Get Mystery Box with random crypto!

የኢትዮጵያን ጀርባ ያጎበጠው ዕዳና የአበዳሪዎች እጅ ጥምዘዛ አሳሳቢ ደረጃ ደርሷል! ኢትዮጵያ ላ | ዘሪሁን ገሠሠ

የኢትዮጵያን ጀርባ ያጎበጠው ዕዳና የአበዳሪዎች እጅ ጥምዘዛ አሳሳቢ ደረጃ ደርሷል!

ኢትዮጵያ ላለፉት ሶስትና ከዚያ በላይ አስርት አመታት ከአለምአቀፍ ዋና ዋና አበዳሪዎች ከተበደረችው ብድርና ከነበረባት እዳ በእጥፍ የሚሆነውን የተበደረችው ባለፉት አራት አመታት ውስጥ ብቻ ነው፡፡ ሀገሪቷ ከገጠማት የፖለቲካ አለመረጋጋትና ጦርነት ባሻገር በዲፕሎማሲው ዘርፍ የገጠማት ውድቀት ጋር ተዳምሮ ኢኮኖሚው እጅግ አሳሳቢ በሆነ ፈተና ውስጥ የወደቀ ሲሆን ፤ ከፍተኛ የዋጋ ግሽበትና የኑሮ ውድነትም የህዝቡን ዳቦ አግኝቶ የመኖር እጣፋንታ አጣብቂኝ ውስጥ የከተተበት ሁኔታ በጉልህ እየተስተዋለ ነው፡፡

በተለይም ሀገሪቱ ከአመት በፊት ጀምሮ ፤ በምእራባውያን አበዳሪዎች በኩል በቅድመ ሁኔታዎች የተያዘባትን ብድር ለማስለቀቅና በአመት መክፈል የሚጠበቅባትን 5 ቢሊየን ዶላር መክፈል ባለመቻሏ የመክፈያ ጊዜ እንዲራዘምላት በተደጋጋሚ ስትጠይቅ እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ የውጭ ብድር አከፋፈል ጫና እፎይታን ለማግኘትና የተያዘባትን ብድር ለማስለቀቅ ከአለም ባንክና የአለማቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይኤምኤፍ) ጋር ውይይቶችንና ድርድሮችን እያደረገች ሲሆን ከሰሞኑ እንኳ የገንዘብና የኢኮኖሚ ሚንስትሩ አቶ አህመድ ሺዴ ወደአሜሪካ ያቀኑበትን ሁኔታ መጥቀስ ይቻላል፡፡

አለምአቀፍ የገንዘብ ተቋማቱ ለኢትዮጵያ ተጨማሪ ብድር ለመስጠትና ያለባትን እዳ የመክፈያ ጊዜ ለማራዘም ከዚህ ቀደም ሲያስቀምጣቸው የነበሩት ቅድመ ሁኔታዎች አሁንም ተጠናክረው በመቀጠላቸው የሀገሪቱን ኢኮኖሚና መሰረታዊ እንቅስቃሴ ፈታኝ ሁኔታ ውስጥ እየከተተው ይገኛል፡፡

የዛሬ አመት በነበረው መረጃ መሠረት ኢትዮጵያ በጥቅሉ ከ30 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር የሚልቅ የውጭ ብድር የነበረባት ሲሆን ከዚያ ውስጥ 22 ቢሊየን ዶላሩ ከሀገራትና እና ከብዙሀን አበዳሪዎች (bilateral and multilateral) የተወሰደ ብድር ነበር። 3.3 ቢሊየን ዶላሩ ደግሞ ኢትዮጵያ በፈረንጆቹ 2014 በዩሮቦንድ ከግል አበዳሪዎች የወሰደችውን አንድ ቢሊየን ዶላርን ጨምሮ ከሌሎች የግል አበዳሪ ተቋማት የወሰደችው ሲሆን 2.3 ቢሊየን ዶላሩ ደግሞ በመንግስት ዋስትና ሰጭነት እንደኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይል አይነት ተቋማት የወሰዱት ብሎም ቀሪው 3.3 ቢሊየን ዶላሩ ደግሞ ያለመንግስት ዋስትና በኢትዮጵያ አየርመንገድና ኢትዮ-ቴሌኮም አይነት ኩባንያዎች ከውጭ አበዳሪዎች የተወሰደ ብድር ነበር።

መንግስት በወቅቱ ይህን ብድር ለመክፈል በማይችልበት ደረጃ መሆኑን ጠቅሶ በወቅቱም መክፈል የነበረበት 5 ቢሊየን እዳ የመክፈያው ጊዜ ሳምንት ብቻ ቀርቶት የነበረ በመሆኑ አበዳሪ ሀገራቱ የእዳ መክፈያ ተጨማሪ ጊዜ እንዲሰጡትና የተያዘበት ብድርም እንዲለቀቅለት ለአለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም ቢማጸንም ያኔ በቀረቡትና ዛሬም በቀጠሉት የአበዳሪዎች ቅድመ ሁኔታ ምክንያት ለሀገር በቀል ኢኮኖሚያዊ ማሻሻያ በሚል የሶስት አመት ፕሮጀክት ሊለቀቅ የነበረውን ወደስድስት ቢሊየን ዶላር ጨምሮ በርካታ የብድር ጥያቄዎችን ሳይፈቅዱ በማጉላላት መቆየታቸው የሚታወቅ ነው፡፡

አለም ባንክ ከሰሞኑ ይፋ ባደረገው መረጃ መሰረት በአሁኑ ሰአት የሀገሪቱ ኢኮኖሚና የዋጋ ግሽበት አሳሳቢ ደረጃ መድረሱንና ፤ የዜጎች የድህነት ደረጃ በከፍተኛ ፍጥነት ወደተባባሰ ድህነት ደረጃ ማደጉን ገልፆ በተለይም የብሄራዊ ባንክ ተቀማጭ የዶላር መጠን ከአንድ ወር በታች ለሆነ ጊዜ ብቻ የሚያገለግል ብቻ መቅረቱ አሳሳቢ መሆኑን አጋርቷል፡፡

የመንግስት ከፍተኛ የብድር ፍላጎት መጨመር ፤ አለማቀፋዊው የኢኮኖሚ መታወክ በተለይ ደግሞ የሀገሪቱ ያልተረጋጋ ውስጣዊ ፖለቲካና የዲፕሎማቲክ አቅም መዳከም ፤ ከጦርነቱ ጋር ተዳምሮ ሀገሪቱን አጣብቂኝ ውስጥ የከተታት ሲሆን ፤ መንግስት ይህን ለማረምና ለማስተካከል የሚወስደው የተጠና የመፍትሄ አማራጭ አለመኖር ችግሩን ከጊዜ ወደጊዜ እየተባባሰ እንዲሄድ አድርጎታል፡፡ ለብሄራዊ ጥቅማቸው መከበር አሸባሪው ትህነግን በስውር የሚደግፉት ምእራባውያን ፤ ከመንግስት የተዳከመ የዲፕሎማቲክ ግንኙነት ጋር ተደምሮ ፤ አበዳሪ ሀገራቱንና የገንዘብ ተቋማቱን እንደእጅ መጠምዘዣና ማስገደጃ እየተጠቀሙባቸው ይገኛሉ፡፡

እንደሚታወሰው ጠ/ሚ አብይ ወደስልጣን ከመጡበትና ‹‹ለውጥ›› እየተባለ ከሚጠራው ጊዜ ወዲህ ሀገሪቱ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ አለማቀፋዊ እዳዋ በእጥፍ አድጎ ይገኛል፡፡