Get Mystery Box with random crypto!

ዝክረ ቅዱስ ያሬድ በአቡነ ጎርጎርዮስ ትምህርት ቤቶች ለቡ ቅርንጫፍ በታላቅ ድምቀት ተከበረ፡፡ | ABG Weyra branch Grade1-8

ዝክረ ቅዱስ ያሬድ በአቡነ ጎርጎርዮስ ትምህርት ቤቶች ለቡ ቅርንጫፍ በታላቅ ድምቀት ተከበረ፡፡
*************
የአቡነ ጎርጎርዮስ ትምህርት ቤቶች ለቡ ቅርንጫፍ መምህራን እና ተማሪዎች ኢትዮጵያዊው ሊቁ ቅዱስ ያሬድ የተሰወረበትን ቀን በትምህርት ቤቱ በተዘጋጀ መርሐግብር ዘክረው ውለዋል፡፡
በ505 ዓ/ም የተወለደው ሊቁ ማኅሌታይ ቅዱስ ያሬድ አክሱም አካባቢ ከእናቱ ክርስቲና (ታኡክልያ) አባቱ ደግሞ ይስሐቅ (አብድዩ) እንደተወለደ የታሪክ ድርሳናት ያወሳሉ:: አንድ ቀን ግን መምህሩ የነገሩት ቀለም አልያዝህ አለው፣ ሲፈትኑትም ባለመመለሱ ተገረፈ:: ዱላው በጣም ስለ ተሰማው ቅዱሱ ከመምህሩ ኮብልሎ ማይ ኪራሕ አካባቢ ሲደርስ ደክሞት አርፎ እግዚአብሔር ትጋትንና ተስፋ አለመቁረጥን ከትል አስተማረው:: ትሏ ስድስት ጊዜ ወድቃ በሰባተኛው ፍሬዋን ስትበላት ተመልክቷልና:: ከዚህ በኋላ ቅዱስ ያሬድ ወደ መምህሩ ተመልሶ እና ይቅርታ ጠይቆ ትምህርት ጀመረ:: ሊቁም ትጋትንና ጸሎትን ከሰጊድ ጋር አበዛ:: እግዚአብሔርም በድንግል እናቱ አማካኝነት የምሥጢር ጽዋን አጠጣው:: እርሱም በጸሎት ላይ ሳለ ተደሞ መጣበት:: ሦስት መላእክት በሦስት ወፎች አምሳል መጥተው አነጋገሩት:: ድንገትም ነጥቀው ወደ ሰማያት ወደ ልዑላኑ መላእክት ዘንድ አደረሱት:: ሊቁ በሰማያት ልዩ ምሥጢር : ልዩ ምስጋናና ልዩ ዜማን አዳመጠ:: ይህንን ምስጋና ብዙ ቅዱሳን ቢሰሙትም ቅዱስ ያሬድ ግን ይዞት እንዲወርድ ተፈቀደለት::
ቅዱስ ያሬድ በሊቅነቱ ካበረከታቸው አምስት ያህል መጻሕፍትን በተጨማሪ በጣና ቂርቆስ፣: በዙር አምባና በሌሎችም ቦታዎች ወንበር ዘርግቶ ብዙ ደቀ መዛሙርትን ያፈራ ሊቅ ሲሆን በሰሜን ተራሮች አካባቢ በትጋሀ መላእክትና በተባሕትዎ እንደኖረም ይነገራል::
በተወለደ በ71 ዓመቱ ግንቦት 11 ቀን በ576 ዓ/ም እንደተሰወረ የሚነገረው ቅዱስ ያሬድን በዜማው በጥበቡ የሚዘክር መርሐ ግብር በተማሪዎች እና መምህራን በማቅረብ የአቡነ ጎርጎርዮስ ትምህርት ቤቶች ለቡ ቅርንጫፍ ዘክረውታል::