Get Mystery Box with random crypto!

☞ የረመዷን ስንብት……!! ~ ከቀናት በፊት የረመዷንን መምጣት በጉጉት ስንጠባበቅ የ | أبو سعيد

☞ የረመዷን ስንብት……!!
~
ከቀናት በፊት የረመዷንን መምጣት በጉጉት ስንጠባበቅ የነበርን ሰዎች ዛሬ ከመቅፅበት የመጨረሻ ቀን ላይ እንገኛለን። «የተቆጠሩ ቀናቶች…» የሚለው የጌታችን ቃል ምንኛ ያማረ አገላለፅ ነው! አዚህ ገር ቆም ብለን እራሳችንን መጠየቅ ይጠበቅብናል። ባሳለፍናቸው ቀናት ምን ያህል ጊዜ ቁርኣንን አኸተምን?፣ ዚክር ላይ እንዴት ነበርን?፣ የሌሊት ሰሏትሳ?፣ የፆመኛ ዱዓእ ተቀባይነት አለው። ታዲያ ችግራችንን ለአሏህ አድርሰናል?፣ ፆመኛን አስፈጥረናል?፣ የታረዘን አልብሰናል?፣ የተራበን መግበናል?… ሌላም ሌላም መልካም ሥራ ላይ ተሰማርተናል? ለእነዚህ ጥያቄዎች መልሳችን "አዎ" ከሆነ አሏህን እናመስግን። "አይ" ከሆነ ግን ነፍሳችንን አርመን ዛሬን እንጠቀም። ካልሆነ ግን የተቀሩት ጥቂት ሰዓታት ያልፉናል። ምክንያቱም በረመዷን አንድ ቀን ማግኘት ታላቅ ዕድል ነውና እንጠቀምበት። በነገራችን ላይ ቀናቶች እየነጎዱ እድሜያችን እየተገባደደ እለተ-ቂያማ ከፊታችን በፍጥነት ወደኛ እየገሰገሰ መሆኑን ማስተዋል ያሻናል።

«...ﻭَﻣَﺂ ﺃَﻣْﺮُ ﭐﻟﺴَّﺎﻋَﺔِ ﺇِﻟَّﺎ ﻛَﻠَﻤْﺢِ ﭐﻟْﺒَﺼَﺮِ ﺃَﻭْ ﻫُﻮَ ﺃَﻗْﺮَﺏ...»
[النحل؛ ،٧٧]
«የሰዓቲቱ (መምጣት) እንደ ዓይን ቅፅበት እንጂ አይደለም። ወይ እርሱ ይበልጥ የቀረበ ነው።…» [አንነሕል ፥77]

አዎ ያለፈ ነገር እንጂ መጪ ነገር ሁሉ ቅርብ ነው። ከረመዷን ሂደት ይህንን መረዳት ይቻላል። ያለፉት የረመዷን ቀናት ላይመለሱ አምልጠዋል። የተጠቀመባቸው አሏህን ያመስግን፤ የተሳነፈባቸው ነፍሱን እንጂ ማንንም መውቀስ አይችልም። ባይሆን የዛሬውን ቀን ከልብ መጠቀም ብልህነት ነው። የዛሬው ቀን ከብዙ እይታ አንፃር ካለፉት ይበልጥ ውድ ነው።

~ አንደኛ፦ የረመዷን ማብቂያና ማጠናቀቂያ በመሆኑ በዚህ ቀን ሥራን ማሳመር ፍፃሜን እንደማሳመር ይታሰባል። የሥራ ማማር የሚመዘነውም አጨራረሱ ላይ ነው። መልዕክተኛችንምﷺ እንደሚከተለው ገልፀዋል፦
«ﺇﻧَّﻤﺎ ﺍﻷﻋﻤﺎﻝُ ﺑﺎﻟﺨﻮﺍﺗﻴﻢِ‏»
«ሥራ (የሚለካው) በፍፃሜው ነው።» ስለሆነም በዛሬው ቀናችን አጨራረሳችንን ለማሳመር መትጋት አማራጭ የሌለው መፍትሔ ነው።

~ ወንጀሉ የሚማረው በመጨረሻው ሌሊት ነው።
«… ﻭﻳﻐﻔﺮ ﻟﻬﻢ ﻓﻲ ﺁﺧﺮ ﻟﻴﻠﺔ ‏» ﻗﻴﻞ: ﺃﻫﻲ ﻟﻴﻠﺔ ﺍﻟﻘﺪﺭ؟ ﻗﺎﻝ: ‏« ﻻ، ﻭﻟﻜﻦ ﺍﻟﻌﺎﻣﻞ ﺇﻧﻤﺎ ﻳﻮﻓﻰ ﺃﺟﺮﻩ ﺇﺫﺍ ﻗﻀﻰ ﻋﻤﻠﻪ‏»
ረሱል ﷺ «…(ለፆመኞች) በመጨረሻው ሌሊት (ወንጀላቸውን) ይምርላቸዋል» አሉ። "ይህ የሚሆነው በውሳኔይቷ ሌሊት ነውን?" ተብለው ተጠየቁ። እሳቸውም፦ «አይደለም። ይልቅ ሠራተኛ ሥራውን ሲጨርስ ነው ሙሉ ክፍያውን የሚሰጠው።» አሉ።

~ ሁለተኛ፦ የዛሬው ቀን ከመጨረሻዎቹ አስርት ቀናት አንዱ ነው። ስለዚህ ባለፉት ቀናት ሰንፈንም ከነበረ ዛሬን እንኳ አንበርታ። አጠቃቀሙን እንቻልበት። ብልህ ሰው ካለፈው ይማራል፣ ለቀጣዩ ቀበቶውን ጠበቅ ያደርጋል።

~ ለማንኛውም አሏህን በብዛት ማምለክ፣ ቁርኣን በብዛት መቅራት፣ ሌሎችም መልካም ተግባራቶች መተግበር ረመዷን ውስጥ ምንዳቸው እጥፍ ድርብ ይሁን እንጂ በሁሉም ወራትና ቀናት ታላላቅ ምንዳዎችን ያሰጣሉ። እንዲያውም እውነቱን ለመናገር ረመዷን ውስጥ ዒባዳ ላይ በብዛት በርትቶ ሲያበቃ ረመዷን ሲወጣ ግዴታዎችን እንኳን እርግፍ አድርጎ ከሚተው አካል ረመዷን ውስጥም ሆነ ውጪ ግዴታዎች ላይ የሚፀና አካል በእጅጉ የተሻለ ነው። በል አይነፃፀሩም! ስለዚህ ጽና! የ2014 ረመዷን አንተ ላይ የለውጥ አሻራውን አኑሮብህ "እኔ ዲኔ ላይ ለውጥ ያመጣሁት፣ የሰላትና መስጂድ ሰው የሆንኩት 2014 ረመዷን ላይ ነበር።" ብለህ የምትተርከው ታሪክ እንዲፈጠር አድርግ

~ ከረመዷን ጋር አብረህ ከመስጂድ እንዳትወጣ። እባክህ የሚጠቅምህን ምክር ሰምተህ ተግባራዊ አድርግ። ለፅናትህ ወሳኝነት አለው። አሏህ ይህንን በቁርኣን በአጽንኦት ገልፆታል፦
"... ﻭَﻟَﻮْ ﺃَﻧَّﻬُﻢْ ﻓَﻌَﻠُﻮﺍ ﻣَﺎ ﻳُﻮﻋَﻈُﻮﻥَ ﺑِﻪِ ﻟَﻜَﺎﻥَ ﺧَﻴْﺮًﺍ ﻟَﻬُﻢْ
ﻭَﺃَﺷَﺪَّ ﺗَﺜْﺒِﻴﺘًﺎ" [النساء؛ ٦٦]
«…እነርሱም በእርሱ የሚገሰጹበትን ነገር በሠሩ ኖሮ ለነሱ መልካምና (በእምነታቸው ላይ) ለመርጋትም በጣም የበረታ በኾነ ነበር።» [አኒ፞ሳእ፥66]

☞ አንባቢ ሆይ! አንብበህ መተግበርን ልመድ። የማንበብህ ዓላማና ዒላማ ተግባር እንጂ የማንበብ ልምድ ማዳበር ብቻ አይሁን። አሏህ እኛንም እናንተንም ፆማችንን ይቀበለን! ከረመዷንም በኋላ ፅናትን ይስጠን!
ወሏሁ አዕለም!

አቡ ሰዒድ (ዐብዱረሒም ሑሴን)
https://t.me/abuseidibnuhussen