Get Mystery Box with random crypto!

በመቀሌ የሚገኙ ጋዜጠኞች በደረሰባቸው ከፍተኛ ድብደባ ክፉኛ መጎዳታቸውን ገለጹ በትግራይ ክልል | አዲስ ነገር መረጃ

በመቀሌ የሚገኙ ጋዜጠኞች በደረሰባቸው ከፍተኛ ድብደባ ክፉኛ መጎዳታቸውን ገለጹ


በትግራይ ክልል የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ባለፈው ጳጉሜ ወር በመቀሌ ከተማ ጠርተውት ከነበረው ሰልፍ ጋር ተያይዞ፤ ለዘገባ በሥፍራው የተገኙ የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች በደረሰባቸው ከፍተኛ ድብደባ ክፉኛ መጎዳታቸውን ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

በሥፍራው ከተገኙት ጋዜጠኞች መካከል በአክሱም ዩኒቨርሲቲ የሕግ መምህር እና ከያበላ ሚዲያ መስራቾች አንዱ መሆናቸውን የገለጹት ተሻገር ፅጋብ፤ “ሰልፉ ይደረግበታል ወደተባለው ሮማናት አደባባይ በማቅናት በእጅ ስልኬ የተወሰነ ተንቀሳቃሽ ምስል ለመያዝ ስሞክር “ቲዲኤፍ” ተብለው የሚጠሩ ኃይሎች ስልኬን ተቀብለው በያዙት ዱላ በመምታት ከጥቅም ውጪ አድርገውታል፡፡” ብለዋል።

አክለውም “በደረሰብኝ ከፍተኛ ድብደባ ራሴን ስቼ ወድቄ ነበር፡፡” ያሉት ተሻገር፤ “ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ሰሜን ክፍለ ከተማ ወደሚገኘው እስር ቤት ወሰዱኝ፡፡” ሲሉ ገልጸዋል፡፡

“እስር ቤት ከገባሁ በኋላም ወደ ዓይደር ሪፈራል ሆስፒታል ሪፈር የተጻፈልኝ ቢሆንም፤ ‘የጥበቃ ኃይል የለንም’ በማለት ፈቃደኛ ሳይሆኑ በመቅረታቸው ከፍተኛ የሆነ ደም ፈሶኛል፡፡” ብለዋል።

እስር ቤት ውስጥ በተፈጸመባቸው ከፍተኛ ድብደባም ዓይናቸው፣ ጭንቅላታቸው እንዲሁም እጅና እግራቸው ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን ገልጸው፤ ሕክምና እየተከታተሉ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም በአያም ሚዲያ ጋዜጠኛ የሆነው መሐሪ ሰሎሞን በበኩሉ፤ ተመሳሳይ ጥቃት እንደደረሰበት በመናገር “በሌሎች እስረኞች ላይም የሚፈጸመው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ከፍተኛ ነው፡፡” ብሏል።

በሰዓቱ በሌሎች ጋዜጠኞች ላይም ድብደባ እና ማዋከብ ሲፈጸም ማየቱን አውስቷል።

የደረሰባቸውን አካላዊ እና ስነልቦናዊ ጉዳት አስመልክቶም በሕግ ለመጠየቅ በዝግጅት ላይ እንደሚገኙ ጋዜጠኞቹ ጠቁመዋል።

ዓለም አቀፉ የጋዜጠኞች መብት ጥብቃ ተሟጋች ኮሚቴ ሲፒጄ በትግራይ የተቃውሞ ሰልፍ ሊዘግቡ የወጡ ሶስት ጋዜጠኞችን ፖሊሶች ደብድበው አስረዋል ሲል ከቀናት በፊት ባወጣው መግለጫ ማስታወቁ ይታወሳል፡፡

ሲፒጄ በመግለጫው “መለዮ የለበሱ ፖሊሶች አስቁመው በዱላ እና በኮረንቲ ገመድ እንደመቷቸው ጋዜጠኞቹ ገልጸውልኛል” ያለ ሲሆን፤ “በጋዜጠኞቹ ላይ የደረሰው ድብደባ በትግራይ ያሉ ባለስልጣናት ሪፖርተሮች መንግሥትን የሚተቹ ጉዳዮችን እንዲዘግቡ እንደማይፈልጉ አሳዛኝ መልዕክት የሚያስተላልፍ ነው፡፡” ሲል ገልጿል፡፡

@Addis_News