Get Mystery Box with random crypto!

የብርቱካን ሚደቅሳው ምርጫ ቦርድ ያስቀጠለው ፥ የትኛውን የመርጋ በቃና ሌጋሲ ነው? በወ/ሪት ብር | ዘሪሁን ገሠሠ

የብርቱካን ሚደቅሳው ምርጫ ቦርድ ያስቀጠለው ፥ የትኛውን የመርጋ በቃና ሌጋሲ ነው?

በወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ የሚመራው ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ፥ በተስፋ አስቆራጩ የኢትዮጵያ የመድብለ ፓርቲና የዴሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ ውስጥ በአሰራር ረገድ እንኳ ጥቂትም ቢሆን የተስፋ ብርሀን ፍንጣቂን ሊያሳየን በመቻሉ ፥ ለዴሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታው እጅግ አስፈላጊ የሆኑት ተቋማት "ተቋም" እንዲሆኑና እንዲጎለብቱ እንደሚሻ ዜጋ "በርቱ ፥ ተበራቱ …!" ብለን በይፋ አጋርነታችንን ሰጥተናል፡፡

ነገርግን ከዚህ ቀደም በነበሩበት እነመርጋ በቃናና አዲሱ ገ/እግዚያብሔርን መሠል የኢህአዴግ ሠዎች ይመራ እንደነበረውና "የኢህአዴግ ቁ.2 ፅ/ቤት" እስከመባል የደረሰው ምርጫ ቦርድ ፥ በመንግሥት እዝና ፖለቲካዊ ተፅእኖ ውስጥ ገብቶ ፥ የተሻለ ተገዳዳሪነትና ህዝባዊ ቅቡልነት ያላቸውን የፖለቲካ ድርጅቶችን "ድምፅ አልባ ሞት" እንዲሞቱና በሂደት ተዳክመው ህዝባዊ ቅቡልነት እንዲያጡ ፥ ሲያደርግ የነበረው ስትራቴጂካዊ ሌጋሲ ፥ ሂደቱ ፣ ስልቱና አፈፃፀሙ ቢለያይም ፥ በወ/ሪቷ በሚመራው ቦርድም ተጠናክሮ የቀጠለ ይመስለኛል፡፡

በኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች ታሪክ "ቅንጅት" ኃላም "አንድነትን" የመሠሉ ሠፊ ህዝባዊ ቅቡልነትና አደረጃጀት የዘረጉ ፓርቲዎችን ፥ የቁም ሞት እንዲሞቱ አድርጎ ፥ ስያሜአቸውን " አየለ ጫሚሶና ትእግስቱ አወሉ" ለሚባሉ የሳምሶናይት ፓርቲ ተረካቢዎች በመስጠት የዴሞክራሲያዊ ትግሉን ተስፋ አስቆራጭና እምነት የማይጣልበት ካደረጉት ኃይሎች መካከል የምርጫ ቦርድ ሚና ከፍተኛው ነበር፡፡ ከዚያ በኃላም በሠማያዊ ፣ በመኢአድ ፣ ….ወዘተ ፓርቲዎች ውስጥ ፥ ሶኬቱ ከገዢው የኢህአዴግ/ህወሓት ስልጣን ስር የተሰካው የምርጫ ቦርድ እጅ እንደነበር የሚካድ አይደለም፡፡

በሌላ መልኩ ጠንካሮቹን ካኮሰመኑ ፥ ከፋፍለውና ለመንግሥት እጅ አስታጣቢ ሊሆን ለሚችለው አካል በገፀ-በረከትነት ከሰጡ በኃላ ፥ እርባና ቢስና በያኔው አገላለፅ "አጋር ፓርቲ" ተብለው ለምርጫ ጊዜ ብቻ የሰርተፍኬታቸውን አቧራ አራግፈው " ብቅ " የሚሉ "ኢሰዴፓን" መሠል የግለሰቦችና የቤተሰብ ድርጅቶች "ፓርቲ" ተብለው ፥ የመሮጫ ትራኩና የፌክ ትግል መድረኩ እንዲመቻችላቸው የማድረጉንም ሀላፊነት ምርጫ ቦርድ ከፊት ሆኖ ይመራው እንደነበርም የሚታወስ ነው፡፡

በቅርቡ የመነቃቃት ሂደትን አሳይቶ በነበረው የፓርቲዎች የሰላማዊ ትግል እንቅስቃሴ ውስጥ ፥ ሰፊ ህዝባዊ መሠረትና ቅቡልነት ማትረፍ ከቻሉት ፓርቲዎች መካከል የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) እና የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ግንባር ቀደም ተጠቃሾች ናቸው፡፡

የእነዚህ ፓርቲዎች አብዛኛው ችግር ውስጣዊና የአመራር ችግር ሲሆን ፥ ይህን ችግር በመፍጠር ረገድ መንግስት ለምክንያት የሚጠቀስ አስተዋፅኦ አለው፡፡ ነገርግን የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄን በሚመለከት በተለየ ሁኔታ የምርጫ ቦርድ "ፓርቲውን ድምፅ አልባ በሆነ መልኩ ቀስ በቀስ እንዲሞት ህግን ባለማስከበር ፥ ውሳኔን ባለማስተግበር ብሎም ሀላፊነትን ባለመወጣት በጉልህ ተባባሪ ሆኖ እየተመለከትነው እንገኛለን፡፡

በመሆኑም ፦ እነዚህ ፓርቲዎች ከምርጫ በኃላ ያሉበት ሁኔታ ምን ይመስላል ? የፓርቲዎቹ ውስጣዊና ውጫዊ ተግዳሮትስ ከቅንጅትና ከአንድነት ፓርቲዎች በምን ይመሳሰላል? በምንስ ይለያያል ? በተለይ ከሁለቱ ፓርቲዎች በውስጣዊና በውጫዊ ፈተና ውስጥ የወደቀው አብንን በሚመለከት የምርጫ ቦርድ አስተዋፅኦ ምንድን ነው ? ህዝባዊ ቅቡልነት በማጣት ረገድ ሁለቱም ተመሳሳይ ቢሆኑም ፥ ጉባኤውን አካሂዶና በምርጫ ቦርድ ሂደት ካለፈው ኢዜማና ጉባኤውን በተደጋጋሚ ሞክሮ ማድረግ ካልተሳካለት አብን እጅግ አሳሳቢ ሁኔታ ውስጥ ያለው ማን ነው ? የአብን ጉዳይስ ለምን እጅግ ተጠባቂና ሰፊ መነጋገሪያ አጀንዳ ሆነ ? ምንስ መደረግ አለበት ?

በቀጣይ የምመለስባቸው የሀሳብ መነሻ ጥያቄዎቼ ይሆናሉ!

ሠላም!