2022-01-18 09:11:13
ከተራ ማለት ምን ማለት ነው | ሊቀ ጉባኤ ጌታሁን ደምፀ
#ከተራ ማለት “ከተረ” ከበበ ዙሪያውን ያዘ ካለው ከግዕዝ
ቃል የተገኘ ነው፡፡ከተራ ማለት ከበባ እጀባ ማለት ነው፡፡
ይኸውም ታቦተ ሕጉ በጳጳሳት፣ በሊቃውንት፣ በቀሳውስት፣
በዲያቆናት እንዲሁም በምእመናን ተከቦ ታጅቦ መጓዙን
የሚያመለክት ገላጭ ቃል ነው፡፡
፪ኛ ከተራ ማለት ከተረ ሰበሰበ ዐጠረ ማለት ሲሆን
ይኸውም ወራጁን ውኃ ሰብስበው ወይም ገድበው
በየሰበካው ተለይቶና ተከልሎ ታቦታቱ በዳስ ወይም
በድንኳን የሚያድሩበት የተለያዩ የውኃ አካላት ተጠርገው
ሚከተሩበት ስለሆነ ነው፡፡ ይህም ስፍራ ‹‹ባሕረ
ጥምቀት›› ወይም ‹‹የታቦት ማደሪያ›› እየተባለ ይጠራል፡፡
ውኃ መሰብሰቢያ ምቋመ ማይ ማለት ነው፡፡
የከተራ በዓል ጥንት ከነገሥታቱ ጀምሮ የሀገር መሪዎች
በቀዳሚነት ተሰልፈው የሚያከብሩት ብሔራዊ በዓል
ከመሆኑ የተነሣ ሃይማኖታዊና ባህላዊ የአከባበር ሥነ
ሥርዓት አለው፡፡ ይኸውም ባህላዊው ከሃይማኖታዊው
ሥርዓት በመነሣት የሚከናወን ሆኖ ማህበረ ሰቡ ደስታውን
ፍቅባሕላዊ ሚገልጥበት የአለባበስ የአጨዋወት ሥርዓት
አለው፡፡
*_ባሕላዊ አከባበሩ_*
እዩት እዩት ሲያምር
የበአታ ደብር።
እንኳን ለታቦት ለደጉ ጌታ
ይጨበጨባል ለጋለሞታ፡፡
ሁሉም ያምረኛል በመር በመሩ፤
እነ መምሬ ቅኔ ሲመሩ፡፡
በሕይወት ግባ በሕይወት፤ የአገሬ ታቦት፡፡
ሲያምር ዋለ ሲያምር፤ የሀገራችንደብር፡፡
እየው ወሮአት ሲገባ፤ ጌታ ባለአበባ፡፡
አለው አለው አበባ፤ የአገሬ ታቦት ሲገባ፡፡
ርግቤ በቀሚሱ ላይ፤ ርግቤ በካባው ላይ፤
የሰላም ምልክት ይዛ ልትታይ፡፡
ልብሱ አረፈረፈ ልብሱ አረፈረፈ፤
ርግብ በራሱ ላይ ዐረፈ፡፡ እያሉ የደብራቸውን ታቦት
ያመሰግናሉ።
በዚህ መልኩ ታቦቱን በልዩ ልዩ ቃላት ያሞግሳል፡፡
ሴቶችም እንደዚሁ በበኩላቸው ከወላጆቻቸው ሲዋረስ
በመጣው መሠረት ነጫጭ የሀገር ልብሳቸውን ለብሰው
ከዋክብት መስለው መቀነታቸውን በወገባቸው ሸብ አርገው
የታቦት ዜማ ያሰማሉ፡፡
*_ሃይማኖታዊ አከባበሩ_ ፡፡*
ጥር ፲ ቀን ከቀኑ በአራት ሰዓት በመላው አጥቢያ አብያተ
ክርስቲያናት ዋዜማ ይቆማል፡፡ ከሰዓት በኋላ ታቦታቱ
በተለያየ ሕብር በተሸለሙ የክህነት አልባሳት በደመቁ
ካህናትና የመጾር መስቀል በያዙ ዲያቆናት ከብረው፣
ከአብያተ ክርስቲያናት ወደ አብሕርተ ምጥማቃት ለመሄድ
ሲነሡ መላው አብያተ ክርስቲያናት የደወል ድምፅ
ያሰማሉ፡፡ ምእመናን ከልጅ እስከ ዐዋቂ በነቂስ ወጥተው
በአጸደ ቤተ ክርስቲያንና ታቦታቱ በሚያልፉባቸው መንገዶች
ይሰባሰባሉ፡፡
*_መንፈሳዊ ምሥጢሩ_*
ቃል ኪዳኑን ታቦት ይዞ አክብሮ ወደ ወንዝ መውረድ
በብሉይ ኪዳን የነበረ ሥርዓት ነው፡፡ ይኸውም ኢያሱ
በሙሴ ተተክቶ ሕዝበ እስኤልን ሲመራ ታቦቱን አሸክሞ
ሲሔድና ከዮርዳስ ወንዝ ሲደርስ ወራጁም ይቆም
እንደነበረ ቅዱስ መጽሐፍ ይናገራል፡፡ እስራኤል ወደ
ምድረ ርስት ሲገቡ ታላቁን የዮርዳስ ወንዝ ሲሻገሩ
ድንኳን ጥለው የቃል ኪዳን ታቦት ድንኳን ውስጥ
አድርገው ሌዋውያኑ ዙሪያውን ካህናቱ በውስጥ ሆነው
እግዚአብሔን እያመሰገኑ እንደተሻገሩ ዛሬም እንደ
ዮርዳኖስ ከጉስቁልና ወደ ብልጽግና ከደዌ ወደ ጤና
አላሻግር ያለን ባሕረ ኀጢአት በቃል ኪዳኑ አማካኝነት
በጥምቀቱ በረከት ያደርቅልናል ስንል ነው፡፡ ኢያሱ ፩፥፲፫ ፣ ኢያሱ ፫፥፰
አንድም ሐዋርያው ፊሊጶስ ኢትዮጵያዊ ጃንደረባውን
ሊያጠምቀው ወደ ወንዝ የመውረዱ ምሳሌ ነው፡፡ (ሐዋሥራ ፰፥፴፬)
ዋናው ምስጢሩ ግን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዮሐንስን
አስከትሎ ሊጠመቅ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ የመሄዱ ምሳሌ
ነው፡፡ ታቦቱ የጌታችን፤ ታቦቱን ተሸክሞ የሚሄደው ካህን
የቅዱስ ዮሐንስ፣ ባሕረ ጥምቀቱ የዮርዳኖስ፣ ታቦታቱን
አጅበው የሚሄዱት ምእመናን ወደ ቅዱስ ዮሐንስ እየመጡ
የንስሐ ጥምቀት ሲጠመቁ የነበሩ ሰዎች ምሳሌዎች
ናቸው፡፡
ታቦታቱ ወደ ጥምቀተ ባሕር ወርደው በዚያው ማደራቸው
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በእደ ዮሐንስ
ለመጠመቅ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ ከማታው ጀምሮ
መውረዱንና ተሰልፎ ተራውን ሲጠብቅ ማደሩን
ያጠይቃል፡፡ ‹‹ጥምቀት የሞቱ የመቃብሩ አምሳል ነው፡፡
ጌታችን የተጠመቀበት ወርኀ ጥር በእስራኤላውያ ዘንድ
የዝናም፣ የበረዶ ወራት ነው፤ እንኳንስ ከወንዝ ዳር
ከማናቸውም ቦታ ቢሆን ያለ መጠለያ መዋልና ማደር
አይቻልም፤ በመሆኑም ከዮሐንስ ለመጠመቅ የሚሄዱ
ሰዎች ሁሉ በዮርዳኖስ ዙሪያ ድንኳናቸውን ተክለው ያርፉ
ነበር፡፡ በዚህ አንጻር ዛሬም በባሕረ ጥምቀት ዙሪያ
በድንኳኖች የተከለሉ ዳሶች ይጣላሉ፡፡
ስለዚህ ከጥንት ጀምሮ የቃል ኪኑን ታቦት ይዘን ወደ ወንዝ
ወርደን በዓለ ጥምቀትን የምናከብረው ከዚህ ታሪክ
በመነሣት ነው፡፡
በዚህ ምክንያት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ
ክርስቲያን በየዓመቱ ጥር ፲ ቀን ተቀራራቢ የሆኑትን
ታቦታትን በየአቅራቢያቸው ወደሚገኘው ወንዝ በአንድነት
እያወረደች ከከተራ ዕለት ጀምሮ የጥምቀትን በዓል በታላቅ
መንፈሳዊ ሥነ ሥርዓት ታከብራለች፡፡ ሌሉቱን ከሚያነጋው
ሕዝበ ክርስቲያን ጋር በመሆን የማኅሌትና የወንጌል ጉባኤ
ተዘርግቶ በመምህራን ወቅታዊ ትምህርት ሲሰጥ ይታደራል
ይዋላል፡፡
*መልካም የጥምቀት በዓል ለመላው ህዝበ ክርስቲያን ይሁን!*
@ABUNE_ABIB
@ABUNE_ABIB
@ABUNE_ABIB
48 viewsB Belete , 06:11