2023-01-17 11:18:39
የአዲስ- አዳማ የፍጥነት መንገድ በደረሰ የእሳት አደጋ መዘጋቱ ተገለጸ::
የአዲስ- አዳማ የክፍያ መንገድ በደረሰ የእሳት አደጋ ዋና መውጫው ላልተወሰነ ጊዜ ዝግ መሆኑን የኢትዮጵያ የክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ አስታውቋል፡፡
በትናትናው ዕለት ምሽት 4 ሰዓት ከ 45 ኤፍ ኤስ አር ተሽከርካሪ ወደ አዳማ የሐበሻ አረቄ ጭኖ እየተጓዘ እያለ አዳማ መዉጫ የመጨረሻ ክፍያ ጣቢያ ሲደርስ በደረሰ አደጋ የአራት ሰዎች ህይወት ሲያልፍ አራት ሰዎች ላይ ከባድ የቃጠሎ አደጋ ደርሶባቸዋ።
በአደጋው በተሽከርካሪዎች ውስጥ የነበሩ ሶስት ሰዎች እና አንድ የክፍያ ጣቢያ ትኬት ቆራጭ ሰራተኛ ወዲያው በቃጠሎው ህይወታቸው ማለፉም ነው የተሰማው፡፡
በተጨማሪም አራት ሰዎችም ከባድ የቃጠሎ አደጋ ደርሶባቸው በአዳማ ሆስፒታል የህክምና ክትትል እየተደረገላቸው ይገኛል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም አረቄ ጭኖ ሲጓዝ የነበረው ተሽከርካሪና ሌሎች ሦስት ተሽከርካሪዎች የተቃጠሉ ሲሆን 10 ሚሊየን ብር የሚገመት ንብረት መውደሙን የአዲስ አበባ እሳትና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ንጋቱ ማሞ ገልጸዋል።
የአደጋዉ መንስኤ የሆነዉ የአበሻ አረቄ በበርሜል የጫነ ኤፍ ኤስ አር ተሽከርካሪ አስቀድሞ በክፍያ መንገዱ ላይ ቃጠሎው ያጋጠመው ሲሆን፤ አሽከርካሪው መኪናውን ማቆም ባለመቻሉ እሳቱ ሊዛመት መቻሉ ተገልጿል፡፡
ህንንም ተከትሎ አዳማ የክፍያ መንገድ የአዳማ ዋና መውጫ ላልተወሰነ ጊዜ ዝግ መደረጉ የኢትዮጵያ የክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ ያስታወቀ ሲሆን ደንበኞች በሞጆ 52 ኪሎ ሜትር፣ 56 ኪሎ ሜትር እንዲሁም በ60 ኪሎ ሜትር አማራጭ የጉዞ መስመሮችን እንዲጠቀሙም አሳስቧል፡፡
@Abbay_Tv
1.1K views08:18