Get Mystery Box with random crypto!

'ኹለቱም ወገኖች' በሚል የሚወጡ መግለጫዎች ከእውነታው ያፈነገጡ በመሆናቸው ተቀባይነት የላቸውም።' | Addis Maleda - አዲስ ማለዳ

"ኹለቱም ወገኖች" በሚል የሚወጡ መግለጫዎች ከእውነታው ያፈነገጡ በመሆናቸው ተቀባይነት የላቸውም።"፦ የመንግሥት ኮሚኒኬሽን አገልግሎት

ሐሙስ ነሐሴ 26 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) "ኹለቱም ወገኖች" በሚል የሚወጡ መግለጫዎች ከእውነታው ያፈነገጡ በመሆናቸው ተቀባይነት የላቸውም ሲል የመንግሥት ኮሚኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ።

የመንግሥት ኮሚኒኬሽን አገልግሎት ዛሬ ባወጣው መግለጫ፤ "በሕወሓት ቡድን እየደረሱ የሚገኙ ጥፋቶችን ለማስቆም መንግሥት ለሰላማዊ አማራጭ ያደረጋቸው ጥረቶች ኹሉ እየመከኑ ባሉበት ሁኔታ፣ አሸባሪውን ሕወሐት መጫን ሲገባቸው "ኹለቱም ወገኖች" በሚል የሚወጡ መግለጫዎች ከእውነታው ያፈነገጡ በመሆናቸው ተቀባይነት የላቸውም።" ሲል ገልጿል።

ሕወሓት ተደጋጋሚ የሰላም ጥሪዎችን ገፍቶ በየአቅጣጫው በለኮሰው እና ዛሬም እያስፋፋ ባለው እሳት ንጹሐን እየተገደሉ ነው፣ ሕዝብ እየተፈናቀለ፣ ንብረትም እየወደመ እንደሚገኝም አስታውቋል።

"አሁን እንደሚታየው ሕወሓት ከአገር አጥፊነት ተግባሩ የማስቆም ግዴታ በኢትዮጵያ መንግሥትና ሕዝብ ላይ ወድቋል።" ያለው አገልግሎቱ፤ የዚህንም ምክንያት እንደሚከተለው በዝርዝር አስቀምጧል፦

=> የሽብር ቡድኑ ሰላማችንን እንዳያደፈርስና አገራችንን እንዳያፈርስ መከላከል ስለሚገባ፤

=> ሕወሓት ወደ ትግራይ የሚላከውን እርዳታ ለተቸገረው ሕዝብ እንዳይደርስ፣ በተቃራኒው እርዳታው ለጦርነት እንዲውል እያደረገ በመሆኑ መንግሥት እርዳታው ለተረጂው ሕዝብ እንዲደርስና ትግራይ ውስጥ ምቹ ኹኔታ በመፍጠር ሕዝቡን ከችግር የመከላከል ግዴታ ስላለበት፤

=> ሕወሓት በእኩይ ተግባሩ ሕዝብን በረሃብ ለመቅጣት ዐቅዶ ተደጋጋሚ ጦርነት የሚከፍተው በክረምት የግብርና ወቅት በመሆኑ፤ መንግሥት ወረራውን እየተከላከለ ያለው ሕዝብን ከረሃብ የማዳን ግዴታ ስላለበት ጭምር ነው። ሲል ገልጿል።

በመሆኑም ሕወሓት ተደጋጋሚ የሰላም አማራጮችን በመግፋት የከፈተው ጥቃት አገራችንን እንዳይበትን፣ የመከላከያ ኃይላችን በኹሉም አቅጣጫ የተከፈተበትን ወረራ ከሰላም ወዳዱ ደጀን ሕዝብ ጋር በመሆን በጽኑ ጀግንነት በመከላከል ላይ እንደሚገኝ የመንግሥት ኮሚኒኬሽን አገልግሎት በመግለጫው አስታውቋል።
_____
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n