2022-04-30 11:37:55
አየር ልቀቅ!
(Samuel Geda)
በአንድ ትልቅ የመኪና ማምረቻ ኩባንያ ውስጥ ተቀጥሮ የሚሠራ መሐንዲስ፤ በዐይነቱ ልዩ የሆነ፣ በተወዳዳሪነቱም የላቀ- አዲስ የመኪና ሞዴል ይነድፋል።
*
የድርጅቱ ባለቤትም በውጤቱ እጅጉን በመደነቅ ምስጋናን ይቸረዋል።
*
ይሁንና መኪናውን ከማምረቻ ሥፍራ ወደ ማሳያ ክፍል (showroom) ለመውሰድ በሚሞክሩበት ጊዜ፤ አዲሱ መኪና ከመግቢያው በር በ10 ሳ.ሜ እንደሚረዝም ይረዳሉ።
*
መሐንዲሱም፤ ቀድሞውኑ የመኪናውን ንድፍ ሲሠራ ይህንን ግንዛቤ ውስጥ ባለማስገባቱ ይተክዝና ያዝን ጀመር።
*
የድርጅቱ ባለቤትም መኪናውን ከማምረቻ ሥፍራ እንዴት እንደሚያወጣው ግራ ይገባዋል።
*
ይህን ጊዜ ቀለም ቀቢው ተነሥቶ፤ "መኪናውን ሊያወጡት እንደሚችሉና በመኪናው ላይኛው ክፍል ብቻ ትንሽ ጭረት እንደሚኖር እሱም ቢሆን ከወጣ በኋላ በቀለም ሊስተካከል እንደሚችል" በመናገር ተስፋን ይሰጣል።
*
ለጥቆ መሐንዲሱ፤ "የመግቢያውን በር ሰብረው መኪናውን ማውጣት እንደሚችሉና መልሰውም በሩን እንደሚጠግኑት" ይናገራል።
*
ይሁንና የኩባንያው ባለቤት የተነሱት የመፍትሄ ሐሳቦች በመላ አልተዋጡለትም፤ መኪናው ላይ የሚደርሰው ጭረትም ሆነ የመግቢያውን በር መስበሩ መልካም መስሎ አልታየውም።
*
ታዲያ ይህ ሁሉ ሲሆን ዳር ቆሞ ሲታዘብ የነበረው የኩባንያው ጥበቃ ሠራተኛ በዝግታ ወደ ባለቤቱ ይጠጋና የሚቻል ከሆነ በነገሩ ላይ ሐሳብ ለመስጠት እንደሚፈልግ ይናገራል።
*
ኃላፊውም የጥበቃ ሠራተኛው የነገራቸው ኤክስፐርቶች ሊሰጡ ያልቻሉትን በመሆኑ እጅጉን ተደነቁ።
*
ጥበቃው የተናገረው፤ "መኪናው ከመግቢያው በር በትንሽ ሳ.ሜ ከፍታ ብቻ ነው የሚረዝመው፤ ስለዚህ በቀላሉ በጎማው ያለውን አየር ስትለቁ የመኪናው ቁመት ይወርዳል፤ በቀላሉም መውጣት ይችላል" የሚል ነበር።
*
ሁሉም በአንድ እጅ አጨበጨቡ!
* * *
ልብ በል፤
• አንድን ችግር ከባለሙያ/ኤክስፐርት እይታ ብቻ ተነስተህ ለመተንተን ወይም ለመፍታት አትሞክር።
• ሁልጊዜም ቢሆን "ተራ" ከሚባል ሰው ለወሳኝ ሁነት የሚሆን ጠቃሚ መልስ እንዳለ አትዘንጋ።
• ጥበብ በትህትና የምትሸመት ገንዘብ መሆኗን ልብ በል።
• አንድን ጥያቄ የሚያከብደውም የሚያቀለውም የነገሩ ውስብስብነት ሳይሆን ችግሩን የምትፈታበት መንገድ መሆኑን አስተውል።
የህይወት ነገርም እንዲሁ ነው.. ቀለል አድርገህ አስብ። ቀላል ነገር ሥራ፤ በቀላሉም ኑር! ምክንያቱም 'ተሞልተን' ነው እንጅ እኛ በተፈጥሮ መልካም ሰዎች ነን።
ይኸውልህ፤ አንተ በጠጣኸው መርዝ ሌላው እንዲሞት መቼም አትጠብቅም፤ ውስጥህን የሞላው 'አየር' ያንተን እጣ ፈንታ ይወስናል። ። ምናልባት ይህ አየር (ንዴት፣ ጸጸት፣ ግራ መጋባት፣ ቂም፣ ጥላቻና በቀል) ጉዞህን ገቶት፣ ነገህን አጨልሞት፣ እርምጃህን ገድቦት፣ ተስፋን አሳጥቶ፡ ሩቅ አልመህ ሩቅ እንዳታድር አድርጎህ... ይሆናል።
የተሞላኸውን አየር ልቀቅ። ስትለቅ የሚለቅና የሚለቀቅ ነገር አለ። ያን ጊዜ አላልፍም ካልክበት ሁኔታ ልታልፍ፣ አልወጣም ካልክበት ማጥ ልትወጣ ትችላለህ። አየህ በስተመጨረሻ ሁሉም ነገር "ቁመትን/አስተሳሰብን ማስተካከል" ይሆናል፤ በውጤቱም- የውስጥ ሰላምን፣ ጤናማ አስተሳሰብን፣ ስኬትንና ደስታን... ማጣጣም ትችላለህ!!
@zikiretibeb
@zikiretibeb
244 viewsፌዮዶር. ዶስቶዬቭስኪይ , 08:37