Get Mystery Box with random crypto!

የፌደራል መንግስት እና በአሸባሪነት የተፈረጀው የሸኔ ቡድን በዚህ ሳምንት በታንዛኒያ ይገናኛሉ ሚ | አዲስ ዘይቤ ~ Addis Zeybe

የፌደራል መንግስት እና በአሸባሪነት የተፈረጀው የሸኔ ቡድን በዚህ ሳምንት በታንዛኒያ ይገናኛሉ

ሚያዚያ 16፤ 2015 ዓ.ም.

(አዲስ ዘይቤ፣ አዲስ አበባ) የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ኦነግ ሸኔ እኩለ-ለሊት ላይ በድረ ገፁ እንዳስታወቀው ሶስተኛ ወገን ባለበት ከመንግስት ጋር ለመደራደር ተስማምቷል።

ጠቅላይ ሚኒስተር አብይ አህመድ (ዶ/ር) "ከኦነግ ሸኔ ጋር የሚደረገው ድርድር ከነገ ወዲያ በታንዛኒያ ይጀመራል" ማለታቸውን ተከትሎ ማምሻውን የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ምላሽ ሲጠበቅ ቆይቷል።

ኦ ኤም ኤን ሚዲያ የሰራዊቱ ከፍተኛ አመራር አማካሪ አቶ ጂሬኛ ጉደታ ገለፁልኝ እንዳለው "የታንዛኒያው ቀጠሮ  የመድረክ ማበጀት ሂደት እንጂ የፍሬ ነገር ወይይት አለመሆኑን" ገልፀዋል።

ድርድሩን በዋነኛነት የማመቻቸት ድርሻ እየተወጡ የሚገኙት ሀገራትም ኬንያ እና ኖርዌይ ቢሆኑም የኦነግ አማካሪ ለኦ ኤም ኤን እንደገለፁት ከአሜሪካ እና አውሮፓ ህብረትም ፍላጎት ነበረ።

"ጠቅላይ ሚንስተር አብይ አህመድ ድርድር ይጀምራል በሚል የገለጹበት መንገድ ሂደቱ ካለበት አንጻር ትንሽ የቸኮለ ይመስላል" ሲሉም አቶ ጂሬኛ ጉደታ አክለዋል። በመግለጫው  በጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር ላይ "ኦነግ ሸኔ" በሚል የተጠቀሰው አጠራርንም ክፉኛ ኮንኖታል።

በመግለጫውም "የድርጅታችን ስም የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ሲሆን ሌላ ማንኛውም ስያሜ የተሳሳተ እና ማንነታችንን እና አላማችንን ለማሳሳት የሚደረግ ሙከራ ነው" በማለት ስያሜውን አውግዟል።

በኦሮሚያ የተለያዩ ዞኖች የሚንቀሳቀሰውን የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት  ኦነግ ሸኔ በሚል በሽብርተኝነት መፈረጁ ይታወሳል። በዚህ ወቅት የትግራይ ህዝቦች ነጻነት ግንባር (ትህነግ) በሽብርተኝነት የተፈረጀ ቢሆንም የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት ተከትሎ ከሽብርተኝነት መዝገብ መሰረዙ ይታወቃል።