Get Mystery Box with random crypto!

ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ በሐረሪ ክልል መጠነ-ሰፊ የደንበኞች የኔትወርክ ሙከራ መጀመሩን አስታወቀ ሐሙስ | Addis Maleda - አዲስ ማለዳ

ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ በሐረሪ ክልል መጠነ-ሰፊ የደንበኞች የኔትወርክ ሙከራ መጀመሩን አስታወቀ

ሐሙስ ነሐሴ 26 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ መጠነ-ሰፊ የደንበኞች የኔትወርክ ሙከራውን በሐረሪ ክልል መጀመሩን በዛሬው ዕለት አሳውቋል።

ይህ የደንበኞች የሙከራ ምዕራፍ ኩባንያው በአገር አቀፍ ደረጃ አገልግሎቱን ለመስጠት ከሚዘጋጅበት ጊዜ አስቀድሞ በተለያዩ ክልሎች እና ከተሞች የኔትወርክ እና የአገልግሎት ጥራቱን በተጠናከረ ሁኔታ የሚፈትሽበት ወቅት መሆኑን ገልጿል።

በሐረሪ ክልል የደንበኞች የኔትወርክ ሙከራ፤ በ2G፣ 3G እና 4G ኔትወርኮች የሚካሔድ ሲሆን ደንበኞች በዐ7 በሚጀምረው የሳፋሪኮም ኢትዮጵያ መስመር የስልክ ቁጥሮቻቸውን መርጠው ሲም ካርድ መግዛት እንደሚችሉም ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ አስታውቋል።

ደንበኞች የሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ሲም ካርዶችን የሳፋሪኮም ኢትዮጵያ መለያ ከተለጠፈባቸው መደብሮች እና ሱቆች ማግኘት የሚችሉ ሲሆን፤ ኔትወርኩን ለአንድ ወር ያህል እንዲሞክሩት የሚረዳ የደንበኝነት ማስጀመሪያ የዳታ፣ የድምጽ እና የጽሁፍ መልዕክቶች ጥቅል እንደሚያገኙ ተገልጿል።

የደንበኝነት ማስጀመሪያ ጥቅሉ በሚያልቅበት ጊዜ ደንበኞች የአየር ሰዓት ከሽያጭ ማዕከላት ወይም መለያ ከተለጠፈባቸው መደብሮች እና ሱቆች በመግዛት መሙላት እና አገልግሎቱን መቀጠል ይችላሉም ተብሏል።

በሐረሪ ክልል አገልግሎት በሚጀምረው የሳፋሪኮም ኢትዮጵያ የሙከራ ኔትወርክ፤ ደንበኞች ዳታ መጠቀም፣ ጥሪዎች እና የጽሁፍ መልዕክቶችን ከሳፋሪኮም ኢትዮጵያ እና ከኢትዮ ቴሌኮም ደንበኞች ጋር መለዋወጥ እንዲሁም የዓለም አቀፍ ጥሪዎችን ማድረግ እንደሚችሉ ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ገልጿል።
_
#አዲስ_ማለዳ