Get Mystery Box with random crypto!

ፖለቲካዊ አላማ ፥ ግብና የሀሳብ መስመርህ  የጠራ ከሆነ ፥ ባልተራዘመና ባልተንዛዛ ትግል አሸናፊ | ዘሪሁን ገሠሠ

ፖለቲካዊ አላማ ፥ ግብና የሀሳብ መስመርህ  የጠራ ከሆነ ፥ ባልተራዘመና ባልተንዛዛ ትግል አሸናፊ ትሆናለህ! 

በረዥም ጊዜ ግላዊ ግምገማዬ ፥ በተለይ በኢትዮጵያ ፖለቲካ አብዛኛዎቹ " የሚያስፈልገን ጥገናዊ ለውጥ እንጂ ስር ነቀል ለውጥ አይደለም!" ብለው የሚያምኑ reformist ሀይሎች አድርባይና በተቃውሞው ጎራም ሆነ በገዢው ሀይል እኩል መወደድ የሚሹ መሀል ሰፋሪዎች ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡ 

የኢትዮጵያን በጥላቻ ትርክት ላይ የተመሠረተ የፅንፈኞች ደም አፋሳሽና አውዳሚ ፖለቲካዊ ስርአት ፥ በዘመን ሂደት ውስጥ በሚገባ ለገመገመ ግን ፖለቲካችንም ሆነ ሀገረ-መንግስታዊ ስርአቱ የሚያስፈልገው  ስር-ነቀላዊ ለውጥ (revolution ) መሆኑን በውል ይረዳዋል፡፡

"ብአዴናዊነት እኩይ የአስተሳሰብ ደዌ ነው!" ብለህ ከተረዳህ ፥ ትግልህ ይሄን አስተሳሰብ ነቅሎ መጣል ላይ ብቻ ያተኩራል፡፡ ይህን አቋም ይዘህ ሳለ አንድ የሰፈርህ ወይም ጓደኛና ዘመድህ የሆነ የስርአቱ ካድሬ ሲነካ " ጎጤ ተነጥሎ ተጠቃ!" ብለህ "እሪታ"  የምታቀልጥ ከሆነ ትግልህ የሀሳብ ጥራት የለውም አንተም አቋምና አላማ የለህም ማለት ነው፡፡ ከዚያ ሹማምንት (ድርጅት) በምታገኘው ግለሰባዊ ጥቅምና በውስጥህ ካለው የለውጥ ፍላጎት መካከል ሆነህ እያንገላጀህ ነው ማለት ነው፡፡ 

የብአዴናዊነትን አስተሳሰብ ጠላህ ማለት በውስጡ ያሉትን ጠንካራም ሆኑ ደካማ ሰዎች ጠላህ ማለት አይደለም፡፡ ፖለቲካዊ ትግልህ ከአስተሳሰብና ከስርአት እንጂ በወንድሞችህ የመረረ ጥላቻ መለከፍና መታወር ሊሆንም አይገባም፡፡ የመረረ ግለሰባዊ ጥላቻ ማዳበር ወደ ደም አፋሳሽና ከፋፋይ የፖለቲካ ውጥንቅጥ የሚያስገባ መሆኑንም አስተውሎ መገንዘብ ያሻል፡፡

ትግልህ ከፖለቲካዊ ቡድንና ከአስተሳሰባቸው ጋር ብቻ መሆኑንም እርግጠኛ መሆን ያስፈልጋል፡፡ በእኛ ሀገር በግራ ቀኙ ጎራ ፦ የትግራይን የፖለቲካ ሀይሎች መታገልና መቃወም የትግራይን ህዝብ ከመጥላት ፤ የኦሮሞ የፖለቲካ ልሂቃንና አገዛዛቸውን መታገል ወይም መተቸት የኦሮሞን ህዝብ በጅምላ መቃወም አድርጎ የመቁጠር ከንቱ አባዜ ይስተዋላል፡፡ 

ሌላው ቀርቶ ከአንድ ህዝብ መካከል በሚደረግ ትግል የአንዱን አካባቢ የፖለቲካ ቡድን ወይም ፖለቲከኛ መተቸት ሙሉ አካባቢውን የመጥላት ወይም የመቃወም ሂደት እንደሆነ የሚቆጠርበት የነቀዘ ሁኔታን ጧት ማታ እናያለን፡፡ ይህ አይነቱ ከንቱ አስተሳሰብ ሴረኛና ሰነፍ አመራሮችን መደበቂያ ዋሻ እንዲያገኙ ከማድረግና በውስጥ ሽኩቻ ተጠምዶ ከዋና አላማ ከመናጠብ ብሎም የትግልን ሂደት የተንዛዛና አሰልቺ ከማድረግ  በስተቀር አንዳች ለህዝብ የሚጠቅም አወንታዊ ጎን የለውም፡፡

የጠራ የሀሳብና የአላማ መስመር ያለው የፖለቲካ ማህበረሰብ ፥  ከየት ተነስቶ የት መድረስና ብሎም የትኛውን ለይቶ መታገል እንዳለበት ጠንቅቆ ያውቃል! ባልተራዘመ ትግልም ከሚፈልግበት ግብ ላይ ይደርሳል!