2022-04-25 09:57:05
~ ዘካቱል ፊጥር ~
ክፍል አንድ
ዘካቱል ፊጥር የረመዷን ፆም በሚጠናቀቅበት ወቅት ግዴታ የሚሆን የዘካ አይነት ነው።ዘካቱል ፊጥር ሙስሊም በሆነ ባሪያም ይሁን ነፃ፣ወንድም ይሁን ሴት፣ህፃንም ይሁን ትልቅ ላይ ግዴታ ተደርጓል።ይህን አስመልክቶ እንዲህ የሚል ሐዲስ ተዘግቦ እናገኛለን: —
عن ابن عمر قال" فرض رسول الله ﷺ زكاة الفطر صاع من تمر أو صاع من شعير على العبد والحر،والذكر والأنثى، والصغير والكبير،من المسلمين" (متفق عليه)
" መልዕተኛው ﷺ ዘካተል ፊጥርን ከተምር ወይም ከገብስ አንድ ቁና ከሙስሊሞች በባሪያውም በነፃውም፣ በወንዱም በሴቱም፣በትንሹም በትልቁም ላይ ግዴታ አድርገዋል" ( ቡኻሪና ሙስሊም ዘግበውታል)
በሐዲሱ ላይ በግልፅ እንደተቀመጠው ዘካቱል ፊጥር በሚከተሉት ሰዎች ላይ ግዴታ ይሆናል:—
① ባሪያዎች እና ነፃ የሆኑ ሰዎች ላይ
ባሪያ ከሆነ እራሱ የሚያንቀሳቅሰው ገንዘብ ስለማይኖረው ዘካውን የማውጣት ግዴታ በሐላፊው ላይ ይሆናል።ባሪያ ያልሆነ ሰው ደሞ ከራሱ ገንዘብ ዘካውን የሚያወጣ ይሆናል።
②ወንድ እና ሴት
ዘካቱል ፊጥር ፆታ የሚለይበት ኢባዳ አይደለምና በሴቱም በወንዱም ላይ ግዴታ ይሆናል።ሴት ልጅ ብር ካላት ለራሷ ታወጣለች ከሌላት ደግሞ ልጅ ስትሆን በወላጆቿ፣ ሚስት ስትሆን ደሞ በበሏ ላይ ግዴታ ይሆናል።
③ሕፃናት እና ትላልቅ ሰዎች
ዘካቱል ፊጥር እድሜም የማይገድበው በትንሹም በትልቁም ላይ ግዴታ የሆነ ትልቅ ኢባዳ ነው።ሕፃናት ገንዘብ ካላቸው ከራሳቸው ገንዘብ ዘካውን እናወጣላቸዋለን፤ ከሌላቸው ደሞ የነሱን ሌሎች መሰረታዊ ወጪዎችን የመሸፈን ሐላፊነት ያለበት ሰው ( ለምሳሌ: ወላጆች) ላይ ይሆናል ግዴታው።ለሕፃናት ዘካቱል ፊጥርን ማውጣት ግዴታ ሲሆን ለተፀነስ ልጅ ዘካውን ማውጣት ግን ግዴታ ሳይሆን የተወደደ ተግባር ነው።ይህም ተግባር( ለፅንስ ዘካተል ፊጥርን ማውጣት) ከኸሊፋው ዑስማን ቢን ዐፋን ተገኝቷል።
ማሳሰቢያ
✘ በአሁኑ ጊዜ ያሉ በደሞዝ ተስማምተው የሚሰሩ የቤት ሰራተኞች ባሪያ የሚለው ውስጥ የሚካተቱ አይደሉምና ለነሱ ዘካ የማውጣት ግዴታ አሰሪያቸው ላይ የለበትም።ዘካውን እራሳቸው ከደሞዛቸው ማውጣት ይኖርባቸዋል።አሰሪው ግን በራሱ ፍቃደኝነት ቢያወጣላቸው ምንም ከልካይ ነገር የለም።
✘ ለፅንስ ዘካ ለማውጣት ፅንሱ 120 ቀን ወይም አራት ወር የሞላው መሆን አለበት ምክንያቱም ከአራት ወር በፊት ሩሕ ስለማይነፋበት እንደ ሰው አይቆጠርምና።
✘ ዘካቱል ፊጥርን ለማውጣት ሰውዬው ወሩን ፆመኛ ሆኖ ያሳለፈ መሆን አለበት አይባልም።ለምሳሌ አንዲት ሴት በወሊድ ደም ምክንያት ወሩን ሙሉ መፆም ባትችል፤ በሕመምም ይሁን በሌላ ሸሪዓዊ ዑዝር ያልፆሙ ሰዎች ዘካቱል ፊጥር ግዴታ የለባቸውም አይባልም።ይልቁንም ከሌላው ሰው ( ወሩን ፆመኛ ሆነው ካሳለፉት ) እኩል ዘካቱል ፊጥርን የማውጣት ግዴታ ይኖርባቸዋል።
✘ እራሳቸውን ችለው የሚኖሩ ልጆች ዘካውን የማውጣት ግዴታ እራሳቸው ላይ እንጂ ወላጆቻቸው ላይ አይደለም።
ወሏሁ ኣዕለም ~~~
ኢንሻአሏህ ይቀጥላል
189 viewsأبو سعيد, 06:57