Get Mystery Box with random crypto!

✞ስለእውነት ምን ይሻላል?✞✞ እውነትን ለማወቅ የሚፈልግ የለም እንጅ እውነትን ለማወቅ | የርዕሰ ሊቃውንት አባ ገብረ ኪዳን ትምህርቶች

ስለእውነት ምን ይሻላል?✞✞

እውነትን ለማወቅ የሚፈልግ የለም እንጅ እውነትን ለማወቅ ሁሉም ደፋ ቀና እያለ ነው። ስለ እውነት የሚጠይቁ የማይቆጠሩ ናቸው። ሰለ እውነት የሚመራመሩትስ ቢሆን! ስለ እውነት የሚዋኙ አሉ። ስለ እውነት የሚከንፉም እልፍ! ስለ እውነት የሚቆፍሩም ትእለፊት ናቸው። እውነት ግን በዚህ ሁሉ የለችም። ምክንያቱም እውነት አይፈልጓትም እንጅ አጠገባቸው አለችና። እውነት ልሳኗ እስኪዘጋ በረጅም ጩኸት አየጮኸች አቤት የሚላት የለም። ለእውነት ጆሮውን የደፈነው ሁሉ ግን ስለ እውነት ተመራማሪ ነው። አንድ ቀን አይቷት ቀርተቶ ሲያልፍ ድምጿ ጭር ያላለችበት ሁሉ የእውነት የልብ ወደጅ ነኝ ብሎ ስለ ራሱ ድርሰት ያስነብባል። እውነት ታማ አጠገባቸው እየረገጡ ወደ ውሸት ሠርግ እየሄዱ የእውነት ጠበቃ ይሆናሉ። ነብርን የፍየል፥ ጅብን የአህያ፥ ፍየልን የቅጠል፥ ቀበሮን የበግ ፥ዶሮን የጥሬ ፤ውሻን የቅቤ ጠበቃ የሚያቆማቸው ማን ነው? አንድ ሚ'ገርመኝ ነገር አለ። ድመትን ነምር ቢያባርራት። ድመትን አስጥሎ ራሱ ለመብላት ነው እንጅ እውነት ሳንባን ከድመት ለመጠበቅ ይሆናልን?

እውነት ቤት ውስጥ አለች ነገር ግን ሰዎች ከቤት ያስወጧት ዘንድ ሌሊት ከቀን እየጎሰሟት ስለ እውነት ግን ደግሞ በአደባባይ ይሰብካሉ። በውሸት ሻማ እውነትን ይፈልጋሉና የእድሜ ነፋስ ሻማውን ያጠፋውና እውነትን ሳያዩ ያሸልባሉ። አንገቱን ያቀረቀረ ሰማይን አያይም፤ ሥግብግብነት ያጎበጠው ሰውም በእውነት ሰማይ ላይ የሚያበራውን ጸሐይ አያይም። መድኀኒቱን በመርዝ ዕቃ ቢጠጡት ይገድላል እንጅ አያደንም። እውነትንም በውሸት መመርመር አይቻልም እውነትን እየሰቀሉ እውነትን ይመረምራሉ። በውሸት በሚኖሩም የውሸት መሞት ግን አይቻልም።

በእውነት ላይ ፍርድ እየፈረዱ እውነት ምንድን ነው ቢሉት ምን ዋጋ አለሁ? ይህቺ ዓለም
ስለ እውነት እየጠየቅን መልሱን ሳንሰማ እንድንወጣ በሁከቷ እድል ትነሳናለች።"ጌታ ኢየሱስም መልሶ እኔ ንጉሥ እንደሆንሁ አንተ ትላለህ። እኔ ስለ እውነት ልመሰክር ስለዚህ ተወልጃለሁ ስለዚህም ወደ ዓለም መጥቻለሁ፤ ከእውነት የሆነ ሁሉ ድምፄን ይሰማል አለው። ጲላጦስም እውነት ምንድን ነው አለው ይህንንም ብሎ ዳግመኛ ወደ አይሁድ ወጥቶ እኔስ አንዲት በደል ስንኳ አላገኘሁበትም።"ዮሐ፲፯፰፥፴፯
ጰላጦስ ስለ እውነት ጠይቆ ሳይመለስለት ለእውነት ጥብቅና ሊቆም ወጣ። ሳይጸናበትም ቀረና እውነትን ሰቀለ። እርሱ በጌታ ላይ በደል አለማግኘቱ ብቻ መስሎታል እውነት! ጌታ ግን የሌለበት ብቻ ሳይሆን ኃጢአትትን የሚደመስስ እውነተኛ አምላክም ነበር። ይህ ግን እሰከ ጊዜው ድረስ አልገባውም ነበር። እውነትን እሽ በጎ ላለማለት እድል የሚነሱት ገንዘብና ሥልጣን መጣበት ናቸው። ዓለም ለእውነት መኖር በሚፈልጉ ሰዎች ላይ ፈጥና ጉሮሯቸው ላይ ትቆማለች ወዲያውም የህልውና ጉዳይ አይደል ምን ይደረግ ታስብላቸዋለች። ማራጭ በማያቀርቡለት ኑሯቸው ለይ ትመጣለች። እነርሱም እውነትን ሳይውጧት ይቀራሉ። ጲላጦስ በከፊሉም ቢሆን ስለ እውነት ሲከራከር አይሁድ"እንግዲያውስ የቄሳር ወዳጅ አይደለህም" ነበር ያሉት። ያን ጊዜ ተብረከረከ። በሹመቱ መጡበታ!

ችግሩ ምንድን ነው። እውነት በጥልቀት ሳትገባው ስለ እውነት መቆሙ። ሳይገባው የወደደ ሳይገባው ይጠላል። ሳይገባው ያመነ፡ሳይገባው ይክዳል። እውነት ክርስቶስ ነው። ቄሳር የጲላጦስ ንጉሥ ቢሆንም ክርስቶስ ግን የቄሳር ፈጣሪ ነው። ስለዚህ ይህ ቢገባው አይሸበርም ነበር።
ሁለተኛ ስለ እውነት ሲኖር ይህ እንደማይቀርለት ማወቅ ነበረበት። ነገር ግን ይህ ሁሉ ባይቀርም በእውነት ነጻ መውጣቱ ደግሞ አይቀርም! ወተአምርዋ ለጽድቅ ወጽድቅኒ ታግዕዘክሙ=እውነትን ታውቃላችሁ እውነትም አርነት ያወጣችኋል" ዮሐ፰፥፴፪
ስለ እውነት እንድናውቅ እውነት እንዲገባን
ስለ እውነት ለመኖር እውነት እንዲመራን
እውነተኛው አምላክ በእውነት ይጠብቀን!
አባ ገብረ ኪዳን
http://t.me/abagebrekidan
http://t.me/abagebrekidan