Get Mystery Box with random crypto!

የጋብቻ ውል (አጫጭር የምልከታ ነጥቦች) ።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።። የጋብቻ ውል(C | AAU,School of Law Info Center⚖️

የጋብቻ ውል (አጫጭር የምልከታ ነጥቦች)
።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።
የጋብቻ ውል(Contract of marriage ) ማለት ምን ማለት ነው? ከጋብቻ ምስክር ወረቀት(Certificate of marriage) በምን ይለያል?

ጋብቻ የሁሉም መሠረት እንደመሆኑ በኢ.ፌ.ድ.ሪ ሕገ መንግሥት(constitution) እና ሌሎች ህጎች ሳይቀር ጥበቃ የተሰጠው ትልቅ ማኅበራዊ ተቋም(institution) ነው፡፡ የጋብቻ ውል(contract of marriage) ማለት ከጠቅላላው ውል ሕግ(Law of contract) ተነስተን ትርጉም የምንሰጠው አይደለም፡፡ ጋብቻ የሚፈጸመው መሃል ላይ የተለያዩ አጋጣሚዎች እንደተጠበቁ ሆነው እስከ ዕለተ ሞት ድረስ በአንድ ጣራ ስር አብሮ ለመኖር ነው፡፡ በዚሁ መሠረት የጋብቻ ውል የሚባለውም ተጋቢዎች ጋብቻቸውን በፈጸሙበት ዕለት ወይም ቀደም ብለው ጋብቻቸው እና አጠቃላይ ጋብቻቸው የሚያስከትለውን ውጤት ወስነው የሚያልፉበት ትልቅ ሰነድ ነው፡፡ በተሻሻለው የፌዴራል መንግስት የቤተሰብ ህግ አዋጅ ቁጥር 213/92 አንቀጽ 42 (1) ላይ የተመለከተውም ይሄንኑ ነው፡፡

የጋብቻ ውል ጥቅም ምንድን ነው?
ምናልባት ተጋቢዎች ትኩስ ፍቅር ላይ ሆነው ወደፊት ጸብ ሊኖር እንደሚችል አይገመቱም፡፡ ፍቅር እንዳለ ጸብም አለ፡፡ እነዚህ የማይነጣጠሉ ክስተቶች ናቸው፡፡ ከዚህ በመነሣት ተጋቢዎች ንብረታቸውን በሚመለከት (የግሉን በግል፣የጋራውን በጋራ) አድርገው የሚወስኑት በዚሁ የጋብቻ ውል ስለሆነ አለመግባባት ተከስቶ የንብረት ይገባኛል ጥያቄ እና ሙግት በሚነሣበት ወቅት ማስረጃነቱ እጅግ ጠቃሚ ነው፡፡ አንዳንድ የፍርድ ቤት ጉዳዮችን ስንመለከት ይህን ባለማድረግ የሚከሰቱ ጉዳዮችም ያጋጥማሉ፡፡ ተጋቢዎች ከጋብቻ በፊት የንብረታቸውን ሁኔታ ወስነው ካላለፉ ለወደፊት ለትዳራቸው አለመስማማት እና ለፍቺ ምክንያት ሊሆን እንደሚችል በመገንዘብ ቀድመው ሊያስቡበት የሚገባ ትልቅ ጉዳይ ነው፡፡
በፍርድ ቤቶች የሚታየው ክርክርም ቢሆን ባልና ሚስት የንብረታቸውን ጉዳይ የግል ንብረቶችን በግል፣የጋራውን ደግሞ በጋራ በየፈርጁ ለይተው ባለማስቀመጣቸው ምክንያት የንብረት ባለቤትነት የሚያሣጣ ባይሆንም ንብረት ያላፈራው ሰው ተጋሪ ሲሆን የምንመለከትበት ሁኔታ ያጋጥማል፡፡

በጋብቻ ውል የንብረታቸውን ጉዳይ ሳይወስኑ የተቀመጡ ተጋቢዎች ዕጣ ፈንታ ምንድንነው?
ተጋቢዎች ቢዘገይ በጋብቻቸው ዕለት ወይም ደግሞ ቀድም ብለው የንብረታቸውን ጉዳይ ወስነው ካላለፉ በትዳር ውስጥ ሆነው የንብረት ማግለል ውል ማድረግ ይችላሉ፡፡ በተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ አንቀጽ 73 መሠረት ውላቸውን ፍርድ ቤት አቅርበው ሊያጸድቁ ይገባል፡፡ በትዳር ውስጥ የሚደረጉ ውሎችን ፍርድ ቤት ሊያጸድቃቸው ይገባል፡፡ (ንብረት ማግለል፣ስጦታ፣ሽያጭ፣………) ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ተጋቢዎች በመካከላቸው የሚያደርጓቸውን ውሎች ውልና ማስረጃ በመውሰድ ተመዝግቦ እንዲረጋገጥላቸው ሲጠይቁ ይስተዋላል፡፡ ውልና ማስረጃም የዚህን ዓይነት የውል ስምምነት የመዘገበበት ሁኔታ ተስተውሏል፡፡ በዚህ ላይ ማረጋገጥ እና ማፅደቅ (authentication and ratification) የሚሉትን ነጥቦች መለየት ያስፈልጋል፡፡

ከጋብቻ የምስክር ወረቀት ጋር ልዩነቱ ምንድን ነው?
የጋብቻ ምስክር ወረቀት(certificate of marriage) ምን ማለት እንደሆነ ከመግለጻችን በፊት በሀገራችን ያሉትን የጋብቻ አፈጻጸም ሥርዓቶችን ማየት ያስፈልጋል፡፡ በሀገራችን ሦስት ዓይነዋና ዋና የጋብቻ አፈጻጸም ሥርዓቶች አሉ (በባህል(Custom) ፣ በሃይማኖት(religion) እና በክብር መዝገብ ፊት(Civil status) የሚፈጸሙ የጋብቻ አፈጻጻም ሥርዓቶች ናቸው)፡፡ ጋብቻው የተፈጸመው በየትኛውም የጋብቻ አፈጻጸም ሥርዓት ቢሆንም ጋብቻን በሚመዘግበው አካል ፊት ቀርቦ መመዝገብ አለበት፡፡ ይህ ነው የጋብቻ ምስክር ወረቀት የሚባለው፡፡ የጋብቻ ምስክር ወረቀት ተጋቢዎች ባልና ሚስት መሆናቸውን የሚያሣይ ሰርቲፊኬት ነው፡፡ ይህም በተሻሻለው የፌዴራል መንግሥቱ የቤተሰብ ሕግ አዋጅ ቁጥር 213/92 አንቀጽ 28/3/ ላይ ተመልክቷል፡፡
አንዳንድ ተጋቢዎች የባልና ሚስት ማስረጃ በሚጠይቁ ግልጋሎት ላይ በሃይማኖት ተቋም የተሰጣቸውን የጋብቻ ምስክር ወረቀት ሲያቀርቡ ይስተዋላሉ፡፡ ምሳሌ፡ ውልና ማስረጃ ላይ ይህን መታዘብ ይቻላል፡፡ ይህ በሃይማኖት ተቋም የሚሰጥ የጋብቻ ምስክር ወረቀት ተጋቢዎች በሃይማኖታቸው መሠረት(ከሦስቱ የጋብቻ አፈጻጸም ሥርዓት በአንደኛው) ጋብቻ የፈጸሙ መሆኑን የሚያሣይ ነው እንጂ በሕጉ የተቀመጠው የጋብቻ ምስክር ወረቀት(certificate of marriage ) አይደለም፡፡

Source: Document Registration and Authentication Office

@AAU_Lawschool