Get Mystery Box with random crypto!

በባቱ (ዝዋይ) ከተማ በመንግሥት የጸጥታ አካላትና በ'ሸኔ' ታጣቂዎች መካከል በተደረገ የተኩስ  ል | አዲስ ነገር መረጃ

በባቱ (ዝዋይ) ከተማ በመንግሥት የጸጥታ አካላትና በ"ሸኔ" ታጣቂዎች መካከል በተደረገ የተኩስ  ልውውጥ የአራት ሰዎች ሕይወት ማለፉ ተሰማ

በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን ባቱ (ዝዋይ) ከተማ እሁድ ሰኔ 4/2015 ዕለት ከሌሊቱ አምስት ሰዓት አካባቢ በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች እና ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ብሎ የሚጠራውና በመንግሥት ኦነግ ሸኔ ተብሎ በአሸባሪነት በተፈረጀው ታጣቂ ቡድን መካከል በተደረገ ከፍተኛ የተኩስ ልውውጥ የአራት ሰዎች ሕይወት ማለፉን የአካባቢው ነዋሪዎች ገልጸዋል፡፡

ከሟቾቹ መካከል አንዲት ሴትን ጨምሮ ሦስቱ የመንግሥት የጸጥታ አካላት መሆናቸው የተገለጸ ሲሆን፤ አንዱ ደግሞ ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ብሎ የሚጠራው ታጣቂ ቡድን አባል ነው ተብሏል።

የተገደለው የሸኔ ታጣቂ ቡድን አባል እግሩን ተመትቶ መሸሽ ባለመቻሉ፤ የታጣቂ ቡድኑ አባላት መረጃ እንዳያወጣ በማለት ገድለውት እንደሸሹ ተጠቁሟል።

ለተከታታይ ኹለት ሰዓታት በላይ ሲደረግ ነበር የተባለው የተኩስ ልውውጥ፤ ዓላማው እስረኛ ለማስፈታት እንደሆነ ተገልጿል።

እስር ቤቱ በተለምዶ ሀይቅ ዳር ወይም የቀድሞ ጤና ጣቢያ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ እንደሚገኝ እና ታጣቂዎቹ ከዚህ ቀደምም በእስር ቤቱ የታሰረባቸውን አባል ለማስፈታት ጥረት ሲያደረጉ የሰዎች ሕይወት ማለፉን ነዋሪዎቹ አውስተዋል።

የሸኔ ታጣቂ ቡድን አባላት ቡልቡላ እና ቱሉ መካከል በተለምዶ ኦኢቱ በምትባል ስፍራ መሽገው እንደሚገኙ የገለጹት ነዋሪዎቹ፤ እስረኞቻቸውን ለማስፈታትም የዝዋይን ሀይቅ በጀልባ እየቀዘፉ መጥተው ጀልባቸውን ጦጣ ወንዝ ተብሎ በሚጠራው ስፍራ እንዳቆሙ አብራርተዋል፡፡

አክለውም፤ እሁድ ሌሊት በተካሄድው የተኩስ ልውውጥ የታሰሩ የታጣቂ ቡድኑን አባላት ለማስፈታት የተደረገው መኩራ አለመሳካቱን በመጥቀስ፤ "የታጣቂ ቡድኑ አባላት አሉ ወደተባለበት ኦኢቱ አካባቢ የመንግሥት የጸጥታ አካላት በተደጋጋሚ ቢያቀኑም በሕይወት ተርፈው የሚመለሱት ጥቂቶች ናቸው።" ሲሉም ተደምጠዋል።

ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ብሎ የሚጠራው እና በመንግሥት ኦነግ ሸኔ ተብሎ በአሸባሪነት የተፈረጀው ታጣቂ ቡድን በአካባው መንቀሳቀስ ከጀመረ ቆይቷል የተባለ ሲሆን፤ በአካባቢው ነዋሪዎች ላይ ከባድ ቀውስ እያሳደረ እንደሚገኝም ተመላክቷል።

@Addis_News
@Addis_News