2022-03-08 18:44:43
የባሕር ዳር ቅርንጫፍ ለወላጆች ሥልጠና ሰጠ
*************
የአቡነ ጎርጎርዮስ ትምህርት ቤቶች ባሕር ዳር ቅርንጫፍ ከአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የሥነ-ምግባር እና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ጋር በመተባበር በሙሉዓለም የባሕል ማዕከል የወላጆች፣ ተማሪዎች እና መምህራን ትስስር በሚል ርዕሰ ጉዳይ ላይ ለወላጆች ሥልጠና ሰጠ፡፡
ሥልጠናው በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ሥነ-ምግባር እና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን የፊት ለፊት ሥልጠና ዘርፍ ባለሙያ በሆኑት በመምህር ዘላለም ንጉሴ የተሰጠ ሲሆን የወላጆች፣ ተማሪዎች እና መምህራን ትስስር ከግብረገብ ምንነት እና አስፈላጊነት አንጻር እንዲሁም ኢትዮጵዊ እሴት ላይ ያተኮረ ነው፡፡
የባሕር ዳር ቅርንጫፍ ትምህርት ቤት አስተዳደር የሆኑት አቶ አድጎ አድምጥ የተማሪዎች ሥነ-ምግባር እና ግብረገብነት የትምህርት ቤቱ፣ የወላጆች እና የማህበረሰቡም ኃላፊነት ጭምር ነው ያሉ ሲሆን ሥልጠናው ወላጆች ለልጆቻቸው አርአያ ሆነው ልጆቻቸውን መቅረጽ እንዲችሉ የሚያስችል ነው ብለዋል፡፡ አስተዳደሩ ጨምረውም ልጆችን በስነምግባር አንጾ ማሳደግ የሁላችንም ድርሻ በመሆኑ ኃላፊነታችንን ልንወጣ ይገባል ብለዋል፡፡
ማህበረሰባዊ እሴቶችን አክባሪነት፣ ለሰው እኩል ክብር መስጠት፣ ማህበረሰባዊ ተደጋጋፊነት፣ ቅንነት፣ታዛዥነት እና የአገልጋይነት ስሜት የመሳሰሉት ርዕሰ ጉዳዮች እና ሌሎች በርካታ የሥነ-ምግባር መገለጫዎች በስልጠናው ተዳሰዋል፡፡
የቅርንጫፍ ትምህርት ቤቱ ከሰባት - አስራሁለተኛ ክፍል ርዕሰ መምህር የሆኑት አቶ አዲሱ አጥናፉ አቡነ ጎርጎርዮስ ካለው አላማ አንጻር ብቻ ተሰርቶ ለውጥ ላይመጣ ይችላል እኛ የሰራነውን ሌሎች ሊያፈርሱት ይችላሉ፡፡ ስለዚህ እንዴት ልጆቻችንን እናሳድግ በሚል ወላጆች ያልሆኑትን ልጆቹ ላይ ለማየት መጠበቅ አስቸጋሪ ስለሚሆን ሥልጠናውን ለወላጆች መስጠቱ አስፈላጊ ሆኖ አግኝተነዋል ብለዋል፡፡
በሥልጠናው ተሳታፊ የነበሩ ወላጆች በበኩላቸው ራሳችንን እንድናይ እና የነገ ሀገር ተረካቢ ትውልድ ለመቅረጽ የድርሻችንን እንድንወጣ መነቃቃትን ፈጥሮልናል ያሉ ሲሆን አክለውም ይህን መሰል ሥልጠና በቀጣይም ማግኘት ብንችል ሲሉ የሥልጠናውን አስፈላጊነት ጠቁመዋል፡፡
የአክሲዮን ማህበራችንን ድህረ ገፅ https://esdros.com/e/ በመከታተል ወቅታዊ መረጃዎችን ያገኛሉ።
2.8K viewsEsdros ICT, 15:44