Get Mystery Box with random crypto!

የሀሙስ ዉሎ መርጃዎች 1፤ የኢትዮጵያ መንግሥት እና የኤርትራ ኃይሎች በሰሜናዊ ትግራይ በአራት አ | አድስ ዜና

የሀሙስ ዉሎ መርጃዎች

1፤ የኢትዮጵያ መንግሥት እና የኤርትራ ኃይሎች በሰሜናዊ ትግራይ በአራት አቅጣጫ የተቀናጀ ወታደራዊ ጥቃት ከፍተውብኛል ሲል ሕወሃት መክሰሱን ጠቅሶ ሮይተርስ ዘግቧል። ሆኖም ሮይተርስ የሕወሃትን ክስ በገለልተኛነት ማረጋገጥ እንዳልቻለ ገልጧል። አንድ ሺሬ ከተማ ያሉ የረድዔት ድርጅት ባልደረባ ግን ሺራሮ ከተማ አካባቢ ትናንት ድንበር ዘለል የመድፍ ድብደባ መኖሩን ከአካባቢው ከሄዱ እማኞች መስማታቸውን እንደነገሩት ዘገባው ጠቅሷል። ሮይተርስ የኢትዮጵያ እና ኤርትራ መንግሥታት ቃል አቀባዮች በሕወሃት ክስ ዙሪያ ላነሳቸው ጥያቄዎች ምላሽ እንዳልሰጡት ገልጧል።

2፤ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ደመቀ የመንግሥት የሰላም በሮች ክፍት መሆናቸው እንደተጠበቀ ሆኖ መንግሥት የዜጎቹን ደኅንነት የመጠበቅ ግዴታውን መወጣት ይቀጥላል ሲሉ ዛሬ ለውጭ ዲፕሎማቶች በሰጡት ማብራሪያ ተናግረዋል። ሕወሃት ተኩስ አቁሙን በመጣስ "በግጭት ቀስቃሽ ፕሮፓጋንዳ፣ ሕዝብን ለጦርነት በማንቀሳቀስ እና ሕጻናትን ለውጊያ በመመልመል" ተሰማርቶ ቆይቷል ያሉት ደመቀ፣ አሁንም "መንግሥትን በሐሰት በመወንጀልና በማጥላላት እና የሐሰት የውጊያ ድል በመንዛት ስልቶች" ላይ ተጠምዷል በማለት ከሰዋል። ደመቀ በዚሁ ማብራሪያቸው፣ "አንዳንድ ወገኖች መንግሥትን እና ሕወሃትን በእኩል ዓይን ከማየት እና ግጭቱን ከሚያባብሱ ድርጊቶች እንዲቆጠቡ" አሳስበዋል።

3፤ የኢትዮጵያ መንግሥት ሕወሃት የከፈተውን ወታደራዊ ጥቃት የሚከላከለው የትግራይ "ሕዝብን ከርሃብ የማዳን ግዴታ ስላለበት ነው" ሲል የመንግሥት ቃል አቀባይ ጽሕፈት ቤት ዛሬ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። መንግሥት ሰብዓዊ ዕርዳታ ለትግራይ ሕዝብ እንዲደርስ እና ሕዝቡ ከችጋር እንዲወጣ የማድረግ ግዴታ እንዳለበት መግለጫው አውስቷል። ሕወሃት የመንግሥትን ተደጋጋሚ የሰላም ጥረቶች በገፋበት ሁኔታ ዓለማቀፉ ኅብረተሰብ ቡድኑ ላይ ጫና በማሳደር ፋንታ፣ "ሁለቱ ወገኖች በሚል የሚወጡ መግለጫዎች ተቀባይነት የላቸውም ብሏል መግለጫው። "መከላከያ ኃይላችን በሁሉም አቅጣጫ የተከፈተበትን ወረራ" መመከት እንደሚቀጥል መግለጫው አረጋግጧል።

4፤ የአሜሪካው ውጭ ጉዳይ ሚንስትር አንቶኒ ብሊንከን የኢትዮጵያ መንግሥትና ሕወሃት ባስቸኳይ ጦርነቱን እንዲያቆሙ በትዊተር ገጻቸው ጠይቀዋል። የብሪታንያ የአፍሪካ ጉዳዮች ሚንስትር ቪኪ ፎርድ በበኩላቸው፣ ሕወሃት በኃይል ከያዛቸው የአማራ ክልል አካባቢዎች እንዲሁም የኤርትራ ሠራዊት የትግራይ ከሆኑ ይዞታዎች ለቀው ይውጡ በማለት ዛሬ ባወጡት መግለጫ ጠይቀዋል። አዲስ ያገረሸው ግጭት በሚያስከትለው ሰብዓዊ ቀውስ በርካታ ሰላማዊ ሰዎች እንደሚጎዱና የሰብዓዊ ዕርዳት አቅርቦት ችግሩንም እንደሚያወሳስበው ሚንስትሯ ጠቁመዋል። ሚንስትሯ ሕወሃት በእጁ ያለውን ነዳጅ ለሰብዓዊ ዕርዳታ ሥራ እንዲያውለውና መንግሥትም ለትግራይ የተቋረጡ መሠረተ ልማቶችን እንዲያስጀምር ጭምር ጠይቀዋል።

5፤ ብሄራዊ ባንክ በሰሜኑ ጦርነት ሳቢያ የተበላሹ ብድሮችን ከባንኮች የፋይናንስ ወይም ኦዲት ሪፖርት ላይ አላነሳም ማለቱን ሪፖርተር አስነብቧል። ልማት ባንክና አንዳንድ ንግድ ባንኮች በተለይ ለትግራይ ተበዳሪዎች ያበደሯቸውን የተበላሹ ብድሮች ብሄራዊ ባንክ ለጊዜው ከሒሳብ ሪፖርታቸው እንዲያነሳላቸው ጠይቀው ነበር። ብሄራዊ ባንክ ግን፣ ጥያቄው "በሒሳብ አያያዝ ሕግ ያልተደገፈ ነው" ሲል ለባንኮቹ ምላሽ መስጠቱን ዘገባው አመልክቷል። ልማት ባንክ ብቻ በትግራይ ክልል 10 ቢሊዮን ብር ብድር ተበላሽቶብኛል ያለ ሲሆን፣ የባንኩ የተበላሸ ብድር ምጣኔም 24.3 በመቶ ደርሷል።

6፤ ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ዛሬ በሐረሬ ክልል መጠነ ሰፊ የሞባይል ስልክ አገልግሎት ሙከራ መጀመሩን አስታውቋል። ላንድ ወር በሚቆየው ሙከራ፣ በክልሉ የሚገኙ ደንበኞች በገዟቸው የሳፋሪኮም ሞባይል ስልክ ቁጥሮች የድምጽና የጽሁፍ መልዕክት ወደ ሳፋሪኮምና ኢትዮ ቴሌኮም ስልክ ቁጥሮች መላላክ እንደሚችሉ ኩባንያው ገልጧል። ኩባንያው ደንበኞች የኢንተርኔት አገልግሎት እና ዓላማቀፍ ጥሪዎችን ጭምር መሞከር ይችላሉ ብሏል። የኩባንያው የሐረሬ ክልል የአገልግሎት ሙከራ ከድሬዳዋ ቀጥሎ ሁለተኛው ነው።