Get Mystery Box with random crypto!

መንግስታዊ ሽፋን የተሠጠው ረፍት-የለሽ ፍጅትና የኦሮሚያ ክልል! ባለፈው በአርሲ ዞን በጀጁ ወ | ዘሪሁን ገሠሠ

መንግስታዊ ሽፋን የተሠጠው ረፍት-የለሽ ፍጅትና የኦሮሚያ ክልል!

ባለፈው በአርሲ ዞን በጀጁ ወረዳ መንበር ሂወት ከሚባል አካባቢ ጭፍጨፋ ከመፈፀሙ አስቀድሞ " ተከበናል ድረሱልን" ሲሉ ነዋሪዎቹ አስተጋቡ፡፡ የክልሉ ልዩ ሀይል ለይስሙላ ወደአካባቢው መጥቶ ማህበረሰቡ በሬ እያረደ ጭምር ሲንከባከበው ቆይቶ ፥ ልክ ጭፍጨፋው በተፈፀመበት እለት ነዋሪዎች "አትውጡብን" እያሉ "ሌላ ግዳጅ አለብን!" ብለው ሲወጡ ፥ ወዲያውኑ ጨካኙ ቡድን ያንን ግፍ ፈፀመ፡፡

በተመሳሳይ ትናንት በዚሁ አካባቢ አዲስ ህይወት ቀበሌ አንዲት እናትን ከነህፃን ልጇ ጨምሮ 9 ሰዎች አሰቃቂ ሁኔታ ማንነትን መሠረት ያደረገ ጭፍጨፋ ሲፈፀምባቸው የክልሉ ልዩ ሀይል በስፍራው አልነበረም፡፡ እርግጥ ነው ቢኖርም አንዳች ነገር እንደማያደርግ አለያም ተባባሪ ሊሆን እንደሚችል ጭምር ፥ ላለፉት አመታት ከደረሱት የጉሊሶን መሠል እልቂቶችና የዘር ፍጅቶች መገንዘብ እንችላለን፡፡

በኦሮሚያ ክልል ላለፉት ከአራት በላይ አመታት ያለእረፍት በየቀኑ ፍጅት እና እልቂት እየተፈፀመ ፥ ሚሊየኖች የሞት ስጋት አንዣቦባቸው ፣ ሚሊየኖች እየተሳደዱ ባለበት ሁኔታ የዜጎችን ሰላምና ደህንነት የማስጠበቅ ተቀዳሚ ሀላፊነት ያለበት የፌደራሉም ሆነ የክልሉ መንግስት ማስቆም አለመቻላቸውም ሆነ አለመፈለጋቸው ጭፍጨፋውን በመንግስታዊ ሽፋን የሚፈፀም የዘር ማጥፋት ያደርገዋል፡፡

በዳቦ ስሙ "ኦነግ ሸኔ" እየተባለ የሚጠራው ጨፍጫፊ ሀይል ራቅ ካሉት የኦሮሚያ ክልል አካባቢዎች አልፎ ፥ ለማዕከላዊ መንግስት መቀመጫዋ አዲስአበባ አቅራቢያ ባሉ የምዕራብና የምስራቅ ሸዋ ዞኖች ውስጥ በሚገኙ አካባቢዎች መሠል እልቂትና ሽብር እየፈፀመ እንዳሻው መንሰራፋቱ የክልሉን መንግሥት መፍረስ በግልፅ የሚያስረዳ ነው!

የኢትዮጵያ የሠብዓዊ መብት ኮሚሽን ፥ አለምአቀፍ ተቋማት ፥ የተለያዩ የሲቪል ማህበራት እንዲሁም የፖለቲካ ፓርቲዎች ጭምር ፥ ይህን ለአመታት የተለመደ ዜና የሆነ ማንነት ተኮር የዘር ፍጅትና ጥቃት ለማስቆም ብሎም ከጉዳዩ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያላቸው የመንግሥት አመራሮችን ጨምሮ አጥፊዎች ለፍርድ እንዲቀርቡ ያላሰለሰ ጥረት ማድረግ ካልቻሉ ይህ ሁኔታ በቀጣይ ሀገር ሊያፈርስ ብሎም የእያንዳንዳችንን ቤት ሊያንኳኳ የሚችል ብሔራዊ የደህንነት ስጋት መሆኑን መገንዘብ ያሻል፡፡

ፈጣሪ የሟቾቹን ነፍስ ይማር!