Get Mystery Box with random crypto!

'አሚር ሆይ! አንተ 'ኸይሩን' ብቻ አስብ፤ “ለሸሩ” ባለቤት አለውና!!' ----- ጸሐፊ: አፈንዲ | AfandishaHarar 🇪🇷🇪🇹🇯🇴🇸🇩🇪🇭🇸🇴

"አሚር ሆይ! አንተ "ኸይሩን" ብቻ አስብ፤ “ለሸሩ” ባለቤት አለውና!!"
-----
ጸሐፊ: አፈንዲ ሙተቂ
----
እነሆ የሀረር ተረት ልናካፍላችሁ ነው፡፡ ተረቱን ያጫወቱን የረጅም ጊዜ ጎረቤታችን የነበሩት አቶ ዑመሬ አብዱልቃዲር ናቸው፡፡ እኚህ ሰው ዛሬ በህይወት የሉም፡፡ አላህ ጀንነት እንዲወፍቃቸው እየተመኘን ተረቱን እንደወረደ እንጽፍላችኋለን (“እኛ” እንዲህ የምንላችሁ “እኛ” መሆናችንን እያስታወሳችሁ)፡፡
------
በጥንት ዘመን አንድ ቅን ሰውዬ በሀረር ከተማ ይኖር ነበር፡፡ ይህ ሰው ሁለት ልጆች ነበሩት፡፡ የመጀመሪያው ልጁ ርህሩህና የዋህ የነበረ ሲሆን ሁለተኛው ልጁ ግን ተንኮል እየፈጠረ ሰዎችን ማሞኘትና መሳቅ ይወድ ነበረ፡፡ አባትዬው ትንሹን ልጅ ቢመክረው አልሰማ እያለ አስቸገረው፡፡ ስለዚህ በትንሹ ልጅ ተስፋ የቆረጠው አባት ዘወትር ትልቁን ልጅ እየጠራው “ልጄ ሆይ! አንተ ደጉን ብቻ አስብ፡፡ ለተንኮል ባለቤት አለውና” የሚል ምክር ይሰጠው ነበር፡፡ አባት በዚህም ሳያበቃ ለትልቁ ልጅ “ዓሊ ኸይሮ” (ቅን አሳቢው ዓሊ) የሚል ቅጽል አወጣለት፡፡ ትንሽየውን ግን “ዓሊ ሸርሮ” (ተንኮለኛው ዓሊ) በማለት ሰየመው፡፡

ከጊዜ በኋላ አባት የአዱኛውን ዓለም ተሰናበተ፡፡ በዚህም የተነሳ ልጆቹ ተቸገሩ፡፡ ኑሮ በጣም ከበዳቸው፡፡ በመሆኑም ወደ ሀረሩ አሚር ሄደው በችግር መቆራመዳቸውን ነገሩት፡፡ አሚሩ በአጋጣሚ የቤተ መንግሥት ከብቶችን የሚጠብቅ ሰው ይፈልግ ነበርና ወንድማማቾቹ ለእረኝነት እንዲቀጠሩ ጠየቃቸው፡፡ ወንድማማቾቹ ለስራው የሚሰጣቸውን ምንዳ ሲጠይቁት ከሚበሉት ምግብና ከሚለብሱት ልብስ በተጨማሪ በዓመቱ መጨረሻ ላይ አንዲት ጊደር እንደሚያገኙ አሳወቃቸው፡፡ ወንድማማቾቹም ከአሚሩ የቀረበላቸውን ጥያቄ በደስታ ተቀበሉትና ስራቸውን ጀመሩ፡፡

ወንድማማቾቹ በመቶዎች የሚቆጠሩትን የአሚሩን ከብቶች “አው-ሓኪም”፣ “አቦከር” እና “ሸድዳ ዋ መድዳ” ወደሚባሉት ተራሮች እያሰማሩ በትጋት ማገዱን ተያያዙት፡፡ ስራቸውን በደህና ሁኔታ እያከናወኑ ዓመቱን አገባደዱት፡፡ የዓመቱ መጨረሻ እየተቃረበ ሲመጣ ግን የ“አሊ ሸርሮ” ልብ በግለኝነት መመታት ጀመረች፡፡ ለምንዳ የምትሰጣቸውን ጊደር ጉዳይ ሲያስብ አዕምሮው በስስት ተወጠረ፡፡ በመሆኑም “ወንድሜን ገድዬው ጊደሪቱን የግሌ ማድረግ አለብኝ” በማለት ወሰነ፡፡ እቅዱንም በአው ሓኪም ተራራ ላይ ለመፈጸም ቆረጠ፡፡

ወንድማማቾቹ ከብቶቹን ወደ “ሓኪም” ተራራ በወሰዱበት በአንደኛው ቀን “አሊ ሸርሮ” ለወንድሙ “አንተ ከዚህ ሆነህ ከብቶቹን ጠብቅ፤ እኔ ተራራው ላይ ወጥቼ ለምለም ሳር እንዳለ ልይና ልመስ” አለው፡፡ “አሊ ኸይሮ”ም በቀረበለት ሃሳብ ተስማምቶ ከብቶቹን ለብቻው መጠበቅ ጀመረ፡፡ “አሊ ሸርሮ” ከተራራው ላይ እንደ ወጣ ትልቅ ድንጋይ አንቀሳቅሶ ወንድሙ ወዳለበት አቅጣጫ ቁልቁል ለቀቀው፡፡ ድንጋዩ ከተራራው ላይ እየተንከባለለ ወረደ፡፡ ከ“አሊ ኸይሮ” አጠገብ ሲደርስ ግን ወደ ወርቅነት ተቀየረ፡፡ “አሊ ኸይሮ” በዚህ ተአምር ተገረመ፡፡ “ወደ ወርቅነት የተቀየረው ድንጋይ እኔና ወንድሜ ሀብታም እንድንሆን ዘንድ ከአላህ የተሰጠን ነው” በማለት በደስታ ፈጣሪውን አመሰገነ፡፡ የተፈጠረውንም ተአምር ለወንድሙ ለመንገር በጉጉት ይጠባበቅ ጀመር፡፡
“አሊ ሸርሮ” በበኩሉ “አሊ ኸይሮ በድንጋይ በመገደሉ “ጊደሪቱ የኔ ብቸኛ ሀብት ትሆናለች” እያለ በደስታ ከተራራው ወረደ፡፡ ወንድሙ ወደነበረበት ቦታ ሲደርስ ግን ያልጠበቀውን ነገር አየ፡፡ “ይህ ወርቅ ከየት ነው የመጣው?” በማለትም ወንድሙን ጠየቀው፡፡ አሊ ኸይሮም “አንድ ትልቅ ድንጋይ ከተራራው ላይ እየተንከባለለ መጥቶ እኔ ጋ ሲደርስ ይህንን ወርቅ ሆነ” በማለት መለሰለት፡፡ “አሊ ሸርሮም “ድንጋዩ የተንከባለለው ከስሩ የነበረውን ለምለም ሳር ለማየት ብዬ ስላንቀሳቀስኩት ነው፤ እዚህ ደርሶ ወደ ወርቅ ከተቀየረ እኔም የራሴ ወርቅ ሊኖረኝ ይገባል፡፡ ስለዚህ አንተም በተራህ ወደ ተራራው ውጣና ሌላ ድንጋይ አንከባልልኝ” አለው፡፡

“አሊ ኸይሮ”ም ከወንድሙ የሰማውን ሳይጠራጠር ወደ ተራራው ወጥቶ ትልቅ ድንጋይ አነሳና “አሊ ሸርሮ” ወደነበረበት አቅጣጫ አንከባለለው፡፡ ይሁንና ድንጋዩ ወደ ወርቅነት ሳይቀየር “አሊ ሸርሮ”ን ጭፍልቅ አድርጎ ገደለው፡፡ “አሊ ኸይሮ” ከተራራው ወርዶ ወንድሙ ወደነበረበት ስፍራ ሲሄድ ወንድሙ ሞቶ አገኘው፡፡ በዚህም በጣም ደነገጠ፡፡ ወደ ሀረሩ አሚር ሄዶም የተከሰተውን ሁሉ አንድ በአንድ ነገረው፡፡ ሆኖም አሚሩ ሊያምነው አልቻለም፡፡ “ወንድምህን ራስህ ነህ የገደልከው” በማለትም ከሰሰው፡፡ በመሆኑም “ነፍስ ያጠፋ ሰው ይገደል” በሚለው የሀረር ከተማ ጥንታዊ ህግ መሰረት በድንጋይ ተጨፍልቆ እንዲሞት ተፈረደበት፡፡

“አሊ ኸይሮ”ም ፍርዱ ሊፈጸምበት ወደ “ሐኪም” ተራራ ግርጌ ተወሰደ፡፡ ከተራራው ላይ ትልቅ ድንጋይ ተንዶ ቁልቁል ተወረወረበት፡፡ ይሁንና ድንጋዩ “አሊ ኸይሮ” አጠገብ ሲደርስ እንደገና ወርቅ ሆኖ ቁጭ አለ፡፡ የቅጣቱን አፈጻጻም ለማየት በስፍራው ተሰብስቦ የነበረው የሀረር ህዝብም በተፈጠረው ነገር በጣም ተገረመ፡፡ “ይህ ተአምር ልጁ ወንድሙን እንዳልገደለ በሐቅ ይመሰክራል” በማለትም ደመደመ፡፡ የሀረሩ አሚር በበኩሉ “የዓሊ ኸይሮ”ን ተአምር ሲያይ “በህይወቴ ስፈልገው የነበረውን ሐቀኛ ሰው ዛሬ አገኘሁት” የሚል ቃል ተናገረ፡፡ “አሊ ኸይሮ”ንም የዙፋኑ ወራሽ በማድረግ ሾመው፡፡
-----
ወደ ሀረርጌ ከመጣችሁ “Amiroo! Kheyruma yaadi, Sharriin abbuma eeydii” የሚል አባባል ትሰማላችሁ፡፡ “አሚር ሆይ! አንተ ኸይሩን ብቻ አስብ፤ ለሸርሩ ባለቤት አለውና” እንደማለት ነው፡፡ ከአባባሉ ጀርባ ብዙ ታሪኮች ይነገራሉ፡፡ ከነዚያ ታሪኮች መካከል አንዱ ከላይ የቀረበው ተረት ነው፡፡

በተረቱ እንደተገለጸው ተንኮለኛ ሰው በለስ የቀናው መስሎት ብዙ የሸር ትብታቦችን ሊተበትብ ይችላል፡፡ ይሁንና እንደዚህ ዓይነቱ ሰው አጓጉል ሆኖ ነው የሚቀረው፡፡ የማታ ማታ ራሱ በሸረበው የተንኮል ድር መታሰሩ የማይቀር ነው፡፡ ስለዚህ በህይወት እያለ ደግ ደጉን ብቻ አስብ!! ለተንኮሉ ባለቤት አለውና!!
በድጋሚ Amiroo kheyruma yaadi, Sharriin abuma eeydi ብለናል፡፡
----
አፈንዲ ሙተቂ
ጥቅምት 11/2007
በሀረር ከተማ ተጻፈ።