Get Mystery Box with random crypto!

#ንስሐ_በቅዱስ_ኤፍሬም ወንድሞቼ ሆይ! ጊዜ ሳለልን ንስሐ እንግባና ለንስሐ የሚገባ ፍሬ እናፍራ፡ | ጎዶልያስ

#ንስሐ_በቅዱስ_ኤፍሬም

ወንድሞቼ ሆይ! ጊዜ ሳለልን ንስሐ እንግባና ለንስሐ የሚገባ ፍሬ እናፍራ፡፡ ጌታችን ምን እንዳለ እስኪ አድምጡ፡- “ንስሐ ከማያስፈልጋቸው ከዘጠና ዘጠኝ ጻድቃን ይልቅ ንስሐ በሚገባ በአንድ ኃጢአተኛ በሰማይ ደስታ ይኾናል” /ሉቃ.15፥7/፡፡

ወንድሞቼ ሆይ! ስለምን ታድያ በኃጢአት፣ በስንፍና፣ በንዝህላል እንደተያዘዝን እንቆያለን? ስለምንድነው ተስፋ ቆርጠን የምንቆዝመው? በእኛ ንስሐ መግባት ምክንያት በሰማያት ታላቅ ደስታ የሚሆን ከሆነ ምንድነው የሚያስፈራን? ቅዱሳን መላዕክት ስለ እኛ ንስሐ እጅግ ደስ የሚላቸው ከሆነ ስለምንድነው እኛ ልል ዘሊል፣ ደንታ ቢስና ፈዛዛ የምንሆነው? የመላዕክት ጌታ ንስሐ ግቡ እያለ አስተምሮን ሳለ ምንድነው የምንፈራው? የማይከፈሉ ሦስት፣ የማይጠቀለሉ አንድ የሚሆኑ ሥላሴ ንስሐ እንገባ ዘንድ እየጠሩን ሳለ እኛ ያለምንም የንስሐ ፍሬ እንቆይ ዘንድ አግባብ ነውን?

ተወዳጆች ሆይ! በዚህ ጊዜአዊ ዓለም ርኵሰት ጣዕም አንታለል፡፡ እንዲህ ካልሆነ ግን እሳቱ የማይጠፋ ትሉ የማያንቀላፋ ምረረ ገሃነም ይጠብቀናል፡፡ ስለዚህ ከዘለዓለማዊው እሳት እንድን ዘንድ አሁን ጥቂት ብናለቅስ ይሻለናል፡፡

ተወዳጆች ሆይ! እስኪ እናስተውል፡፡ ስለምንናገረው ነገርም ችላ የሚለው ሰው ከቶ አይገኝ፡፡ ክርስቶስ ድንገት እንደ ብርሃን ብልጭታ ይመጣልና፡፡ ክርስቶስ ድንገት በመጣ ጊዜ በዙፋኑ ላይ ተቀምጦም ለሁሉም እንደየሥራው ሲከፍለው ማየት አያስፈራምን? የዚያን ጊዜ ሁሉም የየራሱን ሸክም ይሸከማል፡፡እያንዳንዱ ሰው በዚህ ምድር የዘራውን ያጭዳል፡፡ ሁሉም ዕራቆቱ ይቆማል፡፡ ሁሉም ወደ ክርስቶስ የፍርድ ዙፋን ይቀርባል፡፡ የዚያን ጊዜ ማንም ማንንም መርዳት አይችልም፡፡ ወንድም ወንድሙን ወይም ጓደኛ ጓደኛውን መርዳት አይችልም፡፡ ወላጆች ልጆቻቸውን መርዳት አይችሉም፡፡ ልጆች ወላጆቻቸውን መርዳት አይችሉም፡፡ ባሎች ሚስቶቻቸውን መርዳት አይችሉም፡፡ ሁሉም በፍርሐትና በረዐድ በመንቀጥቀጥም የእግዚአብሔርን ፍርድ ይጠብቃል እንጂ ማንም ማንንም መርዳት አይችልም፡፡

ወንድሞቼ ሆይ! ታድያ ለምንድነው ጊዜ ሳለልን የምንሰንፈው? ለምንድነው ልል ዘሊል የምንሆነው? ለምንድነው በምግባር በሃይማኖት የማንዘጋጀው? ለምንድነው ጊዜ ሳለልን የማናስተውለው? ለምንድነው ቃለ ሕይወትን ለመስማት የማንቻኰለው? ስለምንድነው ቃለ እግዚአብሔርን የማንሰማው? ስለምንድነው ቃለ ክርስቶስን ችላ የምንለው? ቃሉ በዚያ ሰዓት እንደሚፈርድብን አትገነዘቡምን? ቃለ ነቢያት ቃለ ሐዋርያት በዚያ ሰዓት እንደሚፈርድብን አታውቁምን? ካላወቃችኁ ጌታችን ለደቀ መዛሙርቱ ያላቸውን አድምጡ “የሚሰማችሁ እኔን ይሰማል እናንተንም የጣለ እኔን ይጥላል፤ እኔንም የጣለ የላከኝን ይጥላል” /ሉቃ.10፥16/፡፡ ዳግመኛም በሌላ አንቀጽ እንዲህ ብሏል፡- “የሚጥለኝ ቃሌንም የማይቀበለው ርሱ የሚፈርድበት አለው፤ እኔ የተናገርኩት ቃል ርሱ በመጨረሻው ቀን ይፈርድበታል” /ዮሐ.12፥48/፡፡ በመጨረሻው ቀን የሚፈርድብን ቃሉስ የትኛው ነው? በወንጌሉ እንዲሁም በሐዋርያትና በነቢያት አድሮ የተናገረው ቃሉ፡፡ እንኪያስ ወንድሞቼ ሆይ! ቃሉን ችላ የምንለው አንኹን፡፡ “ሰማይና ምድር ያልፋሉ፤ ቃሌ ግን አያልፍም” ያለውን አንርሳው /ማቴ.24፥35/፡፡

እንኪያስ እጅግ የምወዳችሁ ሆይ! ኑ! አስፈሪው ቀን ሳይመጣ ቃሉን ሰምተን ንስሐ እንግባ፡፡ የእግዚአብሔርን ምሕረት እንቀበል፡፡ እግዚአብሔር ዛሬ ምሕረቱን እንድንቀበል እንዲህ እያለ ያበረታታናልና፡- “እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ ወደ እኔ ኑ፤ እኔም አሳርፋችኋለሁ” ማቴ.11፡28፡፡ በዚህ ቃሉ ትዕግሥተኛው፣ አፍቃሪውና ሰው ወዳጁ ጌታ ሁላችንም እንድን ዘንድ ይጠራናል፡፡ የጠራው የተወሰኑ ሰዎችን ብቻ አይደለም፤.“ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ” ብሎ ሁላችንም እንጂ፡፡ “ባለጸጋም ቢሆን ድኻም ቢሆን ሁሉም ወደ እኔ ይምጣ፡፡ ወደ እኔም የሚመጣውን ከቶ ወደ ውጭ አላወጣውም፡፡ ወደ እኔ የሚመጣውስ ማን ነው ትዕዛዛቴን የሚጠብቀው፤ ቃሌን የሚሰማው፤ በላከኝም የሚያምነው፡፡” የክርስቶስን ቃል ሰምቶ ንስሐ የሚገባው ንስሐም ገብቶ የንስሐን ፍሬ የሚያፈራ ሰው ንዑድ ክቡር ነው፡፡ የማይሰማው ግን እጅግ ጐስቋላ ሰው ነው፡፡ እንዲህ ተብሎ እንደተጻፈ፡- “በሕያው እግዚአብሔር እጅ መውደቅ የሚያስፈራ ነው” /ዕብ.10፥31/፡፡

@aklesyazetewahdo
@aklesyazetewahdo
@aklesyazetewahdo