Get Mystery Box with random crypto!

ዕለታዊ ዜናዎች 1፣ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ትናንት የክልሉን አማካሪ ምክር ቤት አቋቁሟል። | አዲስ ነገር መረጃ

ዕለታዊ ዜናዎች

1፣ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ትናንት የክልሉን አማካሪ ምክር ቤት አቋቁሟል። የአማካሪ ምክር ቤቱ ሚና፣ በክልሉ በሕዝብ የተመረጠ ዲሞክራሲያዊ መንግስት እስኪቋቋም የኅብረተሰቡን ችግሮች፣ ፍላጎቶችና ጥያቄዎች  ለጊዜያዊ አስተዳደሩ ማቅረብ እንደኾነ ተገልጧል። ዘጠኝ ተቃዋሚ ፓርቲዎችና ሲቪክ ማኅበራት፣ አማካሪ ምክር ቤቱ ጊዜያዊ አስተዳደሩን የመቆጣጠር ሥልጣን ኖሮት እንዲቋቋም ከትናንት ወዲያ ባወጡት የጋራ መግለጫ ጠይቀው ነበር።

2፤ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ደንበኞቹ ወርሃዊ የኤክትሪክ ፍጆታ ሂሳባቸውን በአዋሽ ባንክ አማካኝነት እንዲከፍሉ የሚያስችል ስምምነት ከባንኩ ጋር ትናንት ተፈራርሟል። ተቋሙ ከባንኩ ጋር ስምምነቱን የፈረመው፣ ደንበኞች እስካኹን ከሚጠቀሙባቸው የክፍያ አማራጮች በተጨማሪ፣ ሌላ የክፍያ ሥርዓት እንዲያገኙ እንደኾነ ገልጧል። የአዋሽ ባንክ ዲጂታል የክፍያ ሥርዓት ከኹሉም ባንኮች ጋር የተሳሰረ ነው ተብሏል። አገልግሎቱ፣ ካኹን ቀደም ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክና ኢትዮ ቴሌኮም ጋር የክፍያ አማራጭ ሥርዓቶችን መዘርጋቱ ይታወሳል።

3፤ ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ ርስበርስ የመዋጋት፣ የመግዳደልና የማውደም አዙሪት ካልተበጠሰ ዘላቂ የሰላም ግንባታ ሊሳካ እንደማይችል ተናግረዋል። ፕሬዝዳንቷ ይህን የተናገሩት፣ የተመድ የሰላም ግንባታ ኮሚሽን ልዑካን ቡድን አባላትን በቤተ መንግሥት ትናንት ተቀብለው ባነጋገሩበት ወቅት ነው። በውይይቱ ወቅት፣ የሠላም ግንባታ አካታችና የማኅበረሰቡን ፍላጎት ያገናዘበ ሊኾን እንደሚገባም ፕሬዝዳንቷ ጠቁመዋል። የተመድ የሰላም ግንባታ ልዑክ አዲስ አበባ የገባው፣ በተመድና አፍሪካ ኅብረት የጋራ ስብሰባ ላይ ለመሳተፍ ነው።

4፤ የትውልደ ኢትዮጵያዊቷ ሰዓሊ ጁዲ ምኅረቱ አንድ ስዕል በአፍሪካዊያን ሰዓሊዎች ታሪክ ክብረ ወሰን ነሰበረ 10 ነጥብ 7 ሚሊዮን ዶላር የጨረታ ዋጋ ተሽጧል። ጁድ "ዎከርስ ዊዝ ዘ ዶን ኤንድ ሞርኒንግ" የተሰኘውን ስዕል የሳለችው፣ ከ18 ዓመታት በፊት በውቂያኖስ ማዕበል ለተመታችው የአሜሪካዋ ኒው ኦርሊንስ ከተማ ለተዘጋጀ ኤግዚቢሽን ነው። ጁዲ ባለፈው ወር በ9 ነጥብ 3 ሚሊዮን ዶላር የተሸጠው ሌላ ስዕሏም፣ በአፍሪካዊያን ሰዓሊዎች የስዕል ሽያጭ ታሪክ ክብረ ወሰን የሰበረ ነበር።

5፤ የኬንያ መንግሥት 1 ሺህ ጸጥታ አስከባሪ ፖሊሶችን በነውጠኛ የተደራጁ ቡድኖች በምትናጠው ሐይቲ ለማሠማራት ያሳለፈውን ውሳኔ ፓርላማው አጽድቆለታል። ከፍተኛው ፍርድ ቤት በበኩሉ፣ መንግሥት ፖሊስ ኃይሉን እንዳይልክ የጣለውን ጊዜያዊ እገዳ እንደገና በማራዘም፣ በጥር አጋማሽ ውሳኔ ለመስጠት ቀጥሯል። የተመድ ጸጥታው ምክር ቤት፣ ኬንያ በሐይቲ የሚሠማራ ዓለማቀፍ ጸጥታ አስከባሪ ኃይል ለመምራት ያቀረበችውን ጥያቄ ቀደም ብሎ አጽድቋል። የፍርድ ቤቱ ሂደት ግን፣ የውሳኔውን ተግባራዊነት ሊያዘገየው እንደሚችል ተገምቷል።
via [ዋዜማ]

@Addis_News