Get Mystery Box with random crypto!

የጋራ መኖሪያ ቤት ዕጣ የወጣላቸው ዕድለኞች የቁልፍ መረከቢያ ቅፅ በመውሰድ ላይ እንደሚገኙ ተገለፀ | A.A HOUSING DEVELOPMENT & ADMINISTRATION BUREAU

የጋራ መኖሪያ ቤት ዕጣ የወጣላቸው ዕድለኞች የቁልፍ መረከቢያ ቅፅ በመውሰድ ላይ እንደሚገኙ ተገለፀ

በ2015 በጀት ዓመት በወጣው 14ኛው ዙር የ20/80 እና 3ኛው ዙር 40/60 የቤት ልማት ፕሮግራሞች ዕጣ የወጣላቸው ዕድለኛ ነዋሪዎች የቁልፍ መረከቢያ ቅፅ በመውሰድ ላይ እንደሚገኙ ተገለፀ፡፡ እሰከ መጪው ሰኔ 20 ቀን 2015 ድረስ መውሰድ እንደሚችሉም ተጠቁሟል፡፡

የጋራ መኖሪያ ቤቶች ማስተላለፍ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ካሳሁን ዘውዴ እንደገለፁት በ14ኛው ዙር የ20/80 እና 3ኛው ዙር 40/60 የቤት ልማት ፕሮግራሞች ዕጣ የወጣላቸው ዕድለኛ ነዋሪዎች ቦሌ ክፍለ ከተማ በሚገኘው የቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን የአንድ ማዕከል አገልግሎት እየቀረቡ የቁልፍ መረከቢያ ቅፅ በመውሰድ ላይ ይገኛሉ፡፡

ዕድለኞች ቅፁን ለመረከብ ሲመጡ ከሚኖሩባቸው ወረዳዎች የተሰጠ የነዋሪነት መታወቂያ እንዲሁም ከባንክ ጋር የተዋዋሉበትን ዋናውን እና አንድ ፎቶ ኮፒ ይዘው በመቅረብ በወጣላቸው ፕሮግራም መሠረት እየቀረቡ መስተናገድ እንደሚችሉም አመልክተዋል፡፡

እስከ መጪው ሰኔ 20 ቀን 2015 ድረስ እየቀረቡ የቁልፍ መረከቢያ ቅፁን መውሰድ እንደሚችሉ የጠቆሙት አቶ ካሳሁን በዚህ ጊዜ ውስጥ ቅፁን መውሰድ ሳይችሉ የቀሩ ዕድለኛ ነዋሪዎች ቤቶቹ በሚገኙባቸው ክፍለ ከተሞች እየቀረቡ መውሰድ የሚችሉበት ምቹ ሁኔታ የተፈጠረ በመሆኑ ምንም ችግር አያጋጥማቸውም ብለዋል፡፡

የጋራ መኖሪያ ቤት ዕጣ የወጣላቸው ዕድለኞች ከአቅም በላይ በሆነ ምክንያት በግንባር ቀርበው መዋዋል የማይችሉ ከሆነ ከሚመለከተው ህጋዊ ተቋም የተሰጠ የውክልና ደብዳቤ ይዘው በመቅረብ በተወካዮቻቸው በኩል መዋዋል እንደሚችሉ ገልፀው የብድር ውል ላልተዋዋሉ እና ካርታ ላልታተመላቸው ዕድለኛ ነዋሪዎች አስፈላጊው ቅድመ ሁኔታ እየተዘጋጀ በመሆኑ ተረጋግተው እንዲጠብቁም አሳስበዋል፡፡

በዘንድሮው በጀት ዓመት በ14ኛው ዙር የ20/80 እና 3ኛው ዙር 40/60 የቤት ልማት ፕሮግራሞች ከ25 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ነዋሪዎች የጋራ መኖሪያ ቤት ዕጣ እንደወጣላቸው የሚታወስ ነው፡፡

http://www.aahdab.gov.et

https://www.facebook.com/aahdaboffic