Get Mystery Box with random crypto!

ጥቁር ገበያ (black market) ምንድን ነው? 'መንግስት ጥቆማ ስጡኝ ከማለቱ በፊት ራሱን ይ | ዘሪሁን ገሠሠ

ጥቁር ገበያ (black market) ምንድን ነው?

"መንግስት ጥቆማ ስጡኝ ከማለቱ በፊት ራሱን ይፈትሽ!"

በርካታ ደካማ ሀገረ-መንግስት ያለባቸውና በእርስበርስ ጦርነት የሚታመሱ ሀገራት ጥቁር ገበያ የተንሰራፋባቸውና ለእንቅስቃሴው አመቺ ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡

ጥቁር ገበያ እቃዎችን እና አገልግሎቶችን በህገ-ወጥ ፤ ቁጥጥር በማይደረግበት እና ቁጥጥር በሌለው መንገድ የመሸጥ ሂደት ነው፡፡ በንግዱ ህገወጥነት ባህሪ ምክንያትም "ጥቁር ገበያ" ተብሎ ይጠራል፡፡

የጥቁር ገበያ መንግሥት አንዳንድ ህገ-ወጥ ወይም ከተፈቀደላቸው አካላት ውጪ እንዳይገቡ ብሎ የከለከላቸውን ምርቶች ለማስገባትና በውድ ዋጋ ለመሸጥ ሲባል ሊጀመር ይችላል፡፡ የቁጥጥርና የህግ-ማስከበር ስርአቱ ደካማ የሆነ መንግሥት ከሆነ ሂደቱ ከቁጥጥር ውጫ ሆኖ የሀገርን ኢኮኖሚ በማሽመድመድ ፣ የዜጎችን ኑሮ በማበሰቋቆልና የአቅርቦት ችግርን በመፍጠር እጅግ አስከፊ ወደሆነ አዘቅት የማውረድ አቅም አለው፡፡

ጥቁር ገበያ በሰንሰለቱ ውስጥ ያሉትን ከባለሀብቶች ጀምሮ የመንግሥት ባለስልጣናትና ቸርቻሪዎችን በአጭር ጊዜ የናጠጡ ሀብታሞች የሚያደርግ ቢሆንም በሀገርና በህዝብ እንዲሁም በመንግሥት ላይ በርካታ ተፅዕኖዎችን ያሳድራል፡፡

ከነዚህ ተፅዕኖዎች መካከል ፦

ጥቁር ገበያ እንደ ዕፅ፣ የጦር መሣሪያ እና ሌሎች የተከለከሉ አደገኛ ሸቀጦችንና ሕገወጥ ምርቶች እንቅስቃሴን ያመቻቻል።

ሰዎች ለዝሙት አዳሪነት ተሽጠው በውጭ አገር በባርነት የሚሠሩበትን ሕገወጥ የሰዎች ዝውውርን ጨምሮ የሰው ልጅ የአካል ክፍሎች ሽያጭን ያበረታታል።

ጥቁር ገበያ አሸባሪዎችን ለማስታጠቅ እና ሚስጥራዊ መረጃዎችን ለአሸባሪዎች ለመሸጥ እንደ መንገድ ሊያገለግል ይችላል።

በገበያው ውስጥ ደንብ ባለመኖሩ ገዢዎች በጥቁር ገበያ የመታለል ዕድላቸው ከፍተኛ እንዲሆን ያደርጋል፡፡

በጦር መሳሪያ ንግድ እና ህገወጥ ድርጊቶችን በመፈፀም ብዙ ገንዘብ የማግኘት ፍላጎት እየጨመረ ስለሚመጣ የጥቁር ገበያ የወንጀል መጠን እንዲጨምር ዋና ምክንያት ሊሆን ይችላል።

ጥቁር ገበያው በታክስ ስወራ ስለሚታመስና በዘርፉ የተሰማሩት አካላት ለሚያቀርቡት ሸቀጥም ሆነ አገልግሎት ግብር ስለማይከፍሉ ፥ የሀገር ገቢና ኢኮኖሚ እንዲያሽቆለቁል ያደርጋል፡፡

በጥቁር ገበያ የሚሸጡት እቃዎች ዝቅተኛ ጥራት ያላቸው እና በዋስትና ያልተሸፈኑ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡

የጥቁር ገበያው ዋጋ አነስተኛ በሆኑ ምርቶች ላይ የሚሸጥ ሲሆን ይህም ስለ ኢኮኖሚው ሁኔታ የተሳሳተ ግንዛቤ ሊፈጥር ይችላል።

በጥቁር ገበያው የሚገቡ ሸቀጦች ፦ ለምሳሌ የጦር መሳሪያ ፣ ፣መድሀኒቶች ፣ ማሽነሪዎችና ኤሌክትሮኒክሶች ፥ ….ወዘተ የመሳሰሉት ከህጋዊ መሸጫ ዋጋቸው የቀነሱ ስለሚሆኑ ገዢዎች ታክስና ቀረጥ የሚወጣውን ወጪ ለመቀነስ ተመራጭ ስለሚያደርጓቸው ህብረተሰቡንም የድርጊቱ ተባባሪ የማድረግ እድል ይፈጥራሉ፡፡

በመደበኛው የፋይናንስ ስርአት ውስጥ የሚዘዋወረውን ምንዛሬ እንዲያሽቆለቁል በማድረግ ፥ ከፍተኛ የሆነው የውጭ ምንዛሬ ዝውውር ከመንግሥት ቁጥጥር ስርአት ውጭ ባለው በዚህ የጥቁር ገበያ ስርአት ውስጥ እንዲንቀሳቀስ ያደርገዋል፡፡ በግለሰብም ሆነ በተቋም ደረጃ የሚከወኑ ህገ-ወጥ የሀዋላና የገንዘብ ማዘዋወሪያ ስርአቶች ለዚህ አይነተኛ ሚና የሚጫወቱ ይሆናሉ፡፡

ከላይ የተጠቀሰውን ጨምሮ የጥቁር ገበያ ተፅዕኖ እጅግ በርካታና ፈታኝ አረንቋ ውስጥ የሚከት ሲሆን ፥ ይህንን እንቅስቃሴ ለማስቆም የሚችል ጠንካራ መንግስታዊ ስርአት በሌለበት ብሎም የመንግሥት አካላትና ባለስልጣናቱ ከእነዚህ የጥቁር ገበያ ሰንሰለቶች ጋር በጣምራ በሚሠሩበት እንዲሁም ማህበረሰቡ የንቃተ ደረጃ ዝቅተኛ በሆነበት እንደኛ ሀገር ወቅታዊ ሁኔታ ፥ በህዝብና በሀገር ኢኮኖሚ ላይ ከሚፈጥረው ሁለንተናዊ ችግር ባሻገር ሀገርን እስከማፍረስ የደረሰ አስከፊ ውጤት ሊኖረው ወደሚችል ሀገራዊ ምስቅልቅል ሊያደርስ ይችላል፡፡