወአስተዩኒ ብሒአ ለጽምእየ” (በምግቤ ሐሞት ጨመሩበት፤ ለጥማቴም ኾምጣጤ አጠጡኝ) በማለት የተናገረው ትንቢት ሊደርስ ሊፈጸም አይሁድ በዚያም ኾምጣጤ የመላበት ዕቃ ተቀምጦ ነበርና እነርሱም ኾምጣጤውን በሰፍነግ መልተው በሁስጱም አድርገው በአፉ ውስጥ ጨምቀውለታል፡፡
በመጠማቱም ከእኛ ጽምዐ ነፍስን አርቆልናልና፤ መራራ ሐሞትን በመቅመሱ ከሰው ልጆች ላይ መራራው ሞት ጠፍቷል፡፡
ሊቁ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫም በሰባቱ ጊዜያት የጸሎት መጽሐፉ ላይ፤ ጌታችን ሐሞትንና ከርቤን መጠጣቱ ስለምን እንደኾነ፡-
“ከመ ታስትየነ ለነ ደመ ገቦከ ነባቤ
እንተ አስተዩከ ሐሞተ ወከርቤ
ጸማእኩ በጊዜ ትቤ፤ ስብሐት ለከ”
(ነባቢ የሚኾን የጐንኽን ደም ታጠጣን ዘንድ ተጠማኊ ባልኽ ጊዜ ሐሞትን ከርቤን ያጠጡኽ ጌታ ምስጋና ለአንተ ይገባል) በማለት ገልጦታል፡፡
✞ ቅዱሳን ደናግልም መራራ ሐሞትን ጌታችን በመቅመሱ ለ፭ሺሕ ፭፻ ዘመን የሠለጠነ መራራ ሞት ከሰዎች ስለመወገዱ፡-
“ወሰሪቦ እግዚእ ኢየሱስ ብኂዐ ይቤ ተፈጸመ ኲሉ…” (ጌታችን ኢየሱስ መጣጣውን ቀምሶ በመጽሐፍ የተጻፈው ኹሉ ደረሰ ተፈጸመ አለ፤ በጒረሮው መጠማትና በአንደበቱ መድረቅ ከሥጋና ከነፍስ መጠማት አዳነን፤ በቀትርም ጊዜ የዝኆን ሐሞትና ከርቤ የተቀላቀለበት መጻጻንና የበግ ሐሞትን በመጠጣቱ የጣፈጠ የበለስ ፍሬን ስለ በሉ ስለ አዳምና ስለ ሔዋን ከፈለ፤ ለእኛም መሪር የኾነ ሞትንና ርግማንን አጠፋልን) በማለት ተንትነው ጽፈዋል፡፡
ነገረ ክርስቶስ ክፍል አንድ ከሚለው 622 ገጽ ካለው መጽሐፌ በጥቂቱ የተወሰደ
በመስቀል ተሰቅለኽ ፈያታዊ ዘየማንን ያሰብከው አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ በቸርነትኽ ዐስበን፡፡
በመጋቤ ሐዲስ ዶክተር ሮዳስ ታደሰ

ለኦርቶዶክስ ተዋህዶ ልጆች #share እናድርግ
@aklesyazetewahdo
@aklesyazetewahdo
@aklesyazetewahdo