Get Mystery Box with random crypto!

የውክልናው ጦርነትና የገባንበት አጣብቂኝ ሀገራዊ የሀይል አሰላለፍ! 'አሸባሪው ትህነግና መንግ | ዘሪሁን ገሠሠ

የውክልናው ጦርነትና የገባንበት አጣብቂኝ ሀገራዊ የሀይል አሰላለፍ!

"አሸባሪው ትህነግና መንግሥት በአንድ ላይ ሆነው ኤርትራን የሚወጉበት አጋጣሚ ሊፈጠር ይችላል ብሎ ማሰብ የዋህነት ሊመስለን ቢችልም…! "

ገዢው መንግሥት የሚከተለው የተደበላለቀ የዲፕሎማቲክ የሀይል አሰላለፍ እና መሀል ሰፋሪነት በቀጣይ ምስራቅ አፍሪካን ለሁለት ጎራ ከፍሎ ወደተራዘመ የትርምስ ቀጠናነት እንዳይቀይረው እሰጋለሁ፡፡

አሜሪካና የአውሮፓ ህብረት በቀንድ አፍሪካ ላይ ያላቸውን የበላይነትና ጥቅም ለማስከበር በተለይም ሀያላኑ ሀገራት ብሎም የመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት በሁለት ጎራ ተከፍለው የቀይ ባህርን ፖለቲካ በብቸኝነት ለመቆጣጠር የሚያደርጉት ሽኩቻ ፥ ምዕራባውያኑ ህወሓትን በማጠናከር በይፋ ከሩሲያ ጎን የተሰለፈችውን ኤርትራን እንዲወጋላቸው ያለእረፍት መስራታቸውን ይቀጥላሉ፡፡

በዚህ አሰላለፍ ውስጥ ምዕራባውያኑ የብልጽግና መንግሥት ከኤርትራ ጋር የጀመረውን ስትራቴጂክ አጋርነት በመተው ከህወሓት ጋር ተደራድሮ በመስማማት ኤርትራን እንዲወጉላቸው ያላቸውን ፍላጎት መረዳት እጅግ ቀላል ነገር ነው፡፡

በዚህ ሂደት የኢትዮጵያ መንግስት የጠራ አሰላለፍ የሌለው በመሆኑ አሜሪካ ከሰሞኑ እንኳ በኢትዮጵያና በአሸባሪው ትህነግ ዙሪያ የጎንዮሽ አደራዳሪነት ሚናን በመውሰድ በጅቡቲ እንዲደረጉ ያደረገቻቸው የከሸፉ ሚስጥራዊ ድርድሮች ለዚህ ማሳያዎች ናቸው፡፡

በመሆኑም መንግሥት አንዱን ጎራ በመምረጥ አጣብቂኝ ውስጥ የገባበት ሁኔታ ባለበትና ጦርነቱ በቀጠለበት ሁኔታ ፥ ምእራባውያኑ ህወሓትን በሁለንተናዊ መልኩ የማስታጠቅና የማጠንከር ተግባራቸውን አጠናክረው የሚቀጥሉ ሲሆን ለዚህ የውክልና ጦርነት ደግሞ ሱዳንና ጅቡቲን እንደድልድይ መጠቀማቸው አይቀሬና እየተስተዋለም ያለ ጉዳይ ነው፡፡

ታዋቂው አሜሪካዊ የሞስኮ (ሩሲያ) የፖለቲካ ተንታኝ አንድሪው ኮሪብኮ ፥ << በኢትዮጵያ ላይ በተከፈተው ድብልቅልቅ ጦርነት ውስጥ የአውሮፓ ህብረት እና አሜሪካ ሱዳንን እንደ ተኪዎቻቸው እየተጠቀሙባት ነው! >> በማለት ሱዳን ለህወሓት ትጥቅ ለማስታጠቅ ለሚደረጉ በረራዎች እንደመተላለፊያ ድልድይ ሆና በምዕራባውያን መመረጧን ያተተበት ሁኔታ ለዚህ በቂ ማሳያ ነው፡፡

በሌላ መልኩ ከጊዜ ወደጊዜ እየሻከረ የመጣው የጅቡቲና የኤርትራ የዲፕሎማቲክ ግንኙነትና ጅቡቲ ከሰሞኑ ወታደሮቿን ወደኤርትራ ድንበር ማስጠጋቷ ፥ የምእራባዊያን በአፍሪካ ቀንድ ላይ የሚከተሉት አሰላለፍና ቀጣይ የውክልና ጦርነቱ ድግስ አንድ ማሳያ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡

በሌላ መልኩ ገዢው መንግስት ከገጠመው አለማቀፋዊ የዲፕሎማሲ መታጎልና ኪሳራ ባሻገር ውስጠ - ፖለቲካውን መቆጣጠርና መምራት አለመቻሉ ይዞት የሚመጣው መዘዝ ትንሽ ገዘፍ ያለ ሊሆን ይችላል፡፡

በተለይም ከጦርነቱ አጋማሽ በኃላ ህወሓት የኤርትራና የአማራ ህዝብ ብቻ ቋሚ ጠላት እንደሆነ በመገምገም ፥ " ሁለቱ ህዝቦች የሚኖራቸው ስትራቴጂክ አጋርነት ለስልጣኔ ያሰጋኛል" በሚል ስሁት ብያኔ ፥ ብሎም የጦርነቱ የመጀመሪያው ምእራፍ መጠናቀቅ በኃላ ከኤርትራ ጋር "የወጪ ኪሳራ ስሌት" ጋር በተያያዘ የተፈጠሩ ጉልህ ያልሆኑ መቃቃሮችና የሚያራምደው የመሀል ሰፋሪ አሰላለፍ እንዲሁም የኤርትራ መንግሥት የአማራን ወጣቶች ወታደራዊ ስልጠና ለመስጠትና ለመደገፍ በግልፅ አቋም መያዙ ፥ የሁለቱን ሀገራት መፃኢ ግንኙነት ወደውጥረት እየከተተው እንደሚገኝ ከሁኔታዎች መገንዘብ ይቻላል፡፡ በነገራችን ላይ በአማራ ክልል ከፋኖ ጋር በተያያዘ መንግሥት የሚያራምደው አቋም ከዚህ ጋር የተያያዘ ነው፡፡

በመሆኑም ገዢው መንግሥት አንድም ከምዕራባውያኑ ጎራ በይፋ መነጠልና በእነሱ በኩል የሚመጣን ማንኛውም አደሳዳሪነትም ሆነ ግንኙነት መዝጋት አለያም በእነሱ ምክረ-ሀሳብ መስማማት በሚሉ ሁለት አማራጮች ውስጥ እንደወደቀ ይሰማኛል፡፡

በዚህ ሁኔታ "አሸባሪው ትህነግና መንግሥት በአንድ ላይ ሆነው ኤርትራን የሚወጉበት አጋጣሚ ሊፈጠር ይችላል" ብሎ ማሰብ የዋህነት ሊመስለን ቢችልም ፥ መንግሥት አሰላለፉን በምዕራባውያን በኩል ካደረገ ደግሞ ከህወሓት ጋር በሚያቀርቡት ሀሳብ መሠረት ተስማምቶ ፥ በቀጣይ ኤርትራን በይፋ እንዲወጋ ፍላጎት እንደሚኖራቸው ፥ ዛሬ እብደትና የማይመስል ድስኩር ቢመስለንም ውለን እያደርን የምናረጋግጠው ያፈጠጠ እውነታ መሆኑ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡

በዚህ መሀል የአማራ ህዝብና የሀገሪቱ መፃኢ እጣፋንታ ምን ያህል ፈታኝ ሁኔታዎች እንደተጋረጠባቸው በበቂ ሁኔታ መገንዘብ ይቻላል፡፡

ሠላም!