Get Mystery Box with random crypto!

'በሌሊት ወደ ኢየሱስ መጣ' (ሽራፊ ሃሳብ 1 ከኒቆዲሞስ ምንባብ) ኒቆዲሞስ በውድቅት ሌሊት ወደ | ጎዶልያስ

"በሌሊት ወደ ኢየሱስ መጣ"
(ሽራፊ ሃሳብ 1 ከኒቆዲሞስ ምንባብ)

ኒቆዲሞስ በውድቅት ሌሊት ወደ ጌታችን መጣ። ሌሊት እንግዲህ በቂ ብርሃን የሌለበት ፣ እንቅፋት የሚበዛበት ፣ ጭልም የሚልበት ፣ ግራ ቀኝ ቢያዩ ሰው የሚታጣበት ፣ ማጅራት ከሚመቱ ወንበዴዎች በቀር በመንገድ ሌላ ሰው የማያጋጥምበት ፣ ብርድና ቆፈን ሰውነትን የሚያስጨንቅበት ሰዓት ነው። ይህ የአይሁድ መምህር በሌሊት የመጣበት ምክንያቱ ብዙ ሲሆን ለእምነት ማነስ ማሳያ የሚሆን ሰው ነው።

ዛሬ ደግሞ ለአፍታ ኒቆዲሞስን "በሌሊት ወደ ኢየሱስ በመምጣቱ" በጥቂቱ እናመስግነው። ብዙ እግሮች ወደ ኃጢአት በሚሮጡባት ሌሊት ወደ ክርስቶስ የሮጠውን ይህንን ሰው እስቲ እናድንቀው! ይህንን የሌሊት ግርማ ሳይበግረው ወደ ኢየሱስ የተጓዘ የጨለማ ተጓዥ ፣ ይህንን ሰዓታት ቋሚ ፣ ይህንን ማሕሌት ቋሚ በጥቂቱ ብናመሰግነው ምን አለ? ከጌታ ፊት ቆሞ ቅኔ የተመራውን ፣ ስለ ልደት እየተናገረ ስለ ጥምቀት የሚያመሰጥረውን የፈጣሪን ቅኔ ተቀብሎ ሊያዜም ከጀመረ በኋላ መቀበል ሲያቅተው ጌታችን "አንተ የአይሁድ መምህር ስትሆን ይህንን አታውቅምን?" ብሎ የገሠፀውን ኒቆዲሞስን እስቲ ዛሬ በበጎነቱ አርኣያ እናድርገው።

በሕይወታችን ውስጥ የተስፋ ብርሃን ጭልም ባለብን ጊዜ ፣ እንቅፋት በበዛብን ወቅት ፣ ግራ ቀኝ አይተን ሰው ባጣንበትና ብቸኝነት በዋጠን ሰዓት ፣ ክፉ ከማድረግ በማይመለሱ ጨካኞች በተከበብን ሰዓት እኛስ ወዴት እንሔዳለን?

ሕይወቱ "ሌሊት" የሆነበት ሰው ሁሉ ወደ መድኃኔ ዓለም ክርስቶስ ቢሔድ እንደሚሻለው ከኒቆዲሞስ የተሻለ ምሳሌ የለም። ሕይወቱ የጨለመ ባይሆን እንኳን ልቡ የጨለመበት ፣ በኃጢአት ጠል የጠቆረ ፣ በበደል ብርድ ቆፈን እጅ እግሩ የታሰረ ከእኛ መካከል ስንት አለ?

እመነኝ ፣ ተስፋ ቆርጠህ ቁጭ ብለህ እስከሚነጋልህ ብትጠብቅ አይነጋም። ይልቅ ተነሥና "በሌሊት ወደ ክርስቶስ ሒድ" እርሱ ተስፋ ለቆረጠው ማንነትህ ዳግመኛ መወለድ እንዳለም ይነግርልሃል። ኒቆዲሞስ ጌታችንን ሊያየው ሔዶ ራሱ ታይቶ እንደመጣ አንተም ወደ እርሱ የቀረብህ እንደሆነ ራስህን ታያለህ።

በ"ሌሊት" ውስጥ ለሚኖር ሰው ነግቶ ፀሐይ ትወጣልኛለች ብሎ ከሚጠባበቅ ይልቅ በሌሊት እንደ ኒቆዲሞስ ተነሥቶ ወደ ጽድቅ ፀሐይ ወደ ክርስቶስ ቢሔድ ይሻለዋል። ወደ እርሱ ለሚሔድ ሰው ሌሊቱ ይነጋል ፣ ክርስቶስ ያለበት ሌሊት ከቀን ይልቅ ብሩሕ ነው ፣ እውነተኛው ብርሃን ያለበት ጨለማም ጨለማ አይደለም። ስለ እርሱ "ጨለማም በአንተ ዘንድ አይጨልምም" ተብሎ ተጽፎአልና።

ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ
መጋቢት 16 2010
ኒቆዲሞስ
ናይሮቢ ፣ ኬንያ