Get Mystery Box with random crypto!

ቡሄ ማለት ምን ማለት ነው ? ችቦ ለምን እና መቼ ይበራል? ሙልሙል ልምን ይታደላል? በቡሄ ወቅ | ፍቄ ክራር ቲዩብ-Fike Kirar Tube

ቡሄ ማለት ምን ማለት ነው ? ችቦ ለምን እና መቼ ይበራል? ሙልሙል ልምን ይታደላል? በቡሄ ወቅት ጭራፍ ለምን ይጮሃል ?

ቡሄ

ቡሄ ማለት ብራ፣ ብርሃን፣ ደማቅ ማለት ነው፡፡ ጌታችን ብርሃነ መለኮቱን የገለጠበት በዓል የሚዘከርበት እና ለበዓሉም ችቦ ስለሚበራ የብርሃን በዓል በማለት የቡሄ በዓል እንላለን፡፡ ወቅቱ የክረምት ፤ጨለማ አልፎ የብርሃን የሚወጣበት፤ ሰማይ ከጭጋጋማነት ወደ ብሩህነት የሚለወጥበት የመሸጋገሪያ ወቅት ነው፡፡ “ቡሄ ከዋለ የለም ክረምት፤ ዶሮ ከጮኸ የለም ሌሊት” እንዲሉ፡፡ በሌላ በኩልም “ቡኮ/ሊጥ” ተቦክቶ ዳቦ የሚጋገርበት “#ሙልሙል” የሚታደልበት በዓል በመሆኑ ቡሄ ተብሏል

ጅራፍ

በደብረ ታቦር በዓል በትውፊታዊ መልኩ የሚታየው ምስጢር፤ በኢየሩሳሌም ስለሚሆነው የጌታችን ምስጢራዊ ሞቱ ነው፡፡ ጅራፍ መገመድ(መጥለፍ) እና ጅራፍ ማጮኽ ሁለት ዓይነት ምስጢር የያዘ ትውፊታዊ ተግባር ነው፡፡ የመጀመሪያው ግርፋቱንና ሞቱን እናስብበታለን፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ፤ድምፁን ስንሰማ የባሕርይ አባቱን የአብን ምስክርነት ቃል፤ እንደ ነጎድጓድ ድምፅ ያስታውሰናል፡፡
የጅራፍ ትውፊታዊነት /ውርስ/፣ መጽሐፋዊ ትምህርትና ምስጢር ጠብቆ ለትውልድ እንዲተላለፍ ለማድረግ ጨዋታውን በተራራማ አካባቢ፣ ከመኖሪያ ቤት ርቆና፣ በሜዳ ማድረጉ ጠቃሚ ነው፡፡ ጅራፍን #በርችት መቀየር የሚያመጣውን የምስጢር ተፋልሶ ብቻ መመልከት ከማኅበራዊ ጎጂ ገጽታው በላይ እንድናስወግደው ያስገድደናል

ችቦ

ችቦ የጌታችንን ብርሃነ መለኮት መገለጥ የሚያመለክት ነው፡፡ በመሆኑም ችቦ ለኩሰን በዓሉን እናከብራለን፡፡ የዚህ ትውፊታዊ አመጣጥ በብርሃኑ ድምቀት የቀኑን መምሸት ያልተረዱ እረኞች በሜዳ ቀርተዋልና ወላጆች ከመንደር ችቦ ለኩሰው ልጆቻቸውን ፍለጋ ሔደዋልና ታሪኩን እያዘከርን በዓሉት እናከብራለን፡፡ የችቦው መንደድም ሌላ ትርጉም አለው፡፡ አንድ ምእመን ለሌላው ምእመን መካሪ አስተማሪ መሆኑን፣ መከራ እየተቀበለም አርአያ፣ ምሳሌ፣ ብርሃን መሆኑን ያሳያል፡፡ በሃይማኖትም አርአያ ምሳሌ ይሆንላቸዋል፡፡ ከዚህ ጋርም ተያይዘዞ ችቦ በ13 ምሽት ይበራል ፣ብርሃኑ የተገለጠው በዚችው ዕለት ነውና

ሙልሙል

በችቦ ብርሃን ልጆቻቸውን ፍለጋ የወጡ ወላጆች ዳቦ ጋግረው ይዘውላቸው ወጥተዋል፡፡ ስጦታው ቤተሰባዊነትን፣ ፍቅርንና መተሳሰብን መግለጫ ነው፡፡ ወደ ቤታችን “ ቡሄ ” እያሉ ለሚመጡ አዳጊዎችም፤ ዘምረው እንዳበቁ የሚሰጥ “ሙልሙል” ዳቦ አለ፡፡ ሕፃናቱም ሊዘምሩ ሲመጡ ዳቦ መስጠት ልማዳዊ ብቻ አይደለም

ሕፃናቱ የደቀመዛሙርት ምሳሌ ናቸው፡፡ መዝሙራቸው ደግሞ ሐዋርያት “የምሥራች” ይዘው የመምጣታቸው ምሳሌ ነው፡፡ ሐዋርያት በገቡበት አገር አስተምረው አጥምቀው የጸጋ ልጅነትን አሰጥተው በረከት አድለው እንደሚሔዱም፣ ልጆችም ዘምረው፣ አመስግነው፣ መርቀው “ውለዱ ክበዱ፣ ሀብት አግኙ፣ የመንግሥተ ሰማያት ወራሾች ያድርጋችሁ ….” ይላሉ

በአጠቃላይ በዓለ ደብረ ታቦር ከእነዚህ ምስክር ካላቸው ትምህርቶቹ፣ ምሥጢር ከሚራቀቅባቸው ትርጓሜያቱና ከትውልድ ትውልድ በቅብብል በተላለፈው ቅዱስ ትውፊት ጋር ሃይማኖታዊ ባሕል ሆኖ ሊቀጥል ይገባዋል፡፡ ይህን ማድረግ የሚቻለው ግን አዳጊዎች ሃይማኖታዊ ትውፊቱን ይዘው እንዲያድጉ ጥቆማ በመስጠት፣ ግጥም በመግጠምና

ምሥጢሩን በማብራራት የመጀመሪያዎቹ ባለድርሻዎች ወላጆች ናቸው፡፡ አንዳንድ ጊዜ የሚሰሙ ግጥሞች ስድብ፣ ፌዝና ሥላቅ የተቀላቀለባቸው ይሆናሉ፡፡ ሕፃናቱም ዝማሬውን ሲጀምሩ “ከሰጡን እንነሣ ከነሱን እናርዳ” ብለው ይጀምሩታል፡፡ ከሰጡን እንመርቃለን ካልሰጡን እንራገማለን በማለት፡፡ አሳሳቢው ነገር ደግሞ ሃይማኖታዊ ሥርዓቱን ወደ ገንዘብ ማግኛነት የቀየሩ ሁኔታዎች መታየታቸው ነው

ዳቦ /ሙልሙል/ ትምህርቱንም፣ ምስጢሩንም፣ ትውፊቱንም በአግባቡ ልንጠቀምበት ይገባል ከዚም ጋር ተያይዞ ሰንበት ት/ት ቤታችን ለበርካታ ዓመታት ሲወረድ የመጣውን የዝማሬ ሥርዓት ለአጥብያው ምእምን በየቤቱ በመሄድ የብሄን ዝማሬ ከነሥርዓቱ በመዘመር አገልግሎት ይሰጣል ፤የደብር ታቦርን በዓል በተመለከትም የወረቀት ጽሑፎችን ይበትናል በዝማሬ መኃል ያድላል ፡፡
ቤተክርስቲያን የምሥጢር ግምጃ ቤት ናት፤ የምታከናውነውን ሁሉ ከበቂ መረጃ ጋር ነው ተግባራዊ የምታደርገው

@aboutkirar
@aboutkirar
@aboutkirar