2023-10-01 10:40:21
❖❖❖❖
መስቀሉን እሸከማለሁ የሚል የመድኃኔ ዓለም ወዳጅ ????????????????????????? አንተ ሰው እስኪ ልጠይቅህ? :ጌታ የተሰቀለ ዕለት ዕርጥብ መስቀል ተሸክሞ ወደ ቀራንዮ ሲሄድ ብትኖር ኖሮ ታግዘው ነበርን ? ወይስ አብረህ ትገፋው ነበር ? ወይስ በርቀት ሆነህ ይገባዋል እያልክ ትደነፋ ነበር ? ወይስ አላውቀውም ብለህ ትክድ ነበር ? ወይስ ጥለኸው ትጠፋ ነበር ? ወይስ በልብህ አምነህ አብረህ ከጠላቶቹ ጋር ታመዋለህ ? ወይስ ራቅ ብለህ ትከተለው ይሆን ? እስኪ ዛሬ የደመራ ነጭ ልብስህን እንደለበስህ ይህንን አስብና ምን እንደምታደርግ እርግጡን ለልብህና ለራሱ ለመድኀኔዓለም ንገረው !
አይ ጌታዬ ተሸክሞ እየደከመማ አግዘዋለሁ እንጅ አልክደውም ትለኝ ይሆናል ። እኔም እንዲህ እልሃለሁ ።
አንተ ሰው ! አሕዛብ ቤቱን በማቃጠል ፥ ልጆቹን በማረድ እያሳደዱት በአንተ ዘንድ በልጅነት ያድር ዘንድ በመጣ ጊዜ ሰውነትህን በዝሙትና በበደል አርክሰህ በንስሐ ሳትታጠብ ከቆየኸው ማደሪያ እየነሣኸው አይደለምን ? አብረህ እየገፋኸው አይደለምን ? እርሱ ስለአንተ ርጥብ መስቀል ተሸክሞ አንተ የወንድም እኅቶችህን አመል የማትታገሥ ከሆነ ምኑን መስቀሉን አገዝኸው ? እርሱ ለጠላቶቹ መስቀል ከተሸከመ የእኅት ወንድሞቻችን ሸክም የማንሸከም እኛ ምን እዳ ይጠብቀን ይሆን ? ወዳጄ ክርስቶስ ለቤተክርስቲያን ሲል የተሸከመውን መስቀል አግዘዋለሁ ካልክ አንተ ለምን ለሚስትህ ብለህ ድካሟን አትሸከምም ? እጠቀም የማይል ጌታ የአይሁድን መስቀል ከተሸከመ መንግሥተ ሰማያት ትወርስ ዘንድ ለምን መከራ አትቀበልም ?
ዛሬ በቤተክርስቲያን ውስጥ ! አንዳንዶቻችን በልብ አምነን በአፍ ዝም ያልን ነን ! አንዳንዶቻችን ገብቶንም ሳይገባንም መስቀሉን ከሚገፉ ጋር ተባባሪዎች ነን ! አንዳንዶቻችን ራቅ ብለን እሰይ ይበላቸው እያልን በአባቶቻችን ውርደት የምንሳለቅ ነን ! አንዳንዷቻችን ደግሞ ቀርቦ ከመቃጠል ራቅ ብሎ መጠቅለል እያልን ከባድ ነገር መስማትን የማንወድ ሲነሣ ንገሩኝ አይነት ሰዎች ነን ! አንዳንዶቻችን እንደ ቀንድ አውጣ ደስታ ሲሆን ብቅ መከራ ሲመጣ በኑሯችን ሸማ ጥልቅ የምንል ነን ! አንዳንዶቻችን ጭራሽ ምን እየሆነ እያለ እንኳ የማይገባን አመት በዓል ሲመጣ ለምግብ ብቻ አለሁ ባዮች ጥለን የጠፋን የበረከተ ኅብስትና የድግሥ ክርስቲያኖች እንጅ ቀራንዮ ላይ የለንም ! የመጥፋታችን ምልክቱማ የመስቀል ዕለት መዝፈናችን
አይደል !
መስቀሉን እሸከማለሁ የሚል የመድኃኔ ዓለም ወዳጅ ?????????????????????????
መልስ ፦ እኔ አለሁ የመድኃኔዓለም ወዳጅ ኃይል ባገኝ የቤተክርስቲያናችን ፈተናዎች ለማሳለፍ እተጋለሁ ። ባይቻለኝ ግን የራሴን ፦
1. የራሴን ሥጋዊ የፍትወት መከራ መስቀል እሸከማለሁ እንጅ የፈቃዴ ባርያ አልሆንም ።
2. ዘወትር የዕለት ዳዊትና ውዳሴ ማርያም በመጸለይ ያለ ማቋረጥ አምላኬን እመገባለሁ ።
3. በሠራኋቸው በደሎች ከነገ ጀምሮ ለንስሐ አባቴ እናዘዛለሁ ።
4. ጌታዬ በመስቀል የተሰቀለው ለእኔ ምግብ ሆኖ ሊፈተት ፥ መጠጥ ሆኖ ሊቀዳ ነውና ለእኔ ሲል መሞቱን ቅዱሥ ሥጋውን በመቀበል እመሠክራለሁ ።
5. ምንም ቢሆን ጌታዬ እኔን ፍለጋ ከሰማይ ወደ ምድር ወርዷልና እኔም እርሱን ፍለጋ ቤተክርስቲያን ኪዳን ሳላስደርስ አልውልም ።
6. እርሱ የእኔን ደዌ በመስቀል እንደተሸከመ እኔም የባልንጀራዬን ድካም ታግሼ ማንንም ሆነ ማንን ይቅር እላለሁ ።
8. በመከራዬም ሆነ በደስታየ ከመስቀሉ ሥር እገኛለሁ እንጅ ራበኝ ብየም አልጠፋም ጠገብሁ ብየም አልርቅም !
9. ቢቻለኝ የቤተክርስቲያንን ችግር እፈታለሁ መስቀሉን እሸከማለሁ እንጅ አባቶችን አልተችም ከገፊዎች ጋር አልቆምም ።
10. ጊዜየን በማይረባና ርብሐ ቢስ በሆነ አላባክንም ፤ በየጊዜው ና በየሰዓቱ ስለቤተክርስቲያን ባልናገር እንኳ ቢያን ጆሮየ ለቤተክርስቲያን የተከፈተ አደርጋለሁ ።
11. ሥጋውን ደሙን በለጋሥነት ሀሰጠኝ ጌታ ከጠፊ ገንዘቤ ከአሥር አንዱን በታማኝነት አወጣለሁ ።
12. ለተጠራሁበት የጸጋ ሥጦታ እታመናለሁ ። ድንግል የሆነ ለድንግልና ፣ ባለትዳር እንደሁ ለትዳር ፥ ዲያቆን እንደሁ ለዲቁና ፤ መነኩሴ እንደሁ ለምንኩስና ፣ ጳጳስ እንደሁ ለጵጵስና ፥ ሊቀ ጳጳስ እንደሁ ለሊቀጵጵስና ፥ ለመታመን በቆመበት ቁርጥ ሕሊና የሚከፈትበትን ሁለንተናዊ የአጋንንት ጦርነት የሚታገሥ እርሱ ጌታን በቀራንዮ ያገዘው የቀራንዮ ሰው ነው ! ወዳጄ ሆይ ባለህባት የመንፈሳዊነት ደረጃ የምትገጥምህ መሰናክል ያቺ ለአንተ መስቀልህ ። ከመልካምነትህ ያልተናወጽህ እንደሆነ በእውነት ግርማ አይሁድን ታግሠህ ከክርስቶስ ጋር የቆምክ የመስቀሉ ሰው ነህ !
ርዕሰ ሊቃውንት አባ ገብረ ኪዳን
http://t.me/abagebrekidan
13.7K viewsÃńŧęŋəĥ, 07:40