Get Mystery Box with random crypto!

ፍቅርና ፊዚክስ-2 ..... ካለፈው የቀጠለ       በፍቅር ውስጥ ፍርሃት የለም፤ በፍቅር | ፍልስፍና ለላቀ አስተሳሰብ Philosophy

ፍቅርና ፊዚክስ-2
..... ካለፈው የቀጠለ

     
በፍቅር ውስጥ ፍርሃት የለም፤ በፍቅር ውስጥ ጥርጣሬ የለም፤ ፍቅር በሚወስደን መንገድ ሁሉ በእርግጠኝነት ያለ ፍርሃት እንጓዛለን፡፡ ፍቅር የነገን ህይወት ሳይቀር እርግጠኛ አድርጎ ያሳየናል። በፍቅር፣ በጊዜ አውታር ላይ እንደ ፈለጋችሁ ወደፊትና ወደኋላ እየተመላለሳችሁ ማየት የማትችሉትን ነገንም ሆነ ትናንትን ማየት ትችላላችሁ፡፡

በጊዜ አውታር ላይ ወደፊት ከመጓዝ በስተቀር ወደኋላ መመለስ እንደማይቻል አንስታይን እንቅጩን የነገረን ቢሆንም ጭራሹኑ ተስፋ ቢስ እንዳንሆን ግን አንድ ነገር ሹክ ብሎናል፣

"ልክ እንደ ቦታ አውታር ሁሉ፣ በጊዜ አውታር ላይም እንደፈለጋችሁ ወደፊትና ወደኋላ ለመመላለስ አንድ ነገር ብቻ ያስፈልጋችኋል፤ ከብርሃን ፍጥነት በላይ መጓዝ ብቻ! "

እንዲህ አይነት ደደብ ተስፋ ያናድዳል፡፡ ሰው በማይችለው ነገር ላይ እንዴት እንዲህ ዓይነት ተስፋ ይሰጠዋል! ገና ከፍጥረቱ ጀምሮ እምላክ መሆን የተመኘው ሰው ነገ ላይ ምን ሊከሰት እንደሚችል አለማወቁ ሁልጊዜ እንዳበሳጨው ነው፡፡ ሰው እስከ አሁን ድረስ የወደፊት እጣፈንታው ምን እንደሆነ አላወቀም፡፡ የአንስታይን የማይገመጥ ተስፋ ቢያበሳጨንም አንድ ተጨባጭ ተስፋ ግን አለን፤ እምነትና ፍቅር። እምነትና ፍቅር የደካማነትህ መደጎሚያ፣ የጎዶሎነትህ መሙያ ነው፡፡ በፍቅር ከብርሃን ፍጥነት በላይ ተጉዘን በጊዜ አውታር ላይ እንደፈለግን ወደፊትና ወደኋላ ተመላልሰን ነገንና ትናንትን ማየት ቻልን፡፡

በፍቅር የግራቪቲን ህግ ሽራችሁ እንደፈለጋችሁ ወደ ሰማይ ተነጠቃችሁ፡፡ በርግጥ አንስታይንም ቢሆን ፍቅር ለስበት ሕግ እንደማይገዛ ጠቁሞናል፤ "በፍቅር ብትወድቁ፣ የመሬት ስበት ተጠያቂ አይደለም፤" እናም ውፍቅር ከሕግ በላይ አድርጓችኋል፡፡ ሕግ አመፀኛን መዳኛ መሳሪያ ነው፡፡ ከፍጥረታቸው ባህሪ ውጪ ወደ ሰማይ እንነጠቃለን የሚሉትን የመሬት አመፀኞች ሁሉ ግራቪቲ መሬት ላይ አጣብቆ አሰራቸው፡፡ ፍቅር ውስጥ ግን ምን አመፃ አለ? እናም ፍቅር ከሕግ በላይ አደረጋችሁና እንደፈለጋችሁ ወደ ሰማይ ወደ ጥልቁ፣ ወደ ውቅያኖስ ወደ ስምጡ ተወርዋሪ ሞገድ አደረጋችሁ፣ ልክ ቁስ ግዝፈቱን ሲያጣ ወደ ኢነርጂነት ዝቅ እንደሚለው ሁሉ እናንተንም ፍቅር፣ ደምና ስጋችሁን ሰልቦ፣ ግዝፈታችሁንም አስጥሎ የልብ የሞገድ ብቻ አደረጋችሁ። ስለዚህም አሁን ያለ ክብደት አንዳችሁ በሌላኛው ልብ ውስጥ ሆናችሁ ትጓጓዛላችሁ፡፡ ከፀሀይ ንዝረት (Disturbance) የሚያፈተልከው የብርሃን ሞገድ የፍጥነትን የመጨረሻ ደረጃ የወሰነ ቢሆንም ከልብ ንዝረት የሚረጨው የፍቅር ሞገድ ግን ልኬት አልተገኘለትም። ይህንን የፍቅር ባህሪ የተገነዘበው ኦሾ እንዲህ ይላል፤ "ስፍራን፣ ርቀትንና ጊዜን የሚደመስስ ክስተት ፍቅር ብቻ ነው፡፡"

በዩኒቨርስ ውስጥ የአንድ ቁስ ትክክለኛ መገኛ ቦታ በሦስት አውታሮች (በከፍታ በላቲትዩድና በሎንግቲዩድ) ይገለፃል ሲሉ የነበረ የሂሳብ ሊቆች፣ አንስታይን ከኋላ መጥቶ የጊዜ አውታር በአራተኛነት ካልተጨመረ ትርጉም እንደማይኖረው ካስረዳ በኋላ፣ ማንኛውንም ክስተት በቦታና በጊዜ አውታር መግለጽ ግድ ሆነ፡፡ ኦሾ ግን፣ "ቦታንና ጊዜን የሚደመስስ ክስተት አለ፤" ይላል፡፡ በቦታም ሆነ በጊዜ አውታር የማይለካ፣ በሁሉም ስፍራና ጊዜ የሚዘረጋ፣ የግራቪቲን ሕግ የሚደመስስ ክስተት አለ፣ ፍቅር። "ስፍራን . . ."ይላል ኦሾ "ስፍራን፣ ርቀትንና ጊዜን የሚደመስስ ክስተት ፍቅር ብቻ ነው፡፡ የፍቅር ኬሚስትሪ እስከዛሬ ግንዛቤ አላገኘም፡፡ የፊዚክስ ባለሙያዎች የሚጨነቁት ስለ ስፍራና ጊዜ ነው፡፡ በተፈጥሮ ውስጥ ጊዜና ስፍራ የሚጠፋበት አንድ ታላቅ ቁም ነገር አለ - ፍቅር፡፡

ፍቅር ፍጥነቱ ስንት ቢሆን ነው ስፍራን፣ ርቀትንና ጊዜን የመደምሰስ ሃይል ያገኘው? በፍቅር ከአጠገብህ የሌሉትን ቤተሰቦችህን፣ ልጆችህን፣ ሚስትህን፣ ፍቅረኛህንና፣ ፈጣሪህን ከመቅጽበት ታገኛቸዋለህ፡፡ መቼም በብርሃን ፍጥነት የሚሄድ ባቡር ምንም አይነት ጭረትም ሆነ ስንጥቅ ሳይፈጥር በመስታወት ውስጥ ማለፍ እንደሚችል አንስታይን ነግሮናል፡፡ በምድር ላይ በዚህን ያህል ፍጥነት የሚጓዝ አንድም ነገር እስከ አሁን አላየንም፡፡ በፍቅር ግን ስጋና አጥንትን አልፋችሁ የሰው ልብ ውስጥ ትገባላችሁ፡፡ በዚህም የሰው አእምሮ ውስጥ ፈላጭ ቆራጭ የምትሆኑበትን ግዛት ትፈጥራላችሁ፡፡ እናም ፍቅረኛችሁ ላይ፣ ወላጆቻችሁ ላይና ፈጣሪያችሁ ላይ ሳይቀር ልዩ ግዛት ትመሰርታላችሁ፡፡

ምንጭ ፦ ፍልስፍና ፩
ፀሀፊ ፦ ብሩህ አለምነህ

              ይቀጥላል

@Zephilosophy
@Zephilosophy