Get Mystery Box with random crypto!

በጉራጌ ዞን የሚገኙ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቅርንጫፎች በመዘጋታቸዉ ገንዘባቸውን ማንቀሳቀስ እንዳል | አዲስ ዘይቤ ~ Addis Zeybe

በጉራጌ ዞን የሚገኙ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቅርንጫፎች በመዘጋታቸዉ ገንዘባቸውን ማንቀሳቀስ እንዳልቻሉ ነዋሪዎች ተናገሩ

ነሐሴ 27 ፤ 2014 ዓ.ም.

(አዲስ ዘይቤ:ሐዋሳ) በጉራጌ ዞን በሚገኙ ወረዳዎች እና ከተማዎች ለሁለት ቀናት ከተደረገዉ የስራ ማቆም እና የቤት ዉስጥ የመቀመጥ አድማ ወዲህ በዞኑ የሚገኘው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቅርንጫፎች መዘጋታቸዉን የአካባቢው ነዋሪዎች ተናግረዋል።

በዚህም በወልቂጤ ከተማ እንዲሁም በሌሎች ወረዳዎች ከሰኞ ነሐሴ 23 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቅርንጫፎች አገልገሎት እየሰጡ ባለመሆናቸዉ ገንዘባቸውን ማንቀሳቀስ እንዳልቻሉ ገልፀዋል።

ለአዲስ ዘይቤ ስለ ጉዳዩ ሁኔታውን ያስረዱት የወልቂጤ ከተማ ነዋሪ አቶ አንዋር ዩሱፍ "ባንኩ ያለ ቅድመ ማስጠንቀቂያ ከሰኞ ጀምሮ ዝግ በመሆኑ ገንዘባችንን ማንቀሳቀስ አልቻልም። በዚህ ምክንያት ዩኒቨርስቲ ለሚገኘዉ ልጄ ገንዘብ ለመላክ ሌላ ባንክ ለመጠቀም ተገድጃለሁ" በማለት ይናገራሉ። በተጨማሪም የመንግሥት ሰራተኞች ደሞዛቸው የሚገባዉ በንግድ ባንክ በኩል ቢሆንም ዝግ በመሆኑ መቸገራቸውን አንስተዋል።

በዞኑ በሚገኙ ወረዳዎችም በተመሳሳይ ሁኔታ የባንኩ ቅርንጫፎች ዝግ በመሆናቸው ተጠቃሚዎች ፊታቸውን ወደ "ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ" ማድረጋቸዉን ሰምተናል።

በምሁር አክሊል ወረዳ የሚገኙ ነዋሪዎች በሰጡን አስተያየት “ወቅቱ የበዓል ሰሞን ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በስራ ምክንያት በሀገሪቱ ተበታትነዉ የሚገኙ የአካባቢው ተወላጆች በሚሰባሰቡበት ወቅት ገንዘባቸውን በአብዛኛው የሚለዋወጡበት በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መዘጋቱ አግባብ አይደለም" ብለዋል።

አዲስ ዘይቤ በጉዳዩ ዙሪያ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዋናው መስሪያ ቤት ለማናገር ያደረገችዉ ጥረት አልተሳካም።
@AddisZeybe