Get Mystery Box with random crypto!

አዳማ ከተማ ወሳኝ ዝውውሮችን ፈፅሟል! በ2014 የውድድር ዘመን በሊጉ መቆየቱን ለማረጋገጥ የ | አድዬ የኔ.... / Adama Ketema F.C

አዳማ ከተማ ወሳኝ ዝውውሮችን ፈፅሟል!

በ2014 የውድድር ዘመን በሊጉ መቆየቱን ለማረጋገጥ የመጨረሻ ሳምንታት ጨዋታ ውጤቶችን ለመጠበቅ የተገደደው ክለባችን ለ 2015 የውድድር ዘመን አሰልጣኝ ይታገሱ እንዳለን በዋና አሰልጣኝነት ለማስቀጠል ከወሰነ በኃላ በዝውውር ገበያው እንብዛም ሲንቀሳቀስ ባለመታየቱ ብዙ መሻሻሎችን የሚሻው ቡድን ዝምታን መርጦ መቆየቱ በብዙዎች ዘንድ ቀጣይ የውድድር አመት በምን መልኩ ሊቀርብ ነው በሚል ጥያቄን ሲፈጥር የነበረ ጉዳይ ሆኖ ቆይቷል። ዘግይቶ ወደ ዝውውር ገበያ የገባው ክለባችን ክለቡን ያጠናክራሉ የተባሉ ወሳኝ አዳዲስ ዝውውሮችን ሲፈፅም የነባሮቹንም ውል አድሷል።

አንጋፋው የብሄራዊ ቡድናችን አማካይ መስኡድ መሀመድ መዳረሻው አዳማ ከተማ ሆኗል። የእግር ኳስ ህይወቱን ለመብራት ሀይል በመጫወት የጀመረው ባለ ብዙ ልምዱ አመለ ሸጋው ተጫዋች ያለፈውን የውድድር ዘመን በጅማ አባጅፋር ቆይታ ካደረገ በኃላ ለአዳማ ከተማ ለመጫወት ተስማምቶ ፊርማውን አኑሯል።

ብዙ ውዝግቦች የነበሩበት የዊልያም ሰለሞን ዝውውርም እልባት ሲያገኝ መዳረሻውን አዳማ ከተማ በማድረግ ተቋጭቷል። ወጣቱ የአማካይ ስፍራ ተጫዋች ከሲዳማ ቡና ጋር የቅድመ ውል ስምምነት አድርጎ የነበረ ቢሆንም እልህ አስጨራሹ የዝውውር ሂደት በመጠናቀቁ
ለቀጣዩ 2 አመታት በክለባችን መለያ የምንመለከተው ይሆናል።

ቦና አሊ እና አድናን ረሻድም በዝውውር መስኮቱ ክለባችንን የተቀላቀሉ ተጫዋቾች ሆነው ተመዝግበዋል። በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን ከሊጉ በተሰናበተው ጅማ አባጅፋር ቆይታ የነበራቸው ሲሆን ምንም እንኳን ክለቡ በሊጉ መቆየት ባይችልም በግላቸው ጥሩ የውድድር አመት ካሳለፉ በኃላ ቀጣዮቹን አመታት በክለባችን ለመቆየት ተስማምተው ፊርማቸውን አኑረዋል።

ግብ ጠባቂው ሰኢድ ሀብታሙ ጀማል ጣሰውን ተክቶ አዳማ ከተማ ደርሷል። ያለፈውን የውድድር አመት በወልቂጤ ከነማ ያሳለፈው ግብ ጠባቂው በቀጣይ በክለባችን የምንመለከተው ይሆናል።

ተከላካዩ ጀሚል ያዕቆብ ለተጨማሪ 2 አመታት ውሉን አራዝሟል። ያለፉትን 2 አመታት ከክለባችን ጋር ቆይታ የነበረው የቀኝ መስመር ተከላካዩ በሂደት በሚያሳየው ጥሩ ብቃት እና መሻሻል በደጋፊው እጅጉን ከሚወደዱ ተጫዋቾች መሀል እራሱን ማስቀመጥ ችሏል። ተጫዋቹ ውሉ መጠናቀቁን ተከትሎ በርካታ የዝውውር አማራጮች የነበሩት ቢሆንም ውሳኔው ግን ከአዳማ ከነማ ጋር ለመቆየት ሆኗል።

ክለባችን በቀጣይም ተጨማሪ ተጨዋቾችን ለማስፈረም በድርድር ላይ የሚገኝ ሲሆን ዝውውሮቹ እንደተጠናቀቁም ይፋ የምናደርግ ይሆናል።

ክለባችንን አስመልክቶ ትክክለኛ እና ቀዳሚ የመረጃ ምንጭ የሆነውን የፌስቡክ እና የቴሌግራም ቻናላችንን ይከታተሉ!
አድዬ የኔ. / Adama kenema
t.me/AAdamaa