Get Mystery Box with random crypto!

ፍቅርና ፊዚክስ-1 ፍቅርና የቦታ-ጊዜ አውታር (Love & Space - Time Dimension) | ፍልስፍና ለላቀ አስተሳሰብ Philosophy

ፍቅርና ፊዚክስ-1
ፍቅርና የቦታ-ጊዜ አውታር (Love & Space - Time Dimension)

እጅግ አስደናቂ፣ እጅግም መሳጭና ረቂቅ ወደ ሆነ ሳይንሳዊ ፍልሰፍና ልወስዳችሁ ነው፡፡ ከዚህ በፊት ፈጽሞ አስባችሁት አታውቁም፤ ሆኖም ግን በውስጡ ኖራችኋል፡፡ ሕግጋቱን አክብራችሁ ተመላልሳችኋል፡፡ ክስተቱ አንዳንዶቻችሁን ገጣሚ፣ ሰዓሊና የውበት አድናቂ አድርጓችኋል፤ አንዳንዶቻችሁን ደግሞ የስቃያችሁ መነሻም ሆና አሳልፋችሁታል፤ ለብዙዎቻችሁ ግን የትዳራችሁ መሠረት ሆኗል፤ ይዘቱን ስትቀይሩለት ደግሞ መንፈሳዊ አድርጓችኋል - ፍቅር፡፡ ፍቅር ስለ ዓለም ያለንን ሸውራራ አመላካከት የምንቀይርበት መነጽር ነው፡፡

ስለፍቅር ምን አዲስ ነገር አለ ብላችሁ እንዳትጠይቁኝ፡፡ እኔ ፍቅርን የማሳያችሁ እናንተ አስቀድማችሁ በምታውቁት መንገድ አይደለም፤ ወይም ደግሞ አርቲስቶችና ደራሲያን ባሳዩዋችሁ መንገድም አይደለም የማሳያችሁ፡፡ ፍቅር ያልተዳሰሰ ሚስጢራዊ ገጽታ አለው፤ እጅግ አስገራሚ ፤ እጅግ አስደናቂ፡፡ ፍቅርን ከፊዚክስ ጋር አነፃጽሮ ማን አየው? ፍቅርን ከኬሚስትሪ ጋር አዋህዶ ማን ተመለከተው? ሌላው ይቅርና ፍቅርን ከመለኮት ጋር አጣምሮ ማየት የተለመደ ቢሆንም እንኳ ክስተቱ ግን በደንብ አልተፈተሸም፡፡

ፍቅርን ከአልበርት አንስታይን አንፃራዊነት ንድፈ ሃሳብ ጋር፣ ከእሾ የፍቅር ምልከታ ጋር እና ከፕሌቶ ሁለንተናዊነት (universals) ጋር ለንቁጣችሁ ብትመለከቱት እጅግ ትደነቃላችሁ፤ በርግጥም ፍቅር ገና ያልተዳሰሰ ብዙ ሚስጢራዊ ገጽታ እንዳለው ትደርሱበታላችሁ፡፡ እናም አሁን እኔ ይሄንን የፍቅር ህብረትና ሚስጥር ላሳያችሁ ተጣድፌያለሁ፡፡ ሆኖም ግን ይሄንን ጽሑፍ ለመረዳት የአንስታይንን "አንፃራዊነት" እና የፕሌቶን "ሁለንተናዊነት" በትንሹም ቢሆን ግንዛቤ ሊኖራችሁ ይገባል፡፡


ሕይወት ከቁስ ስለመሰራቱ ሳይንሳዊም ሆነ ሀይማኖታዊ ድጋፍ ኣለው፡፡ አዳም ከአፈር፣ ሄዋንም ከአዳም መሰራታቸውን ማወቃች፣ ስለፍቅር ጾታዊና ግልብ የሆነ አመለካከት ይዘን እንድንቆይ አድርጎናል። ፍቅርን ከፊዚክስና ከሁለንተናዊነት ጋር ያለውን ግንኙነት እንዳንገናዘብ አዘናግቶናል፡፡አስገራሚ የሚያደርገው አዳም ከአፈር ተፈልቅቆ መሰራቱ ሳይሆን ቁስ ወደ ሕይወት ሲሸጋገር መርሆዎችም አብረው መሸጋገራቸው ነው፡፡ ቁስ ወደ ህይወት ሲሸጋገር ቁስን ሲገዛ የነበረው መርህና ሕግ ሕይወትን መግዛት ጀመረ፡፡ ግራቪቲን፣ ኤሌክትሮ ማግኔቲዝምንና የቅራኔ ህግን እንደምሳሌ መውሰድ እንችላለን፡፡ የእነዚህ ቁሳዊ ሕጎች ተጽእኖ ሕይወት ድረስ ዘልቆ የገባ ነው፡፡ ተቃራኒ የኤሌከትሪክ ሙሌቶች (Charges) እንደሚሳሳቡት ሁሉ ተቃራኒ ዋልታዎችም እርስበርስ እንደሚፈላለጉት ሁሉ፣ ከቁስ የተሰራሁ ሕይወትም ይህንን ሕግና ባሕሪ ወርሷል፤ "አጥንትሽ ከአጥንቴ፣ ደምሽም ከደሜ ነውና የኔ ነሽ!" የሚለውን ሕይወታዊ (የፍቅር) ህግ ቋንቋና ስሜት ዘራንበት እንጂ መርሁን የወሰድነው ከተቃራኒ መግነጢሳዊ ዋልታዎችና የኤሌክትሪክ ሙሌቶች ባህሪ ነው፡፡

ወንዶች የስፐርም ህዋሶቻቸውን ባህሪ እንደወረሱት ሀሉ፣ ሴቶችም የእንቁላላቸውን ባህሪ እንደሚያንፀባርቁት ሁሉ፣ ሕይወትም የተሰራበትን ቁሳዊ ህግና መርህ ያንፀባርቃል፡፡ ቁሳዊ ሕግጋት ፊዚክስን ሲወልድ፣ የህይወት ህግጋት ደግሞ ባዮሎጂን ፈጥሯል፡፡ ባዮሎጂም ወደ ሌሎች ማህበራዊ ሳይንስ ዘርፎች ተመንዝሯል፡፡ የኬሚስትሪ ሕጎች ከፊዚክስ ህጎች እንደሚመነጩ ሁሉ፣ እንዲሁም የባዮሎጂ ህግጋት ከኬሚስትሪ ሕግጋት ይመነጫሉ። ሰነልቦናዊና ማህበረሰባዊ (sociological) መርሆዎችም ከባዮሎጂካዊ ሕግጋት እንደሚመነጩ እርግጥ ነው፡፡ እናም ሕይወት ላይ ፊዚክሱ፣ ኬሚስትሪው፣ ሳይኮሎጂውና ሶሲዮሎጂው ሚስጢራዊ ህብረት አላቸው፡፡

ያፈቀረ ሰው ክብደቱ ስንት ነው? ሚዛን ላይ ብታስቀምጡት ስንት ኪሎ ግራም ይመዝናል? ስታፈቅርና ሳታፈቅር ክብደትህ የተለያየ ይሆን!? በሌላ አነጋገር ፍቅር ክብደቱ ስንት ነው? ነው ወይስ ፍቅር ክብደት የለውም! ምንድነው ታዲያ 400 ፍቅር 300 ትዝታ? ግን እኮ የማይጨበጠውና የማይዳሰሰው ኢነርጂ ክብደት እንዳለው ብንደነግጥም አንስታይን ነግሮናል (energy has mass) ስለዚህ ፍቅርም ክብደት ይኖረው ይሆናል!

"እስከ አሁን..." ይላል ኦሾ፣ "እሰከ አሁን መንገደኛን የሚያጓጉዙ ሁሉ፤ ሰዎች በሌላው ልብ ውስጥ ተደብቀው እንደሚጓዙ አልደረሱበትም።"

እናም ፍቅር ያለ አንዳች ቲኬት በሰው ልብ ውስጥ ሆናችሁ ከቦታ ቦታ እንድትጓዙ አስችሏችኋል፡፡

ቁስ ግዝፈቱን ሲያጣ ኢነርጂ እንደሚሆነው ሁሉ፣ ፍቅርም የሰውን ግዝፈት ዋጋ ያሳጣዋል፣ የራስ ኩራትንም ያስጥላል፡፤ ቁስ ግዝፈቱን ሲያጣ ወደ ብዙ ኃይልነት እንደሚለቀቀው ሁሉ፣ ሰውም ግዝፈቱን ጥሎ ወደ ፍቅር ሲሰየም የበረታ ኃይል ይሆናል፡፡ እናም በዚህ ሀይል መላው አካል ይንቀሳቀሳል፤ ውስብስቡ ባዮኮምፒውተር (አእምሮ) ይታዘዛል።

ብሩህ አለምነህ

ይቀጥላል..
@zephilosophy