Get Mystery Box with random crypto!

የመቀሌ ከተማ ነዋሪዎች የውኃ ችግር እንዳጋጠማቸው ገለፁ የውኃ ክፍል ሠራተኞች ወደ ጦርነት መሄዳ | አዲስ ዘይቤ ~ Addis Zeybe

የመቀሌ ከተማ ነዋሪዎች የውኃ ችግር እንዳጋጠማቸው ገለፁ

የውኃ ክፍል ሠራተኞች ወደ ጦርነት መሄዳቸውን ተከትሎ የባለሙያ እጥረት ማጋጠሙ ተጠቁሟል

ሚያዝያ 05፤ 2015 ዓ.ም.

(አዲስ ዘይቤ፤ መቀሌ) በትግራይ ክልል በተለይም በመዲናዋ መቀሌ ከተማ የከፋ የንፁህ መጠጥ ውኃ እጥረት እየተቸገሩ መሆኑን የከተማዋ ነዋሪዎች ለአዲስ ዘይቤ ተናገሩ። በችግሩ ሳቢያ ነዋሪዎች የምንጭ ውኃ ለመጠቀም የተገደዱ ሲሆን ይህም ለእንግልት፣ ላልተገባ ወጭ እና ለህመም መጋለጣቸውን ጠቁመዋል።

ወ/ሮ ሃረግ ይልማ የመቀሌ ከተማ ነዋሪ ናቸው፣ የምንጭ ውኃ ለመቅዳት ወረፋ እየጠበቁ ከአዲስ ዘይቤ ጋር ቆይታ አድርገዋል። “በውኃ እጥረት ምክንያት ትልቅ ችግር ደርሶብናል፤ ልጆች ይዘን ያለ ውኃ ቀናትን ማሣለፍ ከባድ ሆኖብናል” ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

የወ/ሮ ሃረግን ችግር የሚጋሩ በርካታ የመቀሌ ከተማ ነዋሪዎች ችግሩ የከፋ መሆኑን ጠቁመው የሚመለከተው አካል መፍትሄ እንዲያፈላልግላቸው ለአዲስ ዘይቤ ቅሬታቸውን ገልፀዋል። አቶ ገብረዮሃንስ ወልደስላሴ የመቀሌ ከተማ ኩኋ ክፍለከተማ የውሃ አገልግሎት ኃላፊ ናቸው።

የውሃ አገልግሎት በሰፊው ችግር ውስጥ ነው የሚሉት ኃላፊው፣ የአገልግሎቱ ሰራተኞች ወደ ጦርነት በመግባታቸው የሰራተኛ እጥረት ማጋጠሙን ተናግረዋል። ከባለሙያ እጥረት ባለፈ ውኃ ሙሉ ለሙሉ ለማዳረስ የመሳሪያ ችግር መኖሩን ገልፀዋል።

ላለፉት ሁለት ዓመታት አገልግሎት ባይቋረጥም ሙሉ አገልግሎት ሳይሰጥ መቆየቱን የሚገልፁት አቶ ገብረዮሃንስ አሁን ላይ በአገልግሎት ሂደት ብልሽት ሲያጋጥም ለማስተካከል ብዙ ጊዜ እንደሚወስድ ይገልፃሉ። አሁን የተመሰረተው የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር በዚህ ጉዳይ በሰፊው መስራት እንደሚገባው ኃላፍው ከአዲስ ዘይቤ ባደረጉት ቆይታ ተናግረዋል።