Get Mystery Box with random crypto!

አብይ ዜናዎች 1፤ ትናንት እኩለ ሌሊት ላይ በመቀሌ ከተማ የአየር ድብደባ ተፈጽሟል ሲሉ የሕወሃት | አድስ ዜና

አብይ ዜናዎች

1፤ ትናንት እኩለ ሌሊት ላይ በመቀሌ ከተማ የአየር ድብደባ ተፈጽሟል ሲሉ የሕወሃት ቃል አቀባይ ጌታቸው ረዳ በትዊተር ገጻቸው አስታውቀዋል። በጥቃቱ ሦስት ቦምቦች እንደተጣሉ ቃል አቀባዩ ገልጸዋል። ጌታቸው በከተማዋ ላይ ተፈጽሟል ባሉት የአየር ጥቃት በሰው ሕይወት እና ንብረት ላይ ጉዳት ስለመድረሱ ግን ያሉት ነገር የለም። በመንግሥት ኃይሎች እና በሕወሃት መካከል ግጭት በድጋሚ ካገረሸ ወዲህ፣ በመቀሌ የአየር ድብደባ እንደተፈጸመ ሕወሃት ሲገልጽ የአሁኑ ሁለተኛው ነው።

2፤ በአማራ እና ትግራይ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች የተቀሰቀሰውን ጦርነት በመስጋት ወደ መርሳ፣ ኮምቦልቻ እና ደሴ ከተሞች ጉዞ ጀምረው የነበሩ አንዳንድ የወልድያ ከተማ ነዋሪዎች ወደ ቀያቸው መመለስ መጀመራቸውን ለዶይቸቨለ ተናግረዋል። የሰሜን ወሎ ዞን ዋና ከተማ በሆነችው ወልድያ እስከ ትናንት ምሽት መብራት፣ ስልክ እና የባጃጅ ትራንስፖርት አገልግሎት እንዳልተቋረጠ እና በከተማዋ ቅርስ ርቀት ተኩስ እንደማይሰማ ነዋሪዎች ገልጸዋል።

3፤ የተመድ ሰብዓዊ ዕርዳታ ማስተባበሪያ ቢሮ በመንግሥት እና በሕወሃት መካከል አዲስ ባገረሸው ጦርነት ሳቢያ ካለፈው ሳምንት ሐሙስ ጀምሮ ሰብዓዊ ዕርዳታ ለትግራይ ክልል ተረጅዎች ማቅረብ ማቋረጡን አስታውቋል። ቢሮው ያቋረጠው በየብስ ብቻ ሳይሆን በአየር ጭምር ሲያጓጉዝ የቆየውን ዕርዳታ እንደሆነ ገልጧል። ቢሮው በአማራ እና አፋር ክልሎች ነዋሪዎች ጦርነቱን በመስጋት ከቀያቸው እየተፈናቀሉ ስለመሆኑ ያልተረጋገጡ ሪፖርቶች ደርሰውኛል ብሏል።

4፤ ሳፋሪኮም ኩባንያ በድሬዳዋ ለጀመረው የሞባይል አገልግሎት ለድምጽ በደቂቃ 50 ሳንቲም እንደሚያስከፍል ለአል ዓይን ኔትዎርክ በሰጠው ቃል ተናግሯል። የኢንተርኔት አገልግሎት ደሞ 120 ሜጋ ባይት በ10 ብር፣ 900 ሜጋ ባይት በ50 ብር እና ሁለት ጌጋ ባይት በ100 ብር ለደንበኞቹ እየሸጠ እንደሚገኝ ኩባንያው ገልጧል። ኩባንያው እስከ ቀጣዩ ዓመት ሚያዝያ ወር ድረስ የቴሌኮም አገልግሎቱን በ25 ከተሞች እጀምራለሁ ብሏል።

5፤ በደቡብ ሱዳን ሰላም ስምምነት መሠረት የአማጺዎች ተዋጊዎች ከመንግሥት ጦር ሠራዊት ጋር መቀላቀል መጀመራቸውን ዘግበዋል። ሰሞኑን ከ50 ሺህ በላይ የአማጺ ተዋጊዎች ከመንግሥት ጦር ሠራዊት ጋር ተቀላቅለዋል። አማጺያን በሰላም ትጥቅ ፈተው ከመንግሥት ሠራዊት ጋር በመዋሃድ አንድ ብሄራዊ ጦር ሠራዊት እንዲቋቋም ማድረግ ከአራት ዓመት በፊት የተፈረመው የሰላም ስምምነቱ ዋነኛ ግብ ነው። የኢትዮጵያ መከላከያ ሚንስትር አብርሃም በላይ በስነ ሥርዓቱ ላይ ተገኝተዋል።

6፤ የኬንያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ ያሸነፉበት የአገሪቱ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ተጭበርብሯል በማለት ተሸናፊው የቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትሩ ራይላ ኦዲንጋ ያቀረቡትን አቤቱታ ትናንት መስማት ጀምሯል። ሰባት የጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኞች የተሰየሙበት ችሎት፣ የኦዲንጋ ጠበቆችን ከምርጫ ኮሚሽኑ እና ከዊሊያም ሩቶ ጠበቆች ያከራክራል። ችሎቱ በኦዲንጋ አቤቱታ ላይ በመጭው ሰኞ ብይን ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል።