Get Mystery Box with random crypto!

===ቀልዶች በጃንሆይ ዙሪያ=== አፈንዲ ሙተቂ -------- እስቲ ዛሬ ደግሞ ልዑል ተፈሪ መኮንን | 👑 አዳም ረታ 👑

===ቀልዶች በጃንሆይ ዙሪያ===
አፈንዲ ሙተቂ
--------
እስቲ ዛሬ ደግሞ ልዑል ተፈሪ መኮንን “ግርማዊ ጃንሆይ” ከሆኑ በኋላ የተቀለደባቸውን ቀልዶች እናካፍላችሁ፡፡
------------
ሁለት ሰዎች እየተጨዋወቱ ነው፡፡ አንዱ ጃንሆይን ይወዳል፡፡ አንዱ ጃንሆይን ይጠላል፡፡ ጃንሆይን የሚወደው ሰውዬ “ግርማዊ ጃንሆይ ሺ ዓመት ይንገሡ” አለ፡፡ ጃንሆይን የሚጠላው ሰውዬ በጥፊ ከመታው በኋላ እንዲህ አለው፡፡
“አንተን ብሎ እድሜ ቆራጭ! ግርማዊ ጃንሆይ ለዘላለም ይንገሡ አትልም ነበር?”
------------
ግርማዊ ጃንሆይ የአማኑኤል ሆስፒታልን ሊጎበኙ ሄዱ፡፡ አንዱ ሻል ያለው እብድ እንዳያቸው ተጠጋቸውና “ማን ትባላለህ?” አላቸው፡፡
“ሞአ አንበሳ ዘእም ነገደ ይሁዳ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሤ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ ነን” አሉት ጃንሆይ፡፡
ይህንን የሰማው እብድ ሳቅ እያለ “ጉድ ነው! እኔንም እብደት ሲጀምረኝ እንዲህ ነበር ያደረገኝ” አላቸው፡፡
(በርሱ ቤት ጃንሆይ ሊታከም የመጣ እብድ መስሎታል)
------------
እነ ኒል አርምስትሮንግ ጨረቃን ረገጡና ዓለም ጉድ አለ፡፡ የዓለም መሪዎች ወደ ፕሬዚዳንት ሊንደን ቢ ጆንሰን የደስታ መልዕክት ማጉረፍ ጀመሩ፡፡ እንደ አጋጣሚ አሜሪካ የነበሩት ቀዳማዊ ኃይሥላሴም እንዲህ አሉ፡፡
“ጨረቃ ላይ በመውጣት የሰራችሁት ስራ ለናንተ ብቻ ሳይሆን ለዓለም ህዝብም ኩራት ነው፡፡ በሚቀጥለው ጊዜ ደግሞ ተመራምራችሁ ጸሐይ ላይ እንደምትወጡ መልካሙን ሁሉ እንመኝላችኋን”፡፡
ከጃንሆይ አጠገብ የነበሩት ልጅ ይልማ ዴሬሳ ደነገጡ እና “ጃንሆይ ጸሐይ ላይ መውጣት አይቻልም እኮ” አሏቸው፡፡ ጃንሆይም በስጨት ብለው “አንተ ደግሞ አቃቂር ታበዛለህ! እኛ መናገር እንጂ ስለሌላው ምን አገባን? ቢፈልጉ ጸሐይቱ እንዳታቃጥላቸው ማታ ማታ ይጓዙና ይውጡ!”
------------
የዩጎዝላቪያው ማርሻል ቲቶ ኢትዮጵያን ጎብኝተው ካበቁ በኋላ ለጃንሆይ “ሀገራችሁ ጥሩ ናት። ግን ሰዎቻችሁ በየጎዳናው ይሸናሉ” አሏቸው። በሌላ ጊዜ ጃንሆይ ዩጎዝላቪያን እየገበኙ ሳለ በጎዳና ላይ የሚሸና ሰው አዩ። በዚህን ጊዜም ወደ ሰውዬው እያመለከቱ ለማርሻል ቲቶ “ተመልከት! ያንተም ሰዎች በመንገድ ላይ ይሸናሉ” አሏቸው። ቲቶ በጣም ተናደዱ። ወታደሮችን ጠርተው “እዚያ ወዲያ የሚሸናውን ሰውዬ ይዛችሁ ወደኔ አምጡት” በማለት አዘዟቸው። ወታደሮቹ ሰውዬው አጠገብ ከደረሱ በኋላ ባዶ እጃቸውን ተመለሱ።ቲቶም “ለምን አልያዛችሁትም?” አሉ።
“ይቅርታ ማርሻል የዲፕሎማቲክ መብቱን መድፈር አልቻልንም”
“የምን የዲፕሎማቲክ መብት?”
“ሰውዬው አምባሳደር ነው”
“የየት ሀገር አምባሳደር?”
“የኢትዮጵያ”
---------
ጃንሆይ እና ጸሓፌ ትዕዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድ ከተማ ወርደው መዝናናት አማራቸውና ተያይዘው ወጡ። የተቻለውን ያህል ጥንቃቄ እያደረጉ ሲዝናኑ ከቆዩ በኋላ መሸ። በፒያሳ በኩል ወደ ቤተ መንግሥት በመመለስ ላይ ሳሉ ሲኒማ ኢትዮጵያ ደረሱ። “እስቲ እዚህም ገብተን ትንሽ እንይ” አሉና ወደ ሲኒማው ገብተው ከተመልካቾች ተርታ ተቀመጡ።
በዚያ ዘመን ቴሌቭዥን በየቤቱ ስለሌለ ህዝቡ ወደ ሲኒማ ሄዶ ነው ዜና የሚከታተለው። በዜና ላይ ጃንሆይ የታዩ እንደሆነ ደግሞ ማጨብጨብ የዘመኑ ደንብ ነው። ታዲያ ዜና አንባቢው “ግርማዊ ጃንሆይ ዛሬ የጃፓን አምባሳደርን የሹመት ደብዳቤ ተቀበሉ” አለና ዜናውን በምስል አቀረበው። ይሄኔ በአዳራሹ የነበረው ጠቅላላ ህዝብ አጨበጨበ። አሁንም ሌላ የጃንሆይ ዜና ቀረበ። ህዝቡም አጨበጨበ። ሌላ የጃንሆይ ዜና ተከተለ። ህዝቡ አፍታ በአፍታ ማጨብጨቡን ቀጠለ። ጃንሆይና ጸሓፌ ትዕዛዝ ግን አላጨበጨቡም። ይህንን ያየ አንድ ጎልማሳ ተመልካች ወደ ጃንሆይ ተጠግቶ “ሽሜ! ጉድ ሳይፈላብሽ ብታጨበጭቢ ይሻልሻል” አላቸው።
---------

@wegoch
@wegoch
@paappii